ኦሪት ዘፍጥረት 17:1-27

ኦሪት ዘፍጥረት 17:1-27 አማ54

አብራምም የዘጠና ዘጠኝ ዓመት ሰው በሆን ጊዜ እግዚአብሔር ለአብራም ተገለጠለትና፥ እነሆ ኤልሻዳይ ነኝ በፊቴ ተመላለስ፥ ፍጽምም ሁን፤ ቃል ኪዳኔንም በእኔና በአንተ መካከል አደርጋለሁ፥ እጅግም አበዛሃለሁ አለው። አብራምም በግምባሩ ወደቀ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ተናገረው፥ እነሆ፥ ቃል ኪዳኔ ከአንተ ጋር ነው ለብዙ አሕዛብም አባት ትሆናለህ። ከዛሬም ጀምሮ እንግዲህ ስምህ አብራም ተብሎ አይጠራ፥ ነገር ግን ስምህ አብርሃም ይሆናል፤ ለብዙ አሕዛብ አባት አድርጌሃለሁና። እጅግም አበዛሃለሁ፥ ሕዝብም አደርግሃለሁም ነገሥታትም ከአንተ ይወጣሉ። ቃል ኪዳኔንም በእኔና በአንተ መካከል ከአንተም በኍላ ከዘርህ ጋር በትውልዳቸው ለዘላለም ኪፋን አቆማለሁ፥ ለአንተና ለአንተ በኍላ ለዘርህ አምላክ እሆን ዘንድ። በእንግድነት የምትኖርባትን ምድር የከነዓ ምድር ሁሉ ለዘላለም ግዛት ይሆንህ ዘንድ ለአንተና ከአንተ በኍላ ለዘርህ እሰጣለሁ፤ አምላክም እሆናቸዋለሁ። እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው፥ አንተ ደግሞ ቃል ኪዳኔን ትጠብቅለህ፥ አንተ ከአንተም በኍላ ዘርህ በትውልዳቸው። በእኔና በአንተ መካከለ ከአንተም በኍላ በዘርህ መካከል የምትጠብቁት ቃል ኪዳኔን ይህ ነው ከእናንተ ወንድ ሁሉ ይገረዝ። የቍልፈታችሁንም ሥጋ ትገረዛላችሁ፤ በእኔና በእናንተ መካከል ላለውም ቃል ኪዳን ምልክት ይሆንል። የስምንት ቀን ልጅ ይገረዝ፤ በቤት የተወለደ ወይም ከዘራችሁ ያይደለ በብርም ከእንግዳ ሰው የተገዛ፥ ወንድ ሁሉ በትውልዳችሁ ይገርዝ። በቤትህ የተወለደ በብርህም የተገዛ ፈጽሞ ይገረዝ። ቃል ኪዳኔም በሥጋችሁ የዘላለም ቃል ኪዳን ይሆናል። የቍልፈቱን ሥጋ ያልተገረዘ ቆላፍ ሰው ሁሉ ያች ነፍስ ከወገንዋ ተለይታ ትጥፋ ቃል ኪዳኔን አፍርሳለችና። እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው፥ የሚስትህን የሦራን ስም ሦራ ብለህ አትጥራ፥ ስምዋ ሣራ ይሆናል እንጂ። እባርካታለሁ፥ ደግሞም ከእርስዋ ልጅ እሰጥሃለሁ እባርካትማለሁ፥ የአሕዛብም እናት ትሆናለች፤ የአሕዛብ ነገሥታት ከእርስዋ ይወጣሉ። አብርሃምም በግምባሩ ወደቀ፥ ሳቀም፥ በልቡም አለ፥ የመቶ ዓመት ሰው በውኑ ልጅ ይወልዳልን? ዘጠና ዓመት የሆናትም ሣራ ትወልዳለችን? አብርሃምም እግዚአብሔርን፥ እስማኤል በፊትህ ቢኖር በወደድሁ ነበር አለው። እግዚአብሔርም አለ፥ በእውነት ሚስትህ ሣራ ወንድ ልጅን ትወልድልሃለች፥ ስሙንም ይስሐቅ ብልህ ትጠራዋለህ፤ ከእርሱ በኍላ ለዘሩ የዘላለም ቃል ኪዳን እንዲሆን ቃል ኪዳኔን ከእርሱ ጋር አቆማለሁ። ስለ እስማኤልም ሰምቼሃለሁ፤ እነሆ ባርኬዋለሁ፥ ፍሬያምም አደርገዋለሁ፥ እጅግም አበዛዋለሁ፤ አሥራ ሁለት አለቆችንም ይወልዳል፥ ታላቅ ሕዝብም እንዲሆን አደርገዋለሁ። ቃለ ኪዳኔን ግን በሚመጣው ዓመት በዚሁ ጊዜ ሣራ ከምትወልድልህ ከይስሐቅ ጋር አቆማለሁ። ንግግሩንም ከእርሱ ጋር በፈጸም ጊዜ እግዚአብሔር ከአብርሃም ተለይቶ ወጣ። አብርሃምም ልጁን እስማኤልን፥ በቤቱም የተወለዱትን ሁሉ በብሩም የገዛቸውን ሁሉ ከአብርሃም ቤተሰብ ወንዶቹን ሁሉ ወሰደ የቍልፈታቸውንም ሥጋ እግዚአብሔ እንዳለው በዚያው ቀን ገረዘ። አብርሃምም የቍልፈቱን ሥጋ በተገረዘ ጊዜ የዘጠና ዘጠኝ ዓመት ሰው ነበረ፤ ልጅ እስማኤልም የቍልፈቱን ሥጋ በተገረዘ ጊዜ የአሥራ ሦስት ዓመት ልጅ ነበረ። በዚያው ቀን አብርሃም ተገረዘ ልጁ እስማኤልም። በቤት የተወለዱትና በብር ከእንግዶች የተገዙት የቤቱ ሰዎች ሁሉ ከእርሱ ጋር ተገረዙ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}