መጽሐፈ ኢያሱ 22:1-5
መጽሐፈ ኢያሱ 22:1-5 አማ54
በዚያን ጊዜም ኢያሱ የሮቤልን ልጆችና የጋድን ልጆች የምናሴንም ነገድ እኩሌታ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ የእግዚአብሔር ባርያ ሙሴ ያዘዛችሁን ሁሉ ጠብቃችኋል፥ እኔም ላዘዝኋችሁ ነገር ሁሉ ታዝዛችኋል፥ ይህንም ያህል ብዙ ጊዜ እስከ ዛሬ ድረስ ወንድሞቻችሁን አልተዋችሁም፥ የአምላካችሁንም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ጠብቃችኋል። አሁንም አምላካችሁ እግዚአብሔር እንደ ተናገራቸው ወንድሞቻችሁን አሳርፎአቸዋል፥ አሁን እንግዲህ ተመለሱ፥ ወደ ቤታችሁና የእግዚአብሔር ባርያ ሙሴ በዮርዳኖስ ማዶ ወደ ሰጣችሁ ወደ ርስታችሁ ምድር ሂዱ። ብቻ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ያዘዛችሁን ትእዛዙንና ሕጉን ታደርጉ ዘንድ፥ አምላካችሁን እግዚአብሔርን ትወድዱ ዘንድ፥ መንገዱንም ሁሉ ትሄዱ ዘንድ፥ ትእዛዙንም ትጠብቁ ዘንድ፥ ከእርሱም ጋር ትጠጉ ዘንድ፥ በፍጹምም ልባችሁ በፍጹምም ነፍሳችሁ ታመልኩ ዘንድ እጅግ ተጠንቀቁ።

