ትንቢተ ኢሳይያስ 36:4-21

ትንቢተ ኢሳይያስ 36:4-21 አማ54

ራፋስቂስም አላቸው፦ ለሕዝቅያስ እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፦ ታላቁ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፦ ይህ የሚትታመንበት መተማመኛ ምንድር ነው? እኔ፦ ለሰልፍ የሆነው ምክርህና ኃይልህ ከንቱ ነገር ነው አልሁ፥ አሁንም በእኔ ላይ ያመፅኸው በማን ተማምነህ ነው? እነሆ፥ በዚህ በተቀጠቀጠ በሸንበቆ በትር በግብጽ ትታመናለህ፥ ሰው ቢመረኰዘው ተሰብሮ በእጁ ይገባል ያቈስለውማል፥ የግብጽ ንጉሥ ፈርኦን ለሚታመኑበት ሁሉ እንዲሁ ነው። አንተም፦ በአምላካችን በእግዚአብሔር እንታመናለን ብትለኝ፥ ሕዝቅያስ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን፦ በዚህ መሠዊያ ፊት ስገዱ ብሎ የኮረብታ መስገጃዎቹንና መሠዊያዎቹን ያስፈረሰ ይህ አይደለምን? አሁን እንግዲህ ከጌታዬ ከአሦር ንጉሥ ጋር ተወራረድ፥ የሚቀመጡባቸውንም ሰዎች ማግኘት ብቻልህ እኔ ሁለት ሺህ ፈረሶች እሰጥሃለሁ። ስለ ሰረገሎችና ስለ ፈረሰኞች በግብጽ ስትታመን፥ ከጌታዬ ባሪያዎች የሚያንሰውን የአንዱን አለቃ ፊት ትቃወም ዘንድ እንዴት ይቻልሃል? አሁንም በውኑ ያለ እግዚአብሔር ይህን አገር አጠፋ ዘንድ ወጥቻለሁን? እግዚአብሔር፦ ወደዚህ አገር ወጥተህ አጥፋው አለኝ። ኤልያቄምና ሳምናስ ዮአስም ራፋስቂስን፦ እኛ እንሰማለንና እባክህ፥ በሶርያ ቋንቋ ለባርያዎችህ ተናገር፥ በቅጥርም ላይ ባለው ሕዝብ ጆሮ በአይሁድ ቋንቋ አትናገረን አሉት። ራፋስቂስ ግን፦ ጌታዬ ይህን ቃል እናገር ዘንድ ወደ አንተና ወደ ጌታህ ልኮኛልን? ከእናንተ ጋር ኵሳቸውን ይበሉ ዘንድ ሽንታቸውንም ይጠጡ ዘንድ በቅጥር ላይ ወደ ተቀመጡ ሰዎች አይደለምን? አላቸው። ራፋስቂስም ቆሞ በታላቅ ድምፅ በአይሁድ ቋንቋ እንዲህ ብሎ ጮኸ፦ የታላቁን የአሦርን ንጉሥ ቃል ስሙ። ንጉሡ እንዲህ ይላል፦ ያድናችሁ ዘንድ አይችልምና ሕዝቅያስ አያታልላችሁ፥ ሕዝቅያስም፦ እግዚአብሔር በእርግጥ ያድነናል ይህችም ከተማ በአሦር ንጉሥ እጅ አትሰጥም ብሎ በእግዚአብሔር እንድትታመኑ አያድርጋችሁ። ሕዝቅያስንም አትስሙ፥ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፦ ከእኔ ጋር ታረቁ ወደ እኔም ውጡ፥ እያንዳንዳችሁም ከወይናችሁና ከበለሳችሁ ብሉ፥ ከጕድጓዳችሁም ውኃ ጠጡ፥ ይህም መጥቼ ምድራችሁን ወደምትመስለው ምድር፥ እህልና የወይን ጠጅ፥ እንጀራና ወይን ወዳለባት ምድር እስካፈልሳችሁ ድረስ ነው። ሕዝቅያስም፦ እግዚአብሔር ያድነናል ብሎ እንዳያታልላችሁ ተጠንቀቁ። በውኑ የአሕዛብ አማልክት አገሮቻቸውን ከአሦር ንጉሥ እጅ አድነዋቸዋልን? የሐማትና የአልፋድ አማልክት ወዴት አሉ? የሴፈርዋይም አማልክት ወዴት አሉ? ሰማርያን ከእጄ አድነዋታልን? እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ከእጄ ያድን ዘንድ ከእነዚህ አገሮች አማልክት ሁሉ አገሩን ከእጄ ያዳነ ማን ነው? እነርሱም ዝም አሉ፥ አንዳችም አልመለሱለትም፥ ንጉሡ እንዳይመልሱለት አዝዞ ነበርና።