እንዲህም ሆነ፥ በዮርዳኖስ ማዶ በተራራማው በቈላማውም በታላቁ ባሕር ዳር በሊባኖስም ፊት ለፊት የነበሩ ነገሥታት ሁሉ፥ ኬጢያዊ አሞራዊም ከነዓናዊም ፌርዛዊም ኤዊያዊም ኢያቡሳዊም፥ ይህን በሰሙ ጊዜ፥ ኢያሱንና እስራኤልን ሊወጉ አንድ ሆነው ተሰበሰቡ። የገባዖን ሰዎች ግን ኢያሱ በኢያሪኮና በጋይ ያደረገውን በሰሙ ጊዜ፥ እነርሱ ደግሞ ተንኰል አደረጉ፥ ለራሳቸውም ስንቅ ያዙ፥ በአህዮቻቸውም ላይ አሮጌ ዓይበትና ያረጀና የተቀደደ የተጠቀመም የጠጅ አቁማዳ ጫኑ። ያረጀ የተጠቀመም ጫማ በእግራቸው አደረጉ አሮጌም ልብስ ለበሱ፥ ለስንቅም የያዙት እንጀራ ሁሉ የደረቀና የሻገተ ነበረ። ኢያሱም ወደ ሰፈረበት ወደ ጌልገላ ሄደው ለእርሱና ለእስራኤል ሰዎች፦ ከሩቅ አገር መጥተናል፥ አሁንም ከእኛ ጋር ኪዳን አድርጉ አሉ። የእስራኤልም ሰዎች ኤዊያውያን፦ ምናልባት በመካከላችን የምትቀመጡ እንደ ሆነ እንዴትስ ከእናንተ ጋር ቃል ኪዳን እናደርጋለን? አሉአቸው። ኢያሱንም፦ እኛ ባሪያዎችህ ነን አሉት። ኢያሱም፦ እናንተ እነማን ናችሁ? ከወዴትስ መጣችሁ? አላቸው። እነርሱም አሉት፦ ከአምላክህ ከእግዚአብሔር ስም የተነሣ እጅግ ከራቀ አገር ባሪያዎችህ መጥተናል፥ ዝናውንም፥ በግብፅም ያደረገውን ሁሉ፥ በዮርዳኖስ ማዶም በነበሩት በሁለቱ በአሞራውያን ነገሥታት በሐሴቦን ንጉሥ በሴዎን በአስታሮትም በነበረው በባሳን ንጉሥ በዐግ ያደረገውን ሁሉ ሰምተናል። ሽማግሌዎቻችንም በምድራችንም የሚኖሩት ሁሉ፦ ለመንገድ ስንቅ በእጃችሁ ያዙ፥ ልትገናኙአቸውም ሂዱ፦ እኛ ባሪያዎቻችሁ ነን፥ አሁንም ከእኛ ጋር ቃል ኪዳን አድርጉ በሉአቸው አሉን። ወደ እናንተ ለመምጣት በተነሣንበት ቀን ይህን እንጀራ ትኩሱን ለስንቅ ከቤታችን ወሰድነው፥ አሁንም እነሆ፥ ደርቆአል፥ ሻግቶአልም። እነዚህም የጠጅ አቁማዳዎች አዲስ ሳሉ ሞላንባቸው፥ እነሆም፥ ተቀድደዋል፥ መንገዳችንም እጅግ ስለ ራቀብን እነዚህ ልብሶቻችንና ጫማዎቻችን አርጅተዋል። ሰዎቹም ከስንቃቸው ወሰዱ፥ እግዚአብሔርንም አልጠየቁም። ኢያሱም ከእነርሱ ጋር ሰላም አደረገ፥ በሕይወት እንዲተዋቸውም ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፥ የማኅበሩም አለቆች ማሉላቸው።
መጽሐፈ ኢያሱ 9 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ኢያሱ 9:1-15
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች