2 ሳሙኤል 12:1-10
2 ሳሙኤል 12:1-10 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔርም ነቢዩ ናታንን ወደ ዳዊት ላከ፤ ወደ እርሱም መጥቶ አለው፥ “በአንድ ከተማ አንዱ ባለጠጋ፥ አንዱም ድሃ የሆኑ ሁለት ሰዎች ነበሩ። ባለጠጋውም እጅግ ብዙ የበግና የላም መንጋ ነበረው። ለድሃው ግን ከገዛት አንዲት ታናሽ በግ በቀር አንዳች አልነበረውም፤ አሳደጋትም፤ ተንከባከባትም፤ ከእርሱና ከልጆቹ ጋር አደገች፤ ከእንጀራውም ትበላ፥ ከዋንጫውም ትጠጣ፥ በብብቱም ትተኛ ነበረ፤ እንደ ልጁም ነበረች። ወደ ባለጠጋውም እንግዳ በመጣ ጊዜ ከበጉና ከላሙ ወስዶ ለዚያ ወደ እርሱ ለመጣው እንግዳ ያዘጋጅለት ዘንድ ሳሳ፤ የዚያንም የድሃውን ሰው በግ ወስዶ ለዚያ ለመጣው ሰው አዘጋጀ። ዳዊትም በዚያ ሰው ላይ ተቈጣ፤ ዳዊትም ናታንን፥ “ሕያው እግዚአብሔርን! ይህን ያደረገ ሰው ሞት የሚገባው ነው። ይህን አድርጎአልና፥ አላዘነምና ስለ አንዲቱ በግ አራት አድርጎ ይመልስ” አለው። ናታንም ዳዊትን አለው፥ “ይህን ያደረገ ያ ሰው አንተ ነህ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በእስራኤል ላይ ንጉሥ ልትሆን ቀባሁህ፤ ከሳኦልም እጅ አዳንሁህ፤ የጌታህንም ቤት ሰጠሁህ፤ የጌታህንም ሚስቶች በብብትህ ጣልሁልህ፤ የእስራኤልንና የይሁዳን ቤት ሰጠሁህ፤ ይህም አንሶ ቢሆን ኖሮ ከዚህ የበለጠ እጨምርልህ ነበር። አሁንስ በፊቱ ክፉ ትሠራ ዘንድ የእግዚአብሔርን ነገር ለምን አቃለልህ? ኬጤያዊውን ኦርዮን በሰይፍ መትተሃል፤ ሚስቱንም ለአንተ ሚስት ትሆን ዘንድ ወስደሃል፤ እርሱንም በአሞን ልጆች ሰይፍ ገድለሃል። ስለዚህም አቃልለኸኛልና፥ የኬጤያዊውንም የኦርዮን ሚስት ለአንተ ሚስት ትሆን ዘንድ ወስደሃልና ለዘለዓለም ከቤትህ ሰይፍ አይርቅም።
2 ሳሙኤል 12:1-10 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ናታንን ወደ ዳዊት ላከው፤ እርሱም ወደ ዳዊት መጥቶ እንዲህ አለው፤ “በአንድ ከተማ የሚኖሩ ሁለት ሰዎች ነበሩ፤ ከእነርሱም አንዱ ባለጠጋ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ድኻ ነበረ። ባለጠጋው እጅግ ብዙ በጎችና የቀንድ ከብቶች ነበሩት፤ ድኻው ግን ከገዛት ከአንዲት ጠቦት በግ በቀር ሌላ አልነበረውም። ተንከባከባት፤ ዐብራውም ከልጆቹ ጋራ አደገች፤ ዐብራው ትበላ፤ ከጽዋው ትጠጣ እንዲሁም በዕቅፉ ትተኛ ነበር፤ ልክ እንደ ገዛ ልጁ ነበረች። “ወደ ባለጠጋውም ቤት እንግዳ መጣ፤ ባለጠጋው ግን ከራሱ በጎች ወይም ቀንድ ከብቶች ወስዶ ለመጣበት እንግዳ ምግብ ማዘጋጀት አልፈለገም፤ ከዚህ ይልቅ የድኻውን እንስት ጠቦት በግ ወስዶ ቤቱ ለመጣው እንግዳ አዘጋጀው።” ዳዊት በዚያ ሰው ላይ እጅግ ተቈጥቶ ናታንን እንዲህ አለው፤ “ሕያው እግዚአብሔርን ይህን ያደረገው ሰው ሞት ይገባዋል! እንዲህ ያለውን ነገር በማድረጉና ባለማዘኑም ስለ በጊቱ አራት ዕጥፍ መክፈል አለበት።” ከዚያም ናታን፣ ዳዊትን እንዲህ አለው፤ “ያ ሰው አንተ ነህ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህን ነው፤ ‘በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆን ዘንድ ቀባሁህ፤ ከሳኦልም እጅ ታደግሁህ፤ የጌታህን ቤት ሰጠሁህ፣ የጌታህንም ሚስቶች በብብትህ አስታቀፍሁህ፤ የእስራኤልንና የይሁዳን ቤት ሰጠሁህ፤ ይህም ሁሉ አንሶህ ቢሆን ኖሮ፣ ከዚህ በላይ ጨምሬ በሰጠሁህ ነበር። ታዲያ በፊቱ ክፉ ነገር በማድረግ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ያቃለልኸው ስለ ምንድን ነው? ኬጢያዊውን ኦርዮን በሰይፍ መታህ፤ ሚስት እንድትሆንህም ሚስቱን ወሰድሃት፤ እርሱንም በአሞናውያን ሰይፍ ገደልኸው። ስለዚህ ሰይፍ ለዘላለም ከቤትህ አይርቅም፤ እኔን አቃልለኸኛል፤ ሚስት እንድትሆንህም የኬጢያዊውን የኦርዮን ሚስት ወስደሃታልና።’
2 ሳሙኤል 12:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔርም ናታንን ወደ ዳዊት ላከ፥ ወደ እርሱም መጥቶ አለው፦ በአንድ ከተማ አንዱ ባለጠጋ አንዱም ድሀ የሆኑ ሁለት ሰዎች ነበሩ። ባለጠጋውም እጅግ ብዙ በግና ላም ነበረው። ለድሀው ግን ከገዛት አንዲት ታናሽ በግ በቀር አንዳች አልነበረውም፥ አሳደጋትም፥ ከልጆቹም ጋር በእርሱ ዘንድ አደገች፥ እንጀራውንም ትበላ፥ ከዋንጫውም ትጠጣ፥ በብብቱም ትተኛ ነበር፥ እንደ ልጁም ነበረች። ወደ ባለጠጋውም እንግዳ በመጣ ጊዜ ከበጉና ከላሙ ወስዶ ለዚያ ወደ እርሱ ለመጣው እንግዳ ያዘጋጅለት ዘንድ ሳሳ፥ የዚያንም የድሀውን ሰው በግ ወስዶ ለዚያ ለመጣው ሰው አዘጋጀ። ዳዊትም በዚያ ሰው ላይ እጅግ ተቆጥቶ ናታንን፦ ሕያው እግዚአብሔርን! ይህን ያደረገ ሰው የሞት ልጅ ነው። ይህን አድርጎአልና፥ አላዘነምና ስለ አንዲቱ በግ አራት ይመልስ አለው። ናታንም ዳዊትን አለው፦ ያ ሰው አንተ ነህ። የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በእስራኤል ላይ ንጉሥ ልትሆን ቀባሁህ፥ ከሳኦልም እጅ አዳንሁህ፥ የጌታህን ቤት ሰጠሁህ፥ የጌታህንም ሚስቶች በብብትህ ጣልሁልህ፥ የእስራኤልንና የይሁዳን ቤት ሰጠሁህ ይህም አንሶ ቢሆን ኖሮ ከዚህ የበለጠ እጨምርልህ ነበር። አሁንስ በፊቱ ክፉ ትሠራ ዘንድ የእግዚአብሔርን ነገር ለምን አቃለልህ? ኬጢያዊውን ኦርዮን በሰይፍ መትተሃል፥ ሚስቱንም ለአንተ ሚስት ትሆን ዘንድ ወስደሃል፥ እርሱንም በአሞን ልጆች ሰይፍ ገድለሃል። ስለዚህም አቃልለኽኛልና፥ የኬጢያዊውንም የኦርዮን ሚስት ለአንተ ሚስት ትሆን ዘንድ ወስደሃልና ለዘላለም ከቤትህ ሰይፍ አይርቅም።
2 ሳሙኤል 12:1-10 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ነቢዩን ናታንን ወደ ዳዊት ላከው፤ ናታንም ወደ ዳዊት ሄዶ እንዲህ አለው፤ “በአንድ ከተማ የሚኖሩ ሁለት ሰዎች ነበሩ፤ ከእነርሱ አንዱ ሀብታም ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ድኻ ነበር፤ ሀብታሙ ሰው ብዙ የቀንድ ከብቶችና የበግ መንጋ ነበሩት፤ ድኻው ግን በገንዘቡ የገዛት አንዲት የበግ ግልገል ብቻ ነበረችው፤ እርስዋን እየተንከባከበ ከልጆቹ ጋር በቤቱ ውስጥ ያሳድጋት ነበር፤ ከሚመገበው ይመግባት፥ ከሚጠጣውም ያጠጣት ነበር፤ ስትተኛም ያቅፋት ነበር፤ ያቺም ግልገል ልክ እንደ ልጁ ነበረች፤ አንድ ቀን ወደ ሀብታሙ ሰው ቤት አንድ መንገደኛ መጣ፤ ሀብታሙ ሰው ለእንግዳው የሚሆን ምግብ ለማዘጋጀት ከእንሰሶቹ አንዱን ማረድ አልፈለገም፤ ይህንንም በማድረግ ፈንታ የድኻውን ሰው ግልገል ወስዶ በማረድ ለእንግዳው ምግብ አዘጋጀ።” ዳዊት በሀብታሙ ሰው ታሪክ እጅግ ተቈጥቶ “ይህን ያደረገው ሰው ሞት እንደሚገባው በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ! ይህን የመሰለ የጭካኔ ሥራ በመፈጸሙ ከዚያ ሰው የወሰደበትን አራት እጥፍ አድርጎ መመለስ አለበት” አለ። ናታንም ዳዊትን እንዲህ አለው፤ “ያ ሰው አንተ ራስህ ነህ! የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘እኔ ንጉሥ አደረግኹህ፤ ከሳኦልም እጅ በመታደግ አዳንኩህ፤ መንግሥቱንና ሚስቶቹን ሰጠሁህ፤ በእስራኤልና በይሁዳ ላይ አነገሥኩህ፤ ይህም ሁሉ እንኳ የማይበቃህ ቢሆን ኖሮ በተጨማሪ እጥፍ አድርጌ በሰጠሁህ ነበር፤ ታዲያ ትእዛዜን የናቅኸው ስለምንድን ነው? ይህንንስ ክፉ ነገር ለምን አደረግህ? ኦርዮን በጦር ሜዳ አስገደልከው፤ ንጹሑን ሰው ዐሞናውያን እንዲገድሉት አደረግህ፤ ሚስቱንም ወሰድክ! አንተ ለእኔ ስላልታዘዝክ የኦርዮን ሚስት ስለ ወሰድክ፥ እነሆ ከቤትህ በሰይፍ የሚገደል አይጠፋም፤
2 ሳሙኤል 12:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታ ናታንን ወደ ዳዊት ላከው፤ እርሱም ወደ ዳዊት መጥቶ እንዲህ አለው፤ “በአንድ ከተማ የሚኖሩ ሁለት ሰዎች ነበሩ፤ ከእነርሱም አንዱ ሀብታም ሲሆን፥ ሌላው ደግሞ ድኻ ነበረ። ሀብታሙ እጅግ ብዙ በጎችና የቀንድ ከብቶች ነበሩት፤ ድኻው ግን ከገዛት ከአንዲት ጠቦት በግ በስተቀር ሌላ አልነበረውም። እየተንከባከበ አብራውም ከልጆቹ ጋር አደገች፤ አብራው ትበላ፤ ከጽዋውም ትጠጣ እንዲሁም በዕቅፉ ትተኛ ነበር፤ ልክ እንደገዛ ልጁ ነበረች። ወደ ሀብታሙም ቤት እንግዳ መጣ፤ ሀብታሙ ግን ከራሱ በጎች ወይም ቀንድ ከብቶች ወስዶ ለመጣበት እንግዳ ምግብ ማዘጋጀት አልፈለገም፤ የድኻውን ግልገል ወስዶ ቤቱ ለመጣው እንግዳ አዘጋጀው።” ዳዊት በዚያ ሰው ላይ እጅግ ተቆጥቶ ናታንን እንዲህ አለው፤ “ጌታ ምስክሬ ነው! ይህን ያደረገው ሰው ሞት ይገባዋል! እንዲህ ያለውን ነገር በማድረጉና ባለማዘኑም ስለ ግልገሊቱ አራት ዕጥፍ መክፈል አለበት።” ከዚያም ናታን፥ ዳዊትን እንዲህ አለው፦ “ያ ሰው አንተ ነህ፤ የእስራኤል አምላክ ጌታ የሚለው ይህን ነው፤ ‘በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆን ዘንድ ቀባሁህ፤ ከሳኦልም እጅ ታደግሁህ፤ የጌታህን ቤት ሰጠሁህ፥ የጌታህንም ሚስቶች በእቅፍህ አኖርኩ፤ የእስራኤልንና የይሁዳን ቤትም ሰጠሁህ፤ ይህም ሁሉ አንሶህ ቢሆን ኖሮ፤ ከዚህ በላይ ጨምሬ በሰጠሁህ ነበር። ታዲያ በፊቱ ክፉ ነገር በማድረግ፥ የጌታን ቃል ያቃለልኸው ስለምንድን ነው? ሒታዊውን ኦርዮን በሰይፍ መታህ፤ ሚስት እንድትሆንህም ሚስቱን ወሰድሃት፤ እርሱንም በአሞናውያን ሰይፍ ገደልኸው። ስለዚህ እኔን አቃለኸኛል፤ ሚስት እንድትሆንህም የሒታዊውን የኦርዮን ሚስት ወስደሃታልና፥ ሰይፍ ለዘለዓለም ከቤትህ አይርቅም።’ ”