2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 12:1-10

2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 12:1-10 መቅካእኤ

ጌታ ናታንን ወደ ዳዊት ላከው፤ እርሱም ወደ ዳዊት መጥቶ እንዲህ አለው፤ “በአንድ ከተማ የሚኖሩ ሁለት ሰዎች ነበሩ፤ ከእነርሱም አንዱ ሀብታም ሲሆን፥ ሌላው ደግሞ ድኻ ነበረ። ሀብታሙ እጅግ ብዙ በጎችና የቀንድ ከብቶች ነበሩት፤ ድኻው ግን ከገዛት ከአንዲት ጠቦት በግ በስተቀር ሌላ አልነበረውም። እየተንከባከበ አብራውም ከልጆቹ ጋር አደገች፤ አብራው ትበላ፤ ከጽዋውም ትጠጣ እንዲሁም በዕቅፉ ትተኛ ነበር፤ ልክ እንደገዛ ልጁ ነበረች። ወደ ሀብታሙም ቤት እንግዳ መጣ፤ ሀብታሙ ግን ከራሱ በጎች ወይም ቀንድ ከብቶች ወስዶ ለመጣበት እንግዳ ምግብ ማዘጋጀት አልፈለገም፤ የድኻውን ግልገል ወስዶ ቤቱ ለመጣው እንግዳ አዘጋጀው።” ዳዊት በዚያ ሰው ላይ እጅግ ተቆጥቶ ናታንን እንዲህ አለው፤ “ጌታ ምስክሬ ነው! ይህን ያደረገው ሰው ሞት ይገባዋል! እንዲህ ያለውን ነገር በማድረጉና ባለማዘኑም ስለ ግልገሊቱ አራት ዕጥፍ መክፈል አለበት።” ከዚያም ናታን፥ ዳዊትን እንዲህ አለው፦ “ያ ሰው አንተ ነህ፤ የእስራኤል አምላክ ጌታ የሚለው ይህን ነው፤ ‘በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆን ዘንድ ቀባሁህ፤ ከሳኦልም እጅ ታደግሁህ፤ የጌታህን ቤት ሰጠሁህ፥ የጌታህንም ሚስቶች በእቅፍህ አኖርኩ፤ የእስራኤልንና የይሁዳን ቤትም ሰጠሁህ፤ ይህም ሁሉ አንሶህ ቢሆን ኖሮ፤ ከዚህ በላይ ጨምሬ በሰጠሁህ ነበር። ታዲያ በፊቱ ክፉ ነገር በማድረግ፥ የጌታን ቃል ያቃለልኸው ስለምንድን ነው? ሒታዊውን ኦርዮን በሰይፍ መታህ፤ ሚስት እንድትሆንህም ሚስቱን ወሰድሃት፤ እርሱንም በአሞናውያን ሰይፍ ገደልኸው። ስለዚህ እኔን አቃለኸኛል፤ ሚስት እንድትሆንህም የሒታዊውን የኦርዮን ሚስት ወስደሃታልና፥ ሰይፍ ለዘለዓለም ከቤትህ አይርቅም።’ ”