2 ቆሮንቶስ 9:8-12
2 ቆሮንቶስ 9:8-12 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔር መልካሙን ነገር ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል፤ ፍጹም በረከቱንም ለዘወትር ያበዛላችሁ ዘንድ፥ ለሁሉም ታተርፉታላችሁ፤ በጎ ሥራ መሥራትንም ታበዛላችሁ። “በተነ፤ ለድሃም ሰጠ፤ ጽድቁም ለዘለዓለም ይኖራል” ብሎ መጽሐፍ እንደ ተናገረ። እርሱ ዘርን ለዘሪ ይሰጣል፤ እህልንም ለምግብ ይሰጣችኋል፤ ዘራችሁንም ያበዛላችኋል፤ የጽድቃችሁንም መከር ያበጃል። ለብዙ ሰዎች ስለ ሰጣችሁም የእግዚአብሔርን ምስጋና በምታደርግላችሁ ልግስና ሁሉ ባለጸጎች ትሆናላችሁ። ይህቺ የዚህ ሥራ አገልግሎት ግዳጅ የምትፈጽመው ለዚህ ለቅዱሳን ችግር መሟላት ብቻ አይደለም፤ በቅዱሳን ዘንድም ደግሞ የእግዚአብሔርን ምስጋና ታበዛለች።
2 ቆሮንቶስ 9:8-12 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሁልጊዜ በሁሉ ነገር የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ አግኝታችሁ ለበጎ ሥራ ሁሉ እንድትተርፉ፣ እግዚአብሔር ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል፤ ይህም፣ “በተነ፤ ለድኾችም ሰጠ፤ ጽድቁ ለዘላለም ይኖራል” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው። ለዘሪ ዘርን፣ ለመብላት እንጀራን የሚሰጥ እርሱ የምትዘሩትን አትረፍርፎ ይሰጣችኋል፤ የጽድቃችሁንም ፍሬ ያበዛላችኋል። ሁልጊዜ በልግስና መስጠት እንድትችሉ በሁሉ ነገር ያበለጽጋችኋል፤ ልግስናችሁም በእኛ በኩል የሚደርሳቸው ሰዎች እግዚአብሔርን ለማመስገን ምክንያት ይሆናቸዋል። ይህ የምትሰጡት አገልግሎት የቅዱሳንን ጕድለት የሚያሟላ ብቻ ሳይሆን፣ ብዙ ምስጋና ለእግዚአብሔር የሚቀርብበት ነው።
2 ቆሮንቶስ 9:8-12 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በተነ፥ ለምስኪኖች ሰጠ፥ ጽድቁ ለዘላለም ይኖራል ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ እግዚአብሔር፥ ሁልጊዜ በነገር ሁሉ ብቃትን ሁሉ አግኝታችሁ ለበጎ ሥራ ሁሉ ትበዙ ዘንድ፥ ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል። ለዘሪ ዘርን ለመብላትም እንጀራን በብዙ የሚሰጥ እርሱም የምትዘሩትን ዘር ይሰጣችኋል ያበረክትላችሁማል፥ የጽድቃችሁንም ፍሬ ያሳድጋል፤ በእኛ በኩል ለእግዚአብሔር የምስጋና ምክንያት የሚሆነውን ልግስና ሁሉ እንድታሳዩ በሁሉ ነገር ባለ ጠጎች ትሆናላችሁ። የዚህ ረድኤት አገልግሎት ለቅዱሳን የሚጎድላቸውን በሙሉ የሚሰጥ ብቻ አይደለምና፥ ነገር ግን ደግሞ በብዙ ምስጋና ለእግዚአብሔር ይበዛል፤
2 ቆሮንቶስ 9:8-12 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሁልጊዜ በሁሉ ነገር ራሳችሁን ችላችሁ ለመልካም ሥራ ሁሉ ለማዋል እንዲበቃችሁ እግዚአብሔር በብዛት በረከቱን ሊሰጣችሁ ይችላል። ይህም፦ “ለድኾች በልግሥና ሰጠ፤ ጽድቁም ለዘለዓለም ይኖራል” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው። ለዘሪ ዘርን፥ ለምግብ እንጀራን የሚሰጥ አምላክ የምትዘሩትን ዘር አበርክቶ ይሰጣችኋል፤ የልግሥናችሁንም ፍሬ ያበዛላችኋል። ልግሥናችሁ በእኛ አማካይነት የሚደርሳቸው ሰዎች ሁሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ዘንድ ሁልጊዜ እንድትለግሡ እግዚአብሔር በሁሉ ነገር ያበለጽጋችኋል። ይህ የምትፈጽሙት የልግሥና አገልግሎት የክርስቲያኖችን ችግር ከማስወገዱም በላይ ሰዎች ለእግዚአብሔር ብዙ ምስጋና እንዲያቀርቡ ያደርጋቸዋል።
2 ቆሮንቶስ 9:8-12 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሁልጊዜ በነገር ሁሉ ብቃትን አግኝታችሁ በበጎ ሥራ በቸርነት እንድትለግሱ፥ እግዚአብሔር ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል። ይህም፥ “በተነ፤ ለድኾችም ሰጠ፤ ጽድቁ ለዘለዓለም ይኖራል፤” ተብሎ ተጽፏል። ለዘሪ ዘርን፥ ለመብላትም እንጀራን የሚሰጥ፥ እርሱ የምትዘሩትን ዘር ይሰጣችኋል፤ ያበረክትላችሁማል፤ የጽድቃችሁንም ፍሬ ያሳድጋል፤ በእኛ በኩል እግዚአብሔርን የማመስገኛ ምክንያት የሚሆነውን ልግስናችሁ በሁሉ ነገር ባለ ጠጎች ያደርጋችኋል። የዚህ አገልግሎት ረድኤት ለቅዱሳን የሚጎድላቸውን በሙሉ የሚሰጥ ብቻ ሳይሆን ለእግዚአብሔር የሚቀርብ ብዙ ምስጋና ምክንያትም ነው።

