መጽሐፈ ኢያሱ 21:1-19

መጽሐፈ ኢያሱ 21:1-19 አማ54

የሌዋውያን አባቶች አለቆች ወደ ካህኑ ወደ አልዓዛር፥ ወደ ነዌም ልጅ ወደ ኢያሱ፥ ወደ እስራኤልም ልጆች ነገዶች አለቆች ቀረቡ፥ በከነዓን ምድር ባለችው በሴሎ፦ እግዚአብሔር በሙሴ እጅ የምንቀመጥባቸውን ከተሞች፥ ለከብቶቻችንም መሰምርያዎች ትሰጡን ዘንድ አዝዞአል ብለው ተናገሩአቸው። የእስራኤልም ልጆች እንደ እግዚአብሔር ትእዛዝ ከርስታቸው እነዚህን ከተሞችና መሰምርያቸውን ለሌዋውያን ሰጡ። ለቀዓትም ወገኖች ዕጣ ወጣ፥ ሌዋውያንም ለነበሩ ለካህኑ ለአሮን ልጆች ከይሁዳ ነገድ፥ ከስምዖንም ነገድ፥ ከብንያምም ነገድ አሥራ ሦስት ከተሞች በዕጣ ሆኑላቸው። ለቀሩትም ለቀዓት ልጆች ከኤፍሬም ነገድ፥ ከዳንም ነገድ፥ ከምናሴም ነገድ እኩሌታ አሥር ከተሞች በዕጣ ሆኑላቸው። ለጌድሶንም ልጆች ከይሳኮር ነገድ፥ ከአሴርም ነገድ፥ ከንፍታሌምም ነገድ፥ በባሳንም ካለው ከምናሴ ነገድ እኩሌታ አሥራ ሦስት ከተሞች በዕጣ ሆኑላቸው። ለሜራሪም ልጆች በየወገኖቻቸው ከሮቤል ነገድ፥ ከጋድም ነገድ፥ ከዛብሎንም ነገድ አሥራ ሁለት ከተሞች ሆኑላቸው። እግዚአብሔርም በሙሴ እጅ እንዳዘዘ የእስራኤል ልጆች እነዚህን ከተሞችና መሰምርያቸውን ለሌዋውያን በዕጣ ሰጡ። ከይሁዳም ልጆች ነገድ ከስምዖንም ልጆች ነገድ በስማቸው የተጠሩትን እነዚህን ከተሞች ሰጡ። የፊተኛው ዕጣ ለእነርሱ ስለ ወጣ የሌዊ ልጆች የቀዓት ወገን ለሆኑ ለአሮን ልጆች ሆኑ። በይሁዳ ተራራማ አገር ያለችውን ቂርያትአርባቅ የምትባለውን ከተማ በዙሪያዋም ያለውን መሰምርያ ሰጡአቸው፥ እርስዋም ኬብሮን ናት፥ ይህም አርባቅ የዔናቅ አባት ነበረ። የከተማይቱን እርሻ ግን መንደሮችዋንም ለዮፎኔ ልጅ ለካሌብ ርስት አድርገው ሰጡት። ለካህኑም ለአሮን ልጆች እነዚህን ሰጡ፥ ለነፍሰ ገዳይ መማፀኛ ከተማ የሆነችውን ኬብሮንና መሰምርያዋን፥ ልብናንና መሰምርያዋን፥ የቲርንና መሰምርያዋን፥ ኤሽትሞዓንና መሰምርያዋን፥ ሖሎንንና መሰምርያዋን፥ ዳቤርንና መሰምርያዋን፥ ዓይንንና መሰምርያዋን፥ ዮጣንና መሰምርያዋን፥ ቤትሳሜስንና መሰምርያዋን፥ ከእነዚህ ከሁለቱ ነገዶች ዘጠኝ ከተሞችን ሰጡ። ከብንያምም ነገድ ገባዖንንና መሰምርያዋን፥ ናሲብንና መሰምርያዋን፥ አናቶትንና መሰምርያዋን፥ አልሞንና መሰምርያዋን፥ አራት ከተሞችን ሰጡ። የአሮን ልጆች የካህናት ከተሞች ከመሰምርያቸው ጋር አሥራ ሦስት ናቸው።