መጽሐፈ ነህምያ 9:6-28

መጽሐፈ ነህምያ 9:6-28 አማ54

አንተ ብቻ እግዚአብሔር ነህ፥ ሰማዩንና የሰማያት ሰማይን ሠራዊታቸውንም ሁሉ፥ ምድሩንና በእርስዋ ላይ ያሉትን ሁሉ፥ ባሕሮቹንና በእነርሱ ውስጥ ያለውን ሁሉ፥ ፈጥረሃል፥ ሁሉንም ሕያው አድርገኸዋል፥ የሰማዩም ሠራዊት ለአንተ ይሰግዳሉ። አንተ እግዚአብሔር አምላክ ነህ፥ አብራምን መረጥህ፥ ከዑር ከላውዴዎንም አወጣኸው፥ ስሙንም አብርሃም አልኸው፥ ልቡም በፊትህ የታመነ ሆኖ አገኘኸው፥ የከነዓናዊውንና የኬጢያዊውን የአሞራዊውንም የፌርዛዊውንም የኢያቡሳዊውንም የጌርጌሳዊውንም ምድር ለእርሱና ለዘሩ ትሰጥ ዘንድ ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረግህ፥ አንተም ጻድቅ ነህና ቃልህን ፈጸምህ። በግብጽም ሳሉ የአባታችንን መከራ አየህ፥ በኤርትራ ባሕርም ሳሉ ጩኸታቸውን ሰማህ፥ እንደ ታበዩባቸውም አውቀህ ነበርና በፈርዖንና በባሪያዎቹ ሁሉ በምድሩም ሕዝብ ሁሉ ላይ ምልክትና ተአምራት አሳየህ፥ ዛሬም እንደ ሆነው ስምህን አስጠራህ። ከፊታቸውም ባሕሩን ከፈልህ፥ በባሕሩም መካከል በደረቅ አለፉ፥ ጠላቶቻቸውን ግን ድንጋይ ለጥልቅ ውኃ እንዲጣል በቀላይ ውስጥ ጣልሃቸው። የሚሄዱበትንም መንገድ ታበራላቸው ዘንድ በቀን በደመና ዓምድ፥ በሌሊትም በእሳት ዓምድ መራሃቸው። ወደ ሲናም ተራራ ወረድህ፥ ከሰማይም ተናገርሃቸው፥ ቅኑን ፍርድና እውነቱን ሕግ መልካሙንም ሥርዓትና ትእዛዝ ሰጠሃቸው፥ የተቀደሰውንም ሰንበትህን አስታወቅሃቸው፥ ትእዛዝንና ሥርዓትን ሕግንም በባሪያህ በሙሴ እጅ አዘዝሃቸው። ለራባቸውም ከሰማይ እንጀራ ሰጠሃቸው፥ ለጥማታቸውም ከዓለቱ ውኃ አመጣህላቸው፥ ወደ ማልህላቸውም ምድር ገብተው ይወርሱ ዘንድ አዘዝሃቸው። ነገር ግን እነርሱና አባቶቻችን ታበዩ፥ አንገታቸውንም አደነደኑ፥ ትእዛዝህንም አልሰሙም፥ ለመስማትም እንቢ አሉ፥ ያደረግህላቸውንም ተአምራት አላሰቡም፥ አንገታቸውንም አደነደኑ፥ በዓመፃቸውም ወደ ባርነታቸው ይመለሱ ዘንድ አለቃ አደረጉ፥ አንተ ግን ይቅር ባይ፥ ቸርና መሐሪ አምላክ፥ ለቁጣም የምትዘገይ፥ ምሕረትንም የምታበዛ ነህ፥ አልተውሃቸውም። ቀልጦ የተሠራውንም እምቦሳ አድርገው፦ ከግብጽ ያወጣህ አምላክህ ይህ ነው ባሉ ጊዜ፥ እጅግም ባስቈጡህ ጊዜ፥ አንተ በምሕረትህ ብዛት በምድረ በዳ አልተውሃቸውም፥ በመንገድም ይመራቸው ዘንድ የደመና ዓምድ በቀን፥ የሚሄዱበትንም መንገድ ያበራላቸው ዝነድ የእሳት ዓምድ በሌሊት ከእነርሱ አልራቀም። ያስተምራቸውም ዘንድ መልካሙን መንፈስህን ሰጠሃቸው፥ መናህንም ከአፋቸው አልከለከልህም፥ ለጥማታቸውም ውኃ ሰጠሃቸው። አርባ ዓመትም በምድረ በዳ መገብሃቸው፥ ምንም አላጡም፥ ልብሳቸውም አላረጀም፥ እግራቸውም አላበጠም። መንግሥታትንና አሕዛብን ከፍለህ ሰጠሃቸው፥ የሐሴቦንን ንጉሥ የሴዎንን ምድር፥ የባሳንንም ንጉሥ የዐግን ምድር ወረሱ። ልጆቻቸውንም እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛህ፥ ይገቡና ይወርሱ ዘንድ ለአባቶቻቸው ወደ ተናገርህላቸውም ምድር አገባሃቸው። ልጆቹም ገብተው ምድሩን ወረሱ፥ የምድሩን ሰዎች ከነዓናውያንን በፊታቸው አዋረድህ፥ የሚወድዱትንም ነገር ያደረጉባቸው ዘንድ እነርሱንና ነገሥታቶቻቸውን የምድሩንም አሕዛብ በእጃቸው አሳልፈህ ሰጠሃቸው። ምሽጎቹንም ከተሞች የሰባውንም ምድር ወሰዱ፥ መልካሙን ነገር የሞሉትን ቤቶች፥ የተማሱትንም ጕድጓዶች፥ ወይኖቹንና ወይራዎቹን ብዙዎቹንም የፍሬ ዛፎች ወረሱ፥ በሉም፥ ጠገቡም፥ ወፈሩም፥ በታላቅ በጎነትህም ደስ አላቸው። ነገር ግን እንቢተኞች ነበሩ፥ ዐመፁብህም፥ ሕግህንም ወደ ኋላቸው ጣሉት፥ ወደ አንተም ይመለሱ ዘንድ የመሰከሩባቸውን ነቢያትህን ገደሉ፥ እጅግም አስቈጡህ። ስለዚህ ለጠላቶቻቸው እጅ አሳልፈህ ሰጠሃቸው፥ አስጨነቁአቸውም፥ በመከራቸውም ጊዜ ወደ አንተ ጮኹ፥ ከሰማይም ሰማሃቸው፥ እንደ ምሕረትህም ብዛት ከጠላቶቻቸው እጅ ያዳኑአቸውን ታዳጊዎችን ሰጠሃቸው። ባረፉም ጊዜ ተመልሰው በፊትህ ክፉ አደረጉ፥ በጠላቶቻቸው እጅ ተውሃቸው፥ ገዙአቸውም፥ ተመልሰውም ወደ አንተ በጮኹ ጊዜ ከሰማይ ሰማሃቸው፥ እንደ ምሕረትህም ብዛት ታደግሃቸው፥