ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 19:1-23

ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 19:1-23 አማ54

ኢዮአብም ንጉሡ ስለ አቤሴሎም እንዳለቀሰና ዋይ ዋይ እንዳለ ሰማ። በዚያም ቀን፦ ንጉሡ ስለ ልጁ አዘነ ሲባል ሕዝቡ ሰምቶአልና የዚያ ቀን ድል በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ ወደ ኅዘን ተለወጠ። ሕዝቡም ከሰልፍ የሸሸ ሕዝብ አፍሮ ወደ ኋላው እንዲል በዚያ ቀን ወደ ከተማ ተሰርቆ ገባ። ንጉሡም ፊቱን ሸፈነ፥ ንጉሡም በታላቅ ድምፅ፦ ልጄ አቤሴሎም ሆይ፥ ልጄ አቤሴሎም፥ ልጄ ሆይ እያለ ይጮኽ ነበር። ኢዮአብም ወደ ንጉሡ ወደ ቤት ገብቶ እንዲህ አለ፦ ዛሬ ነፍስህንና የወንዶችና የሴቶች ልጆችህን ነፍስ የሚስቶችህንና የቁባቶችህን ነፍስ ያዳኑትን የባሪያዎችህን ሁሉ ፊት ዛሬ አሳፍረሃል፥ አንተ የሚጠሉህን ትወድዳለህ፦ የሚወድዱህንም ትጠላለህ። መሳፍንትህና ባሪያዎችህን እንዳታስብ ዛሬ ገልጠሃል፥ ዛሬ ሁላችን ሞተን ቢሆን ኖር አቤሴሎምም ድኖ ቢሆን ኖሮ ደስ ያሰኘህ እንደ ነበረ ዛሬ አያለሁ። አሁን እንግዲህ ተነሥተህ ውጣ፥ ለባሪያዎችህም የሚያጽናናቸውን ነገር ተናገራቸው፥ ያልወጣህ እንደ ሆነ ግን አንድ ሰው ከአንተ ጋር በዚህች ሌሊት እንዳይቀር በእግዚአብሔር እምላለሁ፥ ይህም ከብላቴናነትህ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ካገኘህ ክፉ ነገር ሁሉ ይልቅ ታላቅ መከራ ይሆንብሃል። ንጉሡም ተነሥቶ በበሩ ተቀመጠ፥ ሕዝቡም ሁሉ ንጉሡ በበሩ እንደተቀመጠ ሰማ፥ ሕዝቡም ሁሉ ወደ ንጉሡ ፊት መጣ። እስራኤልም እያንዳንዱ ወደ ድንኳኑ ሸሽቶ ነበር። ሕዝቡም ሁሉ በእስራኤል ነገድ ሁሉ ውስጥ፦ ንጉሡ ከጠላቶቻችን እጅ ታድጎናል፥ ከፍልስጥኤማውያንም እጅ አድኖናል፥ አሁንም ስለ አቤሴሎም ከአገር ሸሽቶአል። በላያችን እንዲሆን የቀባነው አቤሴሎም በሰልፍ ሞቶአል፥ አሁንም እንግዲህ ንጉሡን ለመመለስ ስለ ምን ዝም ትላላችሁ? እያለ እርስ በርሱ ይከራከር ነበር። ንጉሡም ዳዊት ለካህናቱ ለሳዶቅና ለአብያታር ልኮ እንዲህ አላቸው፦ ለይሁዳ ሽማግሌዎች እንዲህ ብላችሁ ተናገሩአቸው፦ የእስራኤል ሁሉ ነገር ወደ ንጉሡ ደርሶአልና ንጉሡን ወደ ቤቱ ከመመለስ ስለ ምን ዘገያችሁ? እናንተ ወንድሞቼ፥ የአጥንቴ ፍላጭና የሥጋዬ ቁራጭ ናችሁ፥ እናንተ ንጉሡን ከመመለስ ስለ ምን ዘገያችሁ? ለአሜሳይም፦ አንተ የአጥንቴ ፍላጭና የሥጋዬ ቁራጭ አይደለህምን? በዘመንህም ሁሉ በኢዮአብ ፋንታ በፊቴ የሠራዊት አለቃ ሳትሆን ብትቀር እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ ይህንም ይጨምርብኝ በሉት። የይሁዳንም ሰዎች ሁሉ ልብ እንደ አንድ ሰው ልብ አድርጎ አዘነበለ፥ ወደ ንጉሡም ልከው፦ አንተ ከባሪያዎችህ ሁሉ ጋር ተመለስ አሉት። ንጉሡም ተመልሶ እስከ ዮርዳኖስ ድረስ መጣ። የይሁዳ ሰዎች ንጉሡን ሊቀበሉ ንጉሡንም ዮርዳኖስን ሊያሻግሩ ወደ ጌልገላ መጡ። ከብራቂምም አገር የነበረው ብንያማዊው የጌራ ልጅ ሳሚ ከይሁዳ ሰዎች ጋር ዳዊትን ሊቀበል ፈጥኖ ወረደ። ከእርሱም ጋር ብንያማውያን የሆኑ ሺህ ሰዎች ነበሩ፥ የሳኦልም ቤት ባሪያ ሲባ ከእርሱም ጋር አሥራ አምስቱ ልጆችና ሀያው ባሪያዎች ነበሩ፥ በንጉሡም ፊት ፈጥነው ዮርዳኖስን ተሻገሩ። ታንኳውም የንጉሥን ቤተ ሰብ ያሻግር ዘንድ ንጉሡም ደስ ያሰኘውን ያደርግ ዘንድ ይሸጋገር ነበር። ንጉሡም ዮርዳኖስን ከተሻገረ በኋላ የጌራ ልጅ ሳሚ በፊቱ ተደፋ። ንጉሡንም፦ ጌታዬ ሆይ፥ ኃጢአቴን አትቍጠርብኝ፥ ጌታዬ ንጉሡ፥ ከኢየሩሳሌም በወጣህ ቀነ ባሪያህ የበደልሁህን አታስብብኝ፥ ንጉሡም በልቡ አያኑረው። ባሪያህ በደለኛ እንደ ሆንሁ አውቄአለሁና እነሆ፥ ከዮሴፍ ቤት ሁሉ አስቀድሜ ዛሬ መጣሁ፥ ጌታዬንም ንጉሡን ልቀበል ወረድሁ አለው። የጽሩያ ልጅ አቢሳ ግን፦ ሳሚ እግዚአብሔር የቀባውን ሰድቦአልና ሞት የተገባው አይደለምን? አለ። ዳዊትም፦ እናንተ የጽሩያ ልጆች፥ እኔ ከእናንተ ጋር ምን አለኝ? ዛሬ ስለ ምን ጠላቶች ትሆኑብኛላችሁ? ዛሬስ በእስራኤል ዘንድ ሰው ሊሞት ይገባልን? ዛሬስ በእስራኤል ላይ እንደ ነገሥሁ አላወቅሁምን? አለ። ንጉሡም ሳሚን፦ አትሞትም አለው። ንጉሡም ማለለት።