ከእነርሱም ተለይተን ተነሣን፤ በቀጥታም ሄደን ወደ ቆስ በነገውም ወደ ሩድ ከዚያም ወደ ጳጥራ መጣን፤ ወደ ፊንቄም የሚሻገር መርከብ አግኝተን ገባንና ተነሣን። ቆጵሮስንም ባየናት ጊዜ በስተ ግራችን ተውናት ወደ ሶርያም ሄደን ወደ ጢሮስ ደረስን፥ መርከቡ ሸክሙን በዚያ የሚያራግፍ ነበርና። ደቀ መዛሙርትንም ባገኘን ጊዜ በዚያ ሰባት ቀን ተቀመጥን፤ እነርሱም ጳውሎስን ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ በመንፈስ አሉት። ጊዜውንም በፈጸምን ጊዜ ወጥተን ሄድን፤ ሁላቸውም ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር እስከ ከተማው ውጭ ድረስ ሸኙን፥ በባሕሩም ዳር ተንበርክከን ጸለይን፤ እርስ በርሳችንም ተሰነባብተን ወደ መርከብ ወጣን፥ እነዚያም ወደ ቤታቸው ተመለሱ። እኛም የባሕሩን መንገድ ጨርሰን ከጢሮስ ወደ አካ ደረስን፥ ለወንድሞችም ሰላምታ ሰጥተን ከእነርሱ ዘንድ አንድ ቀን ተቀመጥን። በነገውም ወጥተን ወደ ቂሣርያ መጣን፥ ከሰባቱም አንድ በሚሆን በወንጌላዊው ፊልጶስ ቤት ገብተን በእርሱ ዘንድ ተቀመጥን። ለእርሱም ትንቢት የሚናገሩ አራት ደናግል ሴቶች ልጆች ነበሩት። አያሌ ቀንም ተቀምጠን ሳለን ነቢይ የነበረ አጋቦስ የሚሉት አንድ ሰው ከይሁዳ ወረደ። ወደ እኛም መጣና የጳውሎስን መታጠቂያ ወስዶ የገዛ እጁንና እግሩን አስሮ፦ እንዲሁ መንፈስ ቅዱስ፦ ይህ መታጠቂያ ያለውን ሰው አይሁድ በኢየሩሳሌም እንደዚህ ያስሩታል በአሕዛብም እጅ አሳልፈው ይሰጡታል ይላል አለ። ይህንም በሰማን ጊዜ እኛም በዚያ የሚኖሩትም ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ ለመንነው። ጳውሎስ ግን መልሶ፦ እያለቀሳችሁ ልቤንም እየሰበራችሁ ምን ማድረጋችሁ ነው? እኔ ስለ ጌታ ስለ ኢየሱስ ስም በኢየሩሳሌም ለመሞት እንኳ ተሰናድቼአለሁ እንጂ ለእስራት ብቻ አይደለም አለ። ምክርንም ሊቀበል እምቢ ባለ ጊዜ፦ የጌታ ፈቃድ ይሁን ብለን ዝም አልን።
የሐዋርያት ሥራ 21 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሐዋርያት ሥራ 21:1-14
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች