ትንቢተ ኢሳይያስ 42:1-9

ትንቢተ ኢሳይያስ 42:1-9 አማ54

እነሆ ደግፌ የያዝሁት ባሪያዬ፥ ነፍሴ ደስ የተሰኘችበት ምርጤ፥ በእርሱ ላይ መንፈሴን አድርጌአለሁ፥ እርሱም ለአሕዛብ ፍርድን ያወጣል። አይጮኽም ቃሉንም አያነሣም፥ ድምፁንም በሜዳ አያሰማም። የተቀጠቀጠን ሸንበቆ አይሰብርም፥ የሚጤስንም ክር አያጠፋም፥ በእውነት ፍርድን ያወጣል። በምድርም ፍርድን እስኪያደርግ ድረስ ያበራል እንጂ አይጠፋም፥ አሕዛብም በስሙ ይታመናሉ። ሰማያትን የፈጠረ የዘረጋቸውም፥ ምድርንና በውስጥዋ ያለውን ያጸና፥ በእርስዋ ላይ ለሚኖሩ ሕዝብ እስትንፋስን፥ ለሚሄዱባትም መንፈስን የሚሰጥ አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ እግዚአብሔር በጽድቅ ጠርቼሃለህ፥ እጅህንም እይዛለሁ እጠብቅህማለሁ፥ የዕውሩንም ዓይን ትከፍት ዘንድ የተጋዘውንም ከግዞት ቤት በጨለማም የተቀመጡትን ከወህኒ ቤት ታወጣ ዘንድ ለሕዝብ ቃል ኪዳን ለአሕዛብም ብርሃን አድርጌ እሰጥሃለሁ። እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ ስሜ ይህ ነው፥ ክብሬን ለሌላ፥ ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም። እነሆ፥ የቀድሞው ነገር ተፈጸመ፥ አዲስ ነገርንም እናገራለሁ፥ አስቀድሞም ሳይበቅል እርሱን አስታውቃችኋለሁ።