ኢያሱ 6:20-27
ኢያሱ 6:20-27 NASV
መለከቱ ሲነፋ ሕዝቡ ጮኸ፤ የመለከቱ ድምፅ ተሰምቶ፣ ሕዝቡ በኀይል ሲጮኽ ቅጥሩ ፈረሰ፤ እያንዳንዱም ሰው ሰተት ብሎ ገባ፤ ከተማዪቱም በእጃቸው ወደቀች። በከተማዪቱ ውስጥ ያለውን ሁሉ፣ ማለትም ወንዱንና ሴቱን፣ ወጣቱንና ሽማግሌውን፣ ከብቱንና በጉን እንዲሁም አህያውን በሰይፍ ስለት ፈጽመው አጠፉ። ኢያሱ ምድሪቱን የሰለሉትን ሁለቱን ሰዎች፣ “ወደ ጋለሞታዪቱ ቤት ሂዱ፤ በማላችሁላትም መሠረት እርሷንና የእርሷ የሆነውን ሁሉ ከዚያ አውጡ” አላቸው። ስለዚህ ሁለቱ ወጣት ሰላዮች ገብተው ረዓብን፣ አባቷንና እናቷን፣ ወንድሞቿንና የእርሷ የሆኑትን ሁሉ ከዚያ አወጧቸው። ቤተ ዘመዶቿንም ሁሉ አውጥተው ከእስራኤል ሰፈር ውጭ አስቀመጧቸው። ከዚያም ከተማዪቱን በሙሉ፣ በውስጧ ያለውንም ሁሉ አቃጠሉ፤ ብሩንና ወርቁን፣ የናሱንና የብረቱን ዕቃ ግን በእግዚአብሔር ግምጃ ቤት አኖሩ። ኢያሪኮን እንዲሰልሉ ኢያሱ የላካቸውን ሰዎች ስለ ደበቀች፣ ጋለሞታዪቱን ረዓብን፣ ቤተ ሰቧንና የእርሷ የሆኑትን ሁሉ አዳናቸው፤ እርሷም እስከ ዛሬ ድረስ በእስራኤላውያን መካከል ትኖራለች። በዚያ ጊዜም ኢያሱ፣ እንዲህ ሲል ማለ፤ “ይህች ከተማ ኢያሪኮን መልሶ የሚሠራት ሰው በእግዚአብሔር ፊት የተረገመ ይሁን፤ “መሠረቷን ሲጥል፣ የበኵር ልጁ ይጥፋ፤ ቅጥሮቿንም ሲያቆም፣ የመጨረሻ ልጁ ይጥፋ” ብሎ ማለ። ስለዚህ እግዚአብሔር ከኢያሱ ጋራ ነበር፤ ዝናውም በምድሪቱ ሁሉ ላይ ወጣ።

