አሁንም ያዕቆብ ሆይ፥ የፈጠረህ፥ እስራኤልም ሆይ፥ የሠራህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ተቤዥቼሃለሁና አትፍራ፥ በስምህም ጠርቼሃለሁ፥ አንተ የእኔ ነህ። በውኃ ውስጥ ባለፍህ ጊዜ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፥ በወንዞችም ውስጥ ባለፍህ ጊዜ አያሰጥሙህም፥ በእሳትም ውስጥ በሄድህ ጊዜ አትቃጠልም፥ ነበልባሉም አይፈጅህም። እኔ የእስራኤል ቅዱስ አምላክህ እግዚአብሔር መድኃኒትህ ነኝ፥ ግብጽን ለአንተ ቤዛ አድርጌ፥ ኢትዮጵያንና ሳባንም ለአንተ ፋንታ ሰጥቻለሁ። በዓይኔ ፊት የከበርህና የተመሰገንህ ነህና፥ እኔም ወድጄሃለሁና ስለዚህ ሰዎችን ለአንተ አሕዛብንም ለነፍስህ እሰጣለሁ። እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፥ ዘርህንም ከምሥራቅ አመጣዋለሁ፥ ከምዕራብም እሰበስብሃለሁ። ሰሜንን፦ መልሰህ አምጣ፥ ደቡብንም፦ አትከልክል፥ ወንዶች ልጆቼን ከሩቅ ሴቶች ልጆቼንም ከምድር ዳርቻ፥ በስሜ የተጠራውን ለክብሬም የፈጠርሁትን፥ የሠራሁትንና ያደረግሁትን ሁሉ አምጣ እለዋለሁ። ዓይኖች ያሉአቸውን ዕውሮችን ሕዝብ፥ ጆሮዎችም ያሉአቸውን ደንቆሮቹን አውጣ። አሕዛብ ሁሉ በአንድነት ይሰብሰቡ ወገኖችም ይከማቹ፥ ከመካከላቸው ይህን የሚናገር፥ የቀድሞውንስ ነገር የሚያሳየን ማን ነው? ይጸድቁ ዘንድ ምስክሮቻቸውን ያምጡ፥ ሰምተውም፦ እውነት ነው ይበሉ። ታውቁና ታምኑብኝ ዘንድ እኔም እንደ ሆንሁ ታስተውሉ ዘንድ፥ እናንተ የመረጥሁትም ባሪያዬ ምስክሮቼ ናችሁ ይላል እግዚአብሔር፥ ከእኔ በፊት አምላክ አልተሠራም ከእኔም በኋላ አይሆንም። እኔ፥ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ ከእኔ ሌላም የሚያድን የለም። ተናግሬአለሁ አድኜማለሁ አሳይቼማለሁ፥ በእናንተም ዘንድ ባዕድ አምላክ አልነበረም፥ ስለዚህ እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ እኔም አምላክ ነኝ። ከጥንት ጀምሮ እኔ ነኝ ከእጄም የሚያመልጥ የለም፥ እሠራለሁ፥ የሚከለክልስ ማን ነው? የእስራኤል ቅዱስ፥ የሚቤዣችሁ፥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ስለ እናንተ ወደ ባቢሎን ሰድጃለሁ፥ ከላዳውያንንም ሁሉ ስደተኞች አድርጌ በሚመኩባቸው መርከቦች አዋርዳቸዋለሁ። ቅዱሳችሁ፥ የእስራኤል ፈጣሪ፥ ንጉሣችሁ፥ እግዚአብሔር እኔ ነኝ። እግዚአብሔር በባሕር ውስጥ መንገድን በኃይለኛም ውኃ ውስጥ መተላለፊያን ያደርጋል፥ እግዚአብሔር ሰረገላውንና ፈረሱን ሠራዊቱንና አርበኛውን ያወጣል፥ እነርሱ ግን በአንድነት ተኝተዋል፥ አይነሡም፥ ቀርተዋል፥ እንደ ጥዋፍ ኩስታሪም ጠፍተዋል፥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የፊተኛውን ነገር አታስታውሉ፥ የጥንቱንም ነገር አታስቡ። እነሆ፥ አዲስ ነገርን አደርጋለሁ፥ እርሱም አሁን ይበቅላል፥ እናንተም አታውቁትምን? በምድረ በዳም መንገድን በበረሃም ወንዞችን አደርጋለሁ። ምሥጋናዬን እንዲናገሩ ለእኔ የፈጠርሁት ሕዝብ፥ የመረጥሁትን ሕዝቤን አጠጣ ዘንድ በምድረ በዳ ውኃን በበረሀም ወንዞችን ሰጥቻለሁና የምድረ በዳ አራዊት፥ ቀበሮችና ሰጎኖች፥ ያከብሩኛል።
ትንቢተ ኢሳይያስ 43 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ ኢሳይያስ 43:1-21
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች