ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 7:1-11

ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 7:1-11 አማ54

እንዲህም ሆነ፥ ንጉሡ በቤቱ በተቀመጠ ጊዜ እግዚአብሔርም በዙሪያው ካሉት ጠላቶቹ ሁሉ ባሳረፈው ጊዜ፥ ንጉሡ ነቢዩን ናታንን፦ እኔ ከዝግባ በተሠራ ቤት ተቀምጬአለሁ፥ የእግዚአብሔር ታቦት ግን በመጋረጆች ውስጥ እንደ ተቀመጠ እይ አለው። ናታንም ንጉሡን፦ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና ሂድ፥ በልብህም ያለውን ሁሉ አድርግ አለው። በዚያም ሌሊት የእግዚአብሔር ቃል ወደ ናታን መጣ እንዲህም አለው፦ ሂድ፥ ለባሪዬ ለዳዊት ንገረው፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ ምድር ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በድንኳንና በማደሪያ እሄድ ነበር እንጂ በቤት አልተቀመጥሁምና አንተ የምኖርበትን ቤት አትሠራልኝም። ከእስራኤል ልጆች ሁሉ ጋር ባለፍሁበት ስፍራ ሁሉ፦ ስለ ምን ቤትን ከዝግባ እንጨት አልሠራችሁልኝም? ብዬ ሕዝቤን እስራኤልን ይጠብቅ ዘንድ ከእስራኤል ነገድ ላዘዝሁት ለአንዱ በውኑ ተናግሬአለሁን? አሁንም ዳዊትን ባሪያዬን እንዲህ በለው፦ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አንተ መንጋውን ስትከተል በሕዝቤ በእስራኤል ላይ አለቃ ትሆን ዘንድ ከበግ ጥበቃ ወሰድሁህ፥ በሄድህበትም ሁሉ ከአንተ ጋር ነበርሁ፥ ጠላቶችህንም ሁሉ ከፊትህ አጠፋሁ፥ በምድርም ላይ እንዳሉ እንደ ታላላቆቹ ስም ታላቅ ስም አደርግልሃለሁ። ለሕዝቤም ለእስራኤል ስፍራ አደርግለታለሁ፥ እተክለውማለሁ፥ በስፍራውም ይቀመጣል፥ ከዚያም በኋላ አይናወጥም፥ እንደ ቀድሞው ዘመንና በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ፈራጆች እንዳስነሣሁበት ጊዜ ግፈኞች ተመልሰው አያስጨንቁትም፥ ከጠላቶችህም አሳርፍሃለሁ። እግዚአብሔርም ደግሞ፦ ቤት እሠራልሃለሁ ብሎ ይነግርሃል።