የሌዊ ነገድ ቤተሰቦች መሪዎች ወደ ካህኑ አልዓዛር፥ ወደ ነዌ ልጅ ኢያሱና ወደ እስራኤል ሕዝብ የነገድ መሪዎች ሄዱ፤ በዚያም በከነዓን ምድር በምትገኘው በሴሎ ወደ እነርሱ ፊት ቀርበው፦ “እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት የምንኖርባቸው ከተሞችና በዙሪያቸውም ለከብቶቻችን ግጦሽ የሚሆን መሬት እንዲሰጠን አዞአል” አሉአቸው። ስለዚህም በእግዚአብሔር ትእዛዝ መሠረት የእስራኤል ሕዝብ ለሌዋውያን የሚከተሉትን ከተሞችና ለከብት ግጦሽ የሚሆን መሬት ከርስቶቻቸው ከፍለው ሰጡአቸው። የመጀመሪያው ዕጣ ለቀዓት ጐሣ ወጣ፤ ከሌዊ ነገድ ለካህኑ ለአሮን ልጆች ዐሥራ ሦስት ከተሞች በዕጣ ተከፋፈለ፤ እነዚህም ከተሞች የተወሰዱት ከይሁዳ፥ ከስምዖንና ከብንያም ነገዶች ይዞታዎች ነበር፤ ለቀሪው ለቀዓት ጐሣ ከኤፍሬም፥ ከዳንና ከምዕራብ ምናሴ ይዞታዎች ዐሥር ከተሞች በዕጣ ተመደቡለት። ለጌርሾን ጐሣ ከይሳኮር፥ ከአሴር፥ ከንፍታሌምና በባሳን ካለው ከምሥራቅ ምናሴ ግዛት ይዞታዎች ተከፍለው ዐሥራ ሦስት ከተሞች ተመደቡለት። ለመራሪ ጐሣ እንደየወገናቸው ከሮቤል፥ ከጋድና ከዛብሎን ይዞታዎች ተከፍለው ዐሥራ ሁለት ከተሞች ተመደቡላቸው። በሙሴ አማካይነት እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት የእስራኤል ሕዝብ እነዚህን ከተሞችና የግጦሽ ምድር ለሌዋውያን በዕጣ አካፈሉአቸው። ከይሁዳና ከስምዖን ነገዶች በስም የተጠቀሱትን የሚከተሉትን ከተሞች ሰጡ፤ የመጀመሪያው ዕጣ ለእነርሱ ስለ ወጣ ከሌዊ ነገድ የአሮን ዘሮች ለሆኑት ለቀዓት ወገኖች ተሰጠ። በይሁዳ ተራራማ አገር ያለችውን ቂርይትአርባቅ የምትባለውን ከተማ፥ በዙሪያዋ ካለው የግጦሽ መሬት ጋር ሰጡአቸው፤ እርስዋም ኬብሮን ናት፤ ይህም አርባቅ የዐናቅ አባት ነበር። ይሁን እንጂ በከተማይቱ የሚገኘው የእርሻ ቦታና በክልልዋ ውስጥ ያሉት መንደሮች አስቀድሞ ለይፉኔ ልጅ ለካሌብ ርስት ሆነው ተሰጥተዋል። ከመማጸኛ ከተሞች አንድዋ ከሆነችው ኬብሮን ከግጦሽ መሬትዋ ጋር በተጨማሪ ለካህኑ ለአሮን ዘሮች ከዚህ የሚከተሉት ከተሞች ተመደቡላቸው፤ እነርሱም ሊብና፥ ከግጦሽ መሬትዋ ጋር፥ ያቲር፥ ኤሽተሞዓ፥ ሖሎን ከግጦሽ መሬትዋ ጋር፥ ደቢር፥ ከግጦሽ መሬትዋ ጋር ዓይን ከግጦሽ መሬትዋ ጋር፥ ዩጣና ከግጦሽ መሬትዋ ጋር፥ ቤትሼሜሽ ከግጦሽ መሬትዋ ጋር ከይሁዳና ከስምዖን ምድር ተከፍለው የተሰጡ ዘጠኝ ከተሞች ናቸው። ከብንያም ግዛት ተከፍለው አራት ከተሞች ተሰጡአቸው። እነርሱም ከግጦሽ ምድራቸው ጋር ገባዖን፥ ጌባዕ፥ ዐናቶትና ዐልሞን ተብለው የሚጠሩት ናቸው። የአሮን ዘሮች ለሆኑት ካህናት ከግጦሽ ምድራቸው ጋር በድምሩ ዐሥራ ሦስት ከተሞች ተመደቡላቸው።
መጽሐፈ ኢያሱ 21 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ኢያሱ 21:1-19
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች