መጽሐፈ ኢያሱ 6:20-27

መጽሐፈ ኢያሱ 6:20-27 አማ54

ሕዝቡም ጮኹ፥ ካህናቱም ቀንደ መለከቱን ነፉ፥ ሕዝቡም የቀንደ መለከቱን ድምፅ በሰሙ ጊዜ ታላቅ ጩኸት ጮኹ፥ ቅጥሩም ወደቀ፥ ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ አቅንቶ ወደ ፊቱ ወደ ከተማይቱ ወጣ፥ ከተማይቱንም ወሰዱ። በከተማይቱም የነበሩትን ሁሉ፥ ወንዱንና ሴቱን፥ ሕፃኑንና ሽማግሌውን፥ በሬውንም በጉንም አህያውንም፥ በሰይፍ ስለት ፈጽመው አጠፉ። ኢያሱም ምድሪቱን የሰለሉ ሁለቱን ሰዎች፦ ወደ ጋለሞታይቱ ቤት ግቡ፥ ከዚያም ሴቲቱንና ያላትን ሁሉ እንደ ማላችሁላት አውጡ አላቸው። ሰላዮቹም ብላቴናዎች ገብተው ረዓብን፥ አባትዋንና እናትዋን፥ ወንድሞችዋንም፥ ያላትንም ሁሉ፥ ቤተ ዘመዶችዋንም ሁሉ አወጡ፥ ከእስራኤልም ሰፈር በውጭ አስቀመጡአቸው። ከተማይቱንም በእርስዋም የነበረውን ሁሉ በእሳት አቃጠሉ፥ ነገር ግን ብሩንና ወርቁን የናሱንና የብረቱንም ዕቃ በእግዚአብሔር ግምጃ ቤት አደረጉት። ኢያሪኮን ሊሰልሉ ኢያሱ የሰደዳቸውንም መልክተኞች ስለ ሸሸገች ጋለሞታይቱን ረዓብን፥ የአባትዋንም ቤተ ሰብ፥ ያላትንም ሁሉ ኢያሱ አዳናቸው፥ እርስዋም በእስራኤል መካከል እስከ ዛሬ ድረስ ተቀምጣለች። በዚያን ጊዜም ኢያሱ፦ ይህችን ከተማ ኢያሪኮን ለመሥራት የሚነሣ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ርጉም ይሁን፥ መሠረትዋን ሲጀምር በኩር ልጁ ይጥፋ፥ በርዋንም ሲያቆም ታናሹ ልጁ ይጥፋ ብሎ ማለ። እግዚአብሔርም ከኢያሱ ጋር ነበረ፥ ዝናውም በምድር ሁሉ ላይ ወጣ።