የአሦርም ንጉሥ ከባቢሎንና ከኩታ ከአዋና ከሐማት ከሴፈርዋይም ሰዎችን አመጣ፤ በእስራኤልም ልጆች ፋንታ በሰማርያ ከተሞች አኖራቸው፤ ሰማርያንም ወረሱአት፤ በከተሞችዋም ተቀመጡ። በዚያም መቀመጥ በጀመሩ ጊዜ እግዚአብሔርን አይፈሩትም ነበር፤ እግዚአብሔርም አንበሶች ሰደደባቸው፤ ይገድሉአቸውም ነበር። ስለዚህም ለአሦር ንጉሥ “ያፈለስኻቸው፥ በሰማርያም ከተሞች ያኖርኻቸው የአገሩን አምላክ ወግ አላወቁም፤ የአገሩን አምላክ ወግ አላወቁምና አንበሶችን ሰድዶባቸዋል፤ እነሆም፥ ገደሉአቸው፤” ብለው ተናገሩት። የአሦርም ንጉሥ “ከዚያ ካመጣችኋቸው ካህናት አንዱን ውሰዱ፤ ሄዶም በዚያ ይቀመጥ፤ የአገሩንም አምላክ ወግ ያስተምራቸው፤ ብሎ አዘዘ። ከሰማርያም ካፈለሱአቸው ካህናት አንዱ መጥቶ በቤቴል ተቀመጠ፤ እግዚአብሔርንም እንዴት እንዲፈሩት ያስተምራቸው ነበር። በየሕዝባቸውም አምላካቸውን አደረጉ፤ ሳምራውያንም በሠሩት በኮረብታው መስገጃዎች ሕዝቡ ሁሉ በሚኖሩበት ከተሞቻቸው አኖሩአቸው። የባቢሎንም ሰዎች ሱኮትበኖትን ሠሩ፤ የኩታም ሰዎች ኤርጌልን ሠሩ፤ የሐማትም ሰዎች አሲማትን ሠሩ፤ አዋውያንም ኤልባዝርንና ተርታቅን ሠሩ፤ የሴፈርዋይም ሰዎችም ለሴፈርዋይም አማልክት ለአድራሜሌክና ለአነሜሌክ ልጆቻቸውን በእሳት ያቃጥሉ ነበር። እግዚአብሔርንም ይፈሩ ነበር፤ ከመካከላቸውም ለኮረብታው መስገጃዎች ካህናት አደረጉ፤ በኮረብታውም መስገጃዎች ይሠዉ ነበር። እግዚአብሔርንም ሲፈሩ ከመካከላቸው እንደ ፈለሱት እንደ አሕዛብ ልማድ አምላካቸውን ያመልኩ ነበር። እስከ ዛሬ ድረስ እንደ ቀደመው ልማድ ያደርጋሉ፤ እግዚአብሔርንም አይፈሩም፤ እግዚአብሔርም እስራኤል ብሎ የጠራውን የያዕቆብን ልጆች እንዳዘዛቸው ሥርዐትና ፍርድ ሕግና ትእዛዝም አያደርጉም። እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፤ እንዲህም ብሎ አዘዛቸው “ሌሎች አማልክትን አትፍሩ፤ አትስገዱላቸው፤ አታምልኩአቸው፤ አትሠዉላቸው፤ ነገር ግን በታላቅ ኀይል በተዘረጋችም ክንድ ከግብጽ ምድር ያወጣችሁን እግዚአብሔርን እርሱን ፍሩ፤ ለእርሱም ስገዱ፤ ለእርሱም ሠዉ፤ የጻፈላችሁንም ሥርዐትና ፍርድ፥ ሕግና ትእዛዝም ለዘላለም ታደርጉ ዘንድ ጠብቁ፤ ሌሎች አማልክትንም አትፍሩ። ከእናንተም ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳን አትርሱ፤ ሌሎች አማልክትንም አትፍሩ። አምላካችሁን እግዚአብሔርን ፍሩ፤ እርሱም ከጠላቶቻችሁ ሁሉ እጅ ያድናችኋል። ነገር ግን እንደ ቀደመው ልማዳቸው አደረጉ እንጂ አልሰሙም። እነዚህም አሕዛብ እግዚአብሔርን ይፈሩ ነበር፤ ደግሞም የተቀረጹ ምስሎቻቸውን ያመልኩ ነበር፤ ልጆቻቸውም የልጅ ልጆቻቸውም አባቶቻቸው እንዳደረጉ እንዲሁ እስከ ዛሬ ድረስ ያደርጋሉ።
ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 17 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 17:24-41
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች