ሰቈቃወ ኤርምያስ 2:5-19

ሰቈቃወ ኤርምያስ 2:5-19 አማ54

ሄ። ጌታ እንደ ጠላት ሆነ፥ እስራኤልን ዋጠ፥ አዳራሾችዋን ሁሉ ዋጠ፥ አምቦችዋን አጠፋ፥ በይሁዳም ሴት ልጅ ኀዘንና ልቅሶ አበዛ። ዋው። ማደሪያውን እንደ አትክልት ነቀለ፥ የበዓሉን ስፍራ አጠፋ፥ እግዚአብሔር በጽዮን ዓመት በዓሉንና ሰንበቱን አስረሳ፥ በቍጣውም መዓት ንጉሡንና ካህኑን አቃለለ። ዛይ። ጌታ መሠዊያውን ጣለ፥ መቅደሱን ጠላ፥ የአዳራሾችዋንም ቅጥር በጠላት እጅ አሳልፎ ሰጠ፥ ድምፃቸውን እንደ ዓመት በዓል ቀን በእግዚአብሔር ቤት ከፍ ከፍ አደረጉ። ሔት። እግዚአብሔር የጽዮንን ሴት ልጅ ቅጥር ያፈርስ ዘንድ አሰበ፥ የመለኪያውን ገመድ ዘረጋ፥ እጁን ከማጥፋት አልመለሰም፥ ምሽጉና ቅጥሩ እንዲያለቅሱ አደረገ፥ በአንድነት ደከሙ። ጤት። በሮችዋ በመሬት ውስጥ ሰጠሙ፥ መወርወሪያዎችዋን አጠፋ ሰበረም፥ ንጉሥዋና አለቆችዋ ሕግ በሌለባቸው በአሕዛብ መካከል አሉ፥ ነቢያቶችዋም ከእግዚአብሔር ዘንድ ራእይ አላገኙም። ዮድ። የጽዮን ሴት ልጅ ሽማግሌዎች ዝም ብለው በመሬት ላይ ተቀምጠዋል፥ ትቢያን በራሳቸው ላይ ነሰነሱ፥ ማቅም ታጠቁ፥ የኢየሩሳሌም ደናግል ራሳቸውን ወደ ምድር አዘነበሉ። ካፍ። ሕፃኑና ጡት የሚጠባው በከተማይቱ ጐዳና ላይ ሲዝሉ፥ ዓይኔ በእንባ ደከመች፥ አንጀቴም ታወከ፥ ስለ ወገኔ ሴት ልጅ ቅጥቃጤ ጉበቴ በምድር ላይ ተዘረገፈ። ላሜድ። በከተማ ጐዳና እንደ ተወጋ ሰው በዛሉ ጊዜ፥ ነፍሳቸውም በእናቶቻቸው ብብት በወጣች ጊዜ፥ እናቶቻቸውን፦ እህልና የወይን ጠጅ ወዴት አለ? ይሉአቸዋል። ሜም። የኢየሩሳሌም ሴት ልጅ ሆይ፥ ምን እመሰክርልሻለሁ? በምንስ እመስልሻለሁ? ድንግሊቱ የጽዮን ልጅ ሆይ፥ አጽናናሽ ዘንድ በምን አስተካክልሻለሁ? ስብራትሽ እንደ ባሕር ታላቅ ነውና፥ የሚፈውስሽ ማን ነው? ኖን። ነቢያቶችሽ ከንቱና ሐሰተኛ ራእይ አይተውልሻል፥ ምርኮሽንም ይመልሱ ዘንድ በደልሽን አልገለጡም፥ ከንቱና የማይረባ ነገርንም አይተውልሻል። ሳምኬት። መንገድ አላፊዎች ሁሉ እጃቸውን ያጨበጭቡብሻልና፦ በውኑ የውበት ፍጻሜና የምድር ሁሉ ደስታ የሚሉአት ከተማ ይህች ናትን? እያሉ፥ በኢየሩሳሌም ሴት ልጅ ላይ ያፍዋጫሉ፥ ራሳቸውንም ያነቃንቃሉ። ዔ። ጠላቶችሽ ሁሉ አፋቸውን አላቀቁብሽ፥ እያፍዋጩና ጥርሳቸውን እያፋጩ፦ ውጠናታል፥ ነገር ግን ተስፋ ያደረግናት ቀን ይህች ናት፥ አግኝተናታል አይተናትማል ይላሉ። ፌ። እግዚአብሔር ያሰበውን አደረገ፥ በቀድሞ ዘመን ያዘዘውን ቃል ፈጸመ፥ አፈረሰ አልራራምም፥ ጠላትንም ደስ አሰኘብሽ፥ የሚያስጨንቁሽንም ቀንድ ከፍ ከፍ አደረገ። ጻዴ። ልባቸው ወደ ጌታ ጮኸ፥ የጽዮን ሴት ልጅ ቅጥር ሆይ፥ እንባሽን እንደ ፈሳሽ ቀንና ሌሊት አፍስሺ፥ ለሰውነትሽ ዕረፍት አትስጪ፥ የዓይንሽ ብሌን አታቋርጥ። ቆፍ። ተነሺ፥ በሌሊት በመጀመሪያ ክፍል ጩኺ፥ በጌታም ፊት ልብሽን እንደ ውኃ አፍስሺ፥ በጐዳና ሁሉ ራስ ላይ በራብ ስለ ደከሙ ስለ ሕፃናትሽ ነፍስ እጆችሽን ወደ እርሱ አንሺ።