ኢሳይያስ 43:1-21
ኢሳይያስ 43:1-21 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አሁንም ያዕቆብ ሆይ፥ የፈጠረህ፥ እስራኤልም ሆይ፥ የሠራህ እግዝአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ተቤዥችሃለሁና አትፍራ፤ በስምህም ጠርቼሃለሁ፤ አንተ የእኔ ነህ። በውኃ ውስጥ ባለፍህ ጊዜ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ ወንዞችም አያሰጥሙህም፤ በእሳትም ውስጥ በሄድህ ጊዜ አትቃጠልም፤ ነበልባሉም አይፈጅህም። እኔ የእስራኤል ቅዱስ አምላክህ እግዚአብሔር መድኀኒትህ ነኝ፤ ግብፅንና ኢትዮጵያን ለአንተ ቤዛ አድርጌ፥ ሴዎንንም ለአንተ ፋንታ ሰጥቻለሁ። በፊቴ የከበርህና የተመሰገንህ ነህና፥ እኔም ወድጄሃለሁና ስለዚህ ብዙ ሰዎችን ለአንተ ቤዛ፥ አለቆችንም ለራስህ እሰጣለሁ። እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ ዘርህንም ከምሥራቅ አመጣዋለሁ፤ ከምዕራብም እሰበስብሃለሁ። ሰሜንን፦ መልሰህ አምጣ፤ ደቡብምን፦ አትከልክል፤ ወንዶች ልጆችን ከሩቅ፥ ሴቶች ልጆችንም ከምድር ዳርቻ፥ በስሜ የተጠራውን ለክብሬም የፈጠርሁትን፥ የሠራሁትንና ያደረግሁትን ሁሉ አምጣ” እለዋለሁ። ዐይኖች እያሉአቸው የማያዩ ዕውሮችን ሕዝብ፥ ጆሮችም እያሉአቸው የማይሰሙ ደንቆሮዎችን አወጣሁ። አሕዛብ ሁሉ በአንድነት ተሰበሰቡ፤ አለቆችም ተከማቹ፤ ይህን ማን ይናገራል? የቀድሞውንስ ማን ይነግራችኋል? ይጸድቁ ዘንድ ምስክሮቻቸውን ያምጡ፤ ሰምተውም፦ እውነትን ይናገሩ። ታውቁና ታምኑብኝ ዘንድ እኔም እንደ ሆንሁ ታስተውሉ ዘንድ፥ እናንተ፥ የመረጥሁትም ባሪያዬ ምስክሮች ሁኑ፤ እኔም ምስክር እሆናችኋለሁ ይላል እግዚአብሔር አምላክ፤ ከእኔ በፊት አምላክ አልነበረም፤ ከእኔም በኋላ አይኖርም። እኔ፥ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔ ሌላ የሚያድን አምላክ የለም። ተናግሬአለሁ፤ አድኜማለሁ፤ መክሬማለሁ፤ በእናንተም ዘንድ ባዕድ አምልኮ አልነበረም፤ ስለዚህ እኔ እግዚአብሔር አምላክ እንደ ሆንሁ እናንተ ራሳችሁ ምስክሮች ናችሁ፤ ከጥንት ጀምሮ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእጄም የሚያመልጥ የለም፤ እሠራለሁ፤ ወደ ኋላስ የሚመልስ ማን ነው? የእስራኤል ቅዱስ፥ የሚቤዣችሁ፥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ስለ እናንተ ወደ ባቢሎን ሰድጃለሁ፤ ስደተኞችን አስነሣለሁ፤ ከለዳውያንም በመርከብ ውስጥ ይታሰራሉ። ቅዱሳችሁ፥ የእስራኤል ፈጣሪ፥ ንጉሣችሁ፥ እግዚአብሔር አምላክ እኔ ነኝ።” በባሕር ውስጥ መንገድን በኀይለኛም ውኃ ውስጥ መተላለፊያን ያደረገ እግዚአብሔር አምላክ እንዲህ ይላል፦ እግዚአብሔር ሰረገላውንና ፈረሱን ሠራዊቱንና አርበኛውን ያወጣል፤ እነርሱ ግን በአንድነት ተኝተዋል፤ አይነሡም፤ ቀርተዋል፤ እንደ ጥዋፍ ኩስታሪም ጠፍተዋል፤ የፊተኛውን ነገር አታስታውሱ፤ የጥንቱንም ነገር አታስቡ። እነሆ፥ አዲስ ነገርን አደርጋለሁ፤ እርሱም አሁን ይበቅላል፤ እናንተም አታውቁትም፤ በምድረ በዳም መንገድን፥ በበረሃም ወንዞችን አደርጋለሁ። የምድረ በዳ አራዊት፥ ቀበሮችና ሰጎኖች፥ ያከብሩኛል። የመረጥሁትን ሕዝቤን አጠጣ ዘንድ በምድረ በዳ ውኃን፥ በበረሃም ወንዞችን ሰጥቻለሁና፤ እነርሱም ምስጋናዬን እንዲናገሩ ለእኔ የፈጠርኋቸው ሕዝብ ናቸው፤
ኢሳይያስ 43:1-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አሁን ግን፣ ያዕቆብ ሆይ የፈጠረህ፣ እስራኤል ሆይ! የሠራህ፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ተቤዥቼሃለሁና አትፍራ፤ በስምህ ጠርቼሃለሁ፤ አንተ የእኔ ነህ፤ በውሃ ውስጥ በምታልፍበት ጊዜ፣ ከአንተ ጋራ እሆናለሁ፤ ወንዙን ስትሻገረው፣ አያሰጥምህም፤ በእሳት ውስጥ ስትሄድ፣ አያቃጥልህም፤ ነበልባሉም አይፈጅህም። እኔ እግዚአብሔር አምላክህ፣ የእስራኤልም ቅዱስ መድኀኒትህ ነኝና፤ ግብጽን ለአንተ ቤዛ እንድትሆን፣ ኢትዮጵያንና ሳባን በአንተ ፈንታ እሰጣለሁ። ለዐይኔ ብርቅና ክቡርም ስለ ሆንህ፣ እኔም ስለምወድድህ፣ ሰዎችን በአንተ ምትክ፣ ሕዝቦችንም በሕይወትህ ፈንታ እሰጣለሁ። ከአንተ ጋራ ነኝና አትፍራ፤ ልጆችህን ከምሥራቅ አመጣለሁ፤ ከምዕራብም እሰበስብሃለሁ። ሰሜንን፣ ‘አምጣ!’ ደቡብንም፣ ‘ልቀቅ’ እላለሁ፤ ወንዶች ልጆቼን ከሩቅ፣ ሴቶች ልጆቼንም ከምድር ዳርቻ፣ በስሜ የተጠራውን ሁሉ፣ ለክብሬ የፈጠርሁትን፣ ያበጀሁትንና የሠራሁትን አምጡ።” ዐይን እያላቸው የታወሩትን፣ ጆሮ እያላቸው የደነቈሩትን አውጣ። ሕዝብ ሁሉ በአንድነት ይሰብሰብ፤ ሰውም ይከማች፤ ከእነርሱ አስቀድሞ ይህን የነገረን፣ የቀድሞውን ነገር ያወጀልን ማን ነው? ሌሎችን ሰምተው፣ “እውነት ነው” እንዲሉ፣ ትክክለኝነታቸውም እንዲረጋገጥ ምስክሮቻቸውን ያቅርቡ። “ታውቁና ታምኑብኝ ዘንድ፣ እርሱ እኔ እንደ ሆንሁ ትረዱ ዘንድ፣ እናንተ ምስክሮቼ፣ የመረጥሁትም ባሪያዬ ናችሁ” ይላል እግዚአብሔር። “ከእኔ በፊት አምላክ አልተሠራም፤ ከእኔም በኋላ አይኖርም። እኔ፣ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔም ሌላ የሚያድን የለም። ገልጫለሁ፤ አድኛለሁ፤ ተናግሬአለሁ፤ በመካከላችሁ እኔ እንጂ ባዕድ አምላክ አልነበረም። እኔ አምላክ እንደ ሆንሁ፣ እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ” ይላል እግዚአብሔር፤ “ከጥንት ጀምሮ እኔው ነኝ፤ ከእጄም ማውጣት የሚችል የለም፤ እኔ የምሠራውን ማን ማገድ ይችላል?” የእግዚአብሔር የእስራኤል ቅዱስ፣ የሚቤዣችሁ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ስለ እናንተ በባቢሎን ላይ ሰራዊት እሰድዳለሁ፤ በሚመኩባቸውም መርከቦች፣ ባቢሎናውያንን ሁሉ እንደ ኰብላይ አመጣለሁ። እኔ እግዚአብሔር፣ የእናንተ ቅዱስ፣ የእስራኤል ፈጣሪ፣ ንጉሣችሁ ነኝ።” በባሕር ውስጥ መንገድ፣ በማዕበል ውስጥ መተላለፊያ ያበጀ፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ እንደ ገና ላይነሡ እዚያው እንዲተኙ፣ እንደ ጧፍ ኵስታሪ ረግፈው እንዲጠፉ፣ ሠረገሎችንና ፈረሶችን፣ ሰራዊቱንና ደጀኑን በአንድነት ያወጣ እንዲህ ይላል፤ “የቀደመውን ነገር አታስቡ፤ ያለፈውን እርሱ። እነሆ፤ አዲስ ነገር አደርጋለሁ! እርሱም አሁን ይበቅላል፤ አታስተውሉትምን? በምድረ በዳም መንገድ አዘጋጃለሁ፤ በበረሓም ምንጭ አፈልቃለሁ፤ የምድረ በዳ አራዊት፣ ቀበሮና ጕጕት ያከብሩኛል፤ በምድረ በዳ ውሃ፣ በበረሓም ምንጭ እሰጣለሁና። ለመረጥሁት ሕዝቤ ውሃ እሰጣለሁ፤ ለራሴ ያበጀሁት ሕዝብ ምስጋናዬን ያውጅ ዘንድ ይህን አደርጋለሁ።
ኢሳይያስ 43:1-21 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
አሁንም ያዕቆብ ሆይ፥ የፈጠረህ፥ እስራኤልም ሆይ፥ የሠራህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ተቤዥቼሃለሁና አትፍራ፥ በስምህም ጠርቼሃለሁ፥ አንተ የእኔ ነህ። በውኃ ውስጥ ባለፍህ ጊዜ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፥ በወንዞችም ውስጥ ባለፍህ ጊዜ አያሰጥሙህም፥ በእሳትም ውስጥ በሄድህ ጊዜ አትቃጠልም፥ ነበልባሉም አይፈጅህም። እኔ የእስራኤል ቅዱስ አምላክህ እግዚአብሔር መድኃኒትህ ነኝ፥ ግብጽን ለአንተ ቤዛ አድርጌ፥ ኢትዮጵያንና ሳባንም ለአንተ ፋንታ ሰጥቻለሁ። በዓይኔ ፊት የከበርህና የተመሰገንህ ነህና፥ እኔም ወድጄሃለሁና ስለዚህ ሰዎችን ለአንተ አሕዛብንም ለነፍስህ እሰጣለሁ። እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፥ ዘርህንም ከምሥራቅ አመጣዋለሁ፥ ከምዕራብም እሰበስብሃለሁ። ሰሜንን፦ መልሰህ አምጣ፥ ደቡብንም፦ አትከልክል፥ ወንዶች ልጆቼን ከሩቅ ሴቶች ልጆቼንም ከምድር ዳርቻ፥ በስሜ የተጠራውን ለክብሬም የፈጠርሁትን፥ የሠራሁትንና ያደረግሁትን ሁሉ አምጣ እለዋለሁ። ዓይኖች ያሉአቸውን ዕውሮችን ሕዝብ፥ ጆሮዎችም ያሉአቸውን ደንቆሮቹን አውጣ። አሕዛብ ሁሉ በአንድነት ይሰብሰቡ ወገኖችም ይከማቹ፥ ከመካከላቸው ይህን የሚናገር፥ የቀድሞውንስ ነገር የሚያሳየን ማን ነው? ይጸድቁ ዘንድ ምስክሮቻቸውን ያምጡ፥ ሰምተውም፦ እውነት ነው ይበሉ። ታውቁና ታምኑብኝ ዘንድ እኔም እንደ ሆንሁ ታስተውሉ ዘንድ፥ እናንተ የመረጥሁትም ባሪያዬ ምስክሮቼ ናችሁ ይላል እግዚአብሔር፥ ከእኔ በፊት አምላክ አልተሠራም ከእኔም በኋላ አይሆንም። እኔ፥ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ ከእኔ ሌላም የሚያድን የለም። ተናግሬአለሁ አድኜማለሁ አሳይቼማለሁ፥ በእናንተም ዘንድ ባዕድ አምላክ አልነበረም፥ ስለዚህ እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ እኔም አምላክ ነኝ። ከጥንት ጀምሮ እኔ ነኝ ከእጄም የሚያመልጥ የለም፥ እሠራለሁ፥ የሚከለክልስ ማን ነው? የእስራኤል ቅዱስ፥ የሚቤዣችሁ፥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ስለ እናንተ ወደ ባቢሎን ሰድጃለሁ፥ ከላዳውያንንም ሁሉ ስደተኞች አድርጌ በሚመኩባቸው መርከቦች አዋርዳቸዋለሁ። ቅዱሳችሁ፥ የእስራኤል ፈጣሪ፥ ንጉሣችሁ፥ እግዚአብሔር እኔ ነኝ። እግዚአብሔር በባሕር ውስጥ መንገድን በኃይለኛም ውኃ ውስጥ መተላለፊያን ያደርጋል፥ እግዚአብሔር ሰረገላውንና ፈረሱን ሠራዊቱንና አርበኛውን ያወጣል፥ እነርሱ ግን በአንድነት ተኝተዋል፥ አይነሡም፥ ቀርተዋል፥ እንደ ጥዋፍ ኩስታሪም ጠፍተዋል፥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የፊተኛውን ነገር አታስታውሉ፥ የጥንቱንም ነገር አታስቡ። እነሆ፥ አዲስ ነገርን አደርጋለሁ፥ እርሱም አሁን ይበቅላል፥ እናንተም አታውቁትምን? በምድረ በዳም መንገድን በበረሃም ወንዞችን አደርጋለሁ። ምሥጋናዬን እንዲናገሩ ለእኔ የፈጠርሁት ሕዝብ፥ የመረጥሁትን ሕዝቤን አጠጣ ዘንድ በምድረ በዳ ውኃን በበረሀም ወንዞችን ሰጥቻለሁና የምድረ በዳ አራዊት፥ ቀበሮችና ሰጎኖች፥ ያከብሩኛል።
ኢሳይያስ 43:1-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የያዕቆብ ልጆች እስራኤላውያን ሆይ! የፈጠራችሁ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የታደግኋችሁ ስለ ሆነ አትፍሩ፤ እናንተ የእኔ ናችሁ፤ በስማችሁም ጠርቼአችኋለሁ። በውሃ ውስጥ በምታልፉበት ጊዜ እኔ ከእናንተ ጋር እሆናለሁ፤ በወንዞች መካከል በምታልፉበት ጊዜ አያሰጥሙአችሁም፤ በእሳትም ውስጥ በምታልፉበት ጊዜ አያቃጥላችሁም፤ ነበልባሉም ዐመድ አያደርጋችሁም። እኔ የእስራኤል ቅዱስ እግዚአብሔር አምላካችሁና አዳኛችሁ ነኝ፤ እናንተን ለመታደግ ግብጽን፥ ኢትዮጵያውያንንና ሳባን እሰጣለሁ። እናንተ በእኔ ፊት የተወደዳችሁ ናችሁ፤ ስለምወዳችሁ ሕይወታችሁን ለማዳን ሕዝቦችንና መንግሥታችን አሳልፌ እሰጣለሁ። እኔ ከእናንተ ጋር ስለ ሆንኩ አትፍሩ፤ ከምሥራቅም ከምዕራብም እናንተንና ልጆቻችሁን ሰብስቤ አመጣለሁ። “ወንዶች ልጆቼ ከሩቅ አገር እንዲመጡ በሰሜን በኩል ያሉትን አገሮች ተዉአቸው፥ በደቡብ በኩል ያሉትን አገሮች ‘አትያዙአቸውም’ ብዬ አዛለሁ። እነርሱ በስሜ የተጠሩና ለክብሬ የፈጠርኳቸው በእጄም የአበጀኋቸውና የሠራኋቸው ሕዝቤ ናቸው።” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ዐይን እያላቸው የማያዩ ጆሮ እያላቸው የማይሰሙ፥ ሕዝቤን በአንድነት ሰብስቡ! ሕዝቦች ሁሉ በአንድነት ይሰብሰቡ፤ ከእነርሱ መካከል የአሁንና የቀድሞዎቹን ነገሮች አስቀድሞ የተናገረና የገለጠ ማነው? እውነተኛነታቸውን ለማረጋገጥ ምስክሮቻቸውን ያምጡ። እነርሱም ሰምተው እውነት ነው ይበሉ። “እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ተረድታችሁ ታውቁኝና ታምኑብኝ ዘንድ የመረጥኳችሁ አገልጋዮቼና ምስክሮቼ እናንተ ናችሁ። በእርግጥ ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ የለም፤ ከእዚህ በፊት አልነበረም፤ ወደ ፊትም አይኖርም። “እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከእኔም ሌላ የሚያድን የለም እኔ ወደፊት የሚሆነውን ነገር አስቀድሜ ተናግሬአለሁ፤ እናንተን ያዳንኩ እኔ ነኝ፤ ከባዕዳን አማልክት አንድ እንኳ ይህን አላደረገም፤ ለዚህ ሁሉ እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ። እኔ ከጥንት ጀምሮ አምላክ ነኝ፤ ከእጄ ማንም ማንንም አያድንም፤ እኔ ያደረግኹትን መለወጥ የሚችል የለም።” አዳኛችሁ የእስራኤል ቅዱስ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ስለ እናንተ በባቢሎን ላይ የሚዘምት ሠራዊት እልካለሁ፤ የከተማዋን ቅጽር በሮች እሰባብራለሁ፤ የባቢሎናውያንም ፉከራ ወደ ለቅሶ ይለወጣል። እኔ እግዚአብሔር የእናንተ ቅዱስ አምላክ ነኝ፤ እስራኤል ሆይ! እኔ ፈጠርኳችሁ፤ ንጉሣችሁም እኔ ነኝ።” እግዚአብሔር በባሕር መካከል መንገድን ሠራ፤ በውሃ መካከል መተላለፊያን አበጀ፥ ሠረገሎችንና ፈረሶችን፥ የጦር ሠራዊትንና ጀግኖችን ወደ ጥፋታቸው መራቸው፤ እነርሱ ወደቁ፤ ዳግመኛም አይነሡም፤ እፍ ሲሉት እንደሚጠፋ ጧፍም ሆኑ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ያለፉትን ድርጊቶች አታስታውሱ፤ ከዚህ በፊት የሆነውንም ነገር አታሰላስሉ። ይልቅስ የማደርገውን አዲስ ነገር ተመልከቱ፤ እርሱም በመፈጸም ላይ ስለ ሆነ ልታዩት ትችላላችሁ፤ በበረሓ መንገድን አወጣለሁ፤ በምድረ በዳም ወንዞችን አፈልቃለሁ። ለተመረጡት ሕዝቤ ውሃን ለመስጠት ወንዞች በበረሓ ጅረቶች በምድረ በዳ እንዲፈስሱ ባደረግሁ ጊዜ የምድር አራዊት እንኳ ሳይቀሩ ያከብሩኛል፤ ቀበሮዎችና ሰጎኖችም ያመሰግኑኛል። እነርሱም ለራሴ የሠራኋቸው ሕዝቦች ስለ ሆኑ እኔን ያመሰግናሉ።”
ኢሳይያስ 43:1-21 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አሁንም ያዕቆብ ሆይ፥ የፈጠረህ፥ እስራኤልም ሆይ፥ የሠራህ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ተቤዥቼሃለሁና አትፍራ፤ በስምህም ጠርቼሃለሁ፥ አንተ የእኔ ነህ። በውኃ ውስጥ ባለፍህ ጊዜ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፥ በወንዞችም ውስጥ ባለፍህ ጊዜ አያሰምጡህም፤ በእሳትም ውስጥ በሄድህ ጊዜ አትቃጠልም፤ ነበልባሉም አይፈጅህም። እኔ የእስራኤል ቅዱስ አምላክህ ጌታ መድኃኒትህ ነኝ፤ ግብጽን ለአንተ ቤዛ አድርጌ፥ ኢትዮጵያንና ሳባንም ለአንተ ፋንታ እሰጣለሁ። በዓይኔ ፊት የከበርህና የተመሰገንህ ነህና፥ እኔም ወድጄሃለሁና ስለዚህ ሰዎችን ለአንተ፥ አሕዛብንም ለነፍስህ እሰጣለሁ። እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ ዘርህንም ከምሥራቅ አመጣዋለሁ፥ ከምዕራብም እሰበስብሃለሁ። ሰሜንን፦ “መልሰህ አምጣ፥” ደቡብንም፦ “ልቀቅ፥ ወንዶች ልጆቼን ከሩቅ ሴቶች ልጆቼንም ከምድር ዳርቻ፥ አምጣ እለዋለሁ፤ በስሜ የተጠራውን ለክብሬም የፈጠርሁትን፥ የሠራሁትንና ያደረግሁትን ሁሉ።” ዐይኖች ያሏቸውን ዕውር ሕዝቦችን፥ ጆሮዎችም ያሏቸውን ደንቆሮቹን አውጣ! አሕዛብ ሁሉ በአንድነት ይሰብሰቡ፥ ወገኖችም ይከማቹ፤ ከመካከላቸው ይህን የሚናገር፥ የቀድሞውንስ ነገር የሚያሳየን ማን ነው? እንዲጸድቁ ምስክሮቻቸውን ያምጡ፥ ሰምተውም፦ “እውነት ነው” ይበሉ። ታውቁና ታምኑብኝ ዘንድ እኔም እንደሆንሁ ታስተውሉ ዘንድ፥ እናንተ የመረጥሁትም አገልጋዬ ምስክሮቼ ናችሁ ይላል ጌታ፤ ከእኔ በፊት አምላክ አልተሠራም ከእኔም በኋላ አይኖርም። እኔ፥ እኔ ጌታ ነኝ፥ ከእኔ ሌላም የሚያድን የለም። ተናግሬአለሁ፥ አድኛለሁ፥ አሳይቻለሁ፥ በእናንተም ዘንድ ባዕድ አምላክ አልነበረም፤ ስለዚህ እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ፥ ይላል ጌታ። እኔም አምላክ ነኝ፥ ከጥንት ጀምሮ እኔ ነኝ ከእጄም የሚያመልጥ የለም፤ እሠራለሁ፥ የሚከለክልስ ማን ነው? የእስራኤል ቅዱስ፥ የሚቤዣችሁ፥ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ስለ እናንተ ወደ ባቢሎን ሰድጃለሁ፥ ከላዳውያንንም ሁሉ ስደተኞች አድርጌ በሚመኩባቸው መርከቦች አዋርዳቸዋለሁ። ቅዱሳችሁ፥ የእስራኤል ፈጣሪ፥ ንጉሣችሁ፥ ጌታ እኔ ነኝ። ጌታ እንዲህ ይላል፥ በባሕር ውስጥ መንገድን በኃይለኛም ውኃ ውስጥ መተላለፊያን ያደርጋል፤ ሠረገላውንና ፈረሱን ሠራዊቱንና አርበኛውን ያወጣል፥ እነርሱ ግን በአንድነት ተኝተዋል፥ አይነሡም፤ ቀርተዋል፥ እንደ ጥዋፍ ኩስታሪም ጠፍተዋል። የፊተኛውን ነገር አታስታውሱ፥ የጥንቱንም ነገር አታስቡ። እነሆ፥ አዲስ ነገርን አደርጋለሁ፤ እርሱም አሁን ይበቅላል፥ ይህን እናንተም አታውቁም? በምድረ በዳም መንገድን በበረሃም ወንዞችን እዘረጋለሁ። የምድረ በዳ አራዊት፤ ቀበሮዎችና ሰጎኖች ያከብሩኛል፤ ለመረጥሁት ሕዝቤ ውሃ ላጠጣ፥ በምድረ በዳ ውሃ፤ በበረሓም ምንጭ እሰጣለሁ። ለራሴ ያበጀሁት ሕዝብ ምስጋናዬን እንዲያውጅ ይህን አደርጋለሁ።