2 ነገሥት 17:24-41

2 ነገሥት 17:24-41 NASV

የአሦርም ንጉሥ ሕዝቡን ከባቢሎን፣ ከኩታ፣ ከአዋና ከሐማት፣ ከሴፈርዋይም ከተሞች አምጥቶ በእስራኤላውያን ቦታ እንዲገቡ በሰማርያ ከተሞች አሰፈራቸው፤ እነርሱም ሰማርያን ወርሰው በከተሞቿ ይኖሩ ጀመር። በዚያ መኖር እንደ ጀመሩም እግዚአብሔርን አይፈሩትም ነበር፤ ስለዚህ እግዚአብሔር አንበሶች ሰደደባቸው፤ ከእነርሱም ጥቂቶቹን ሰብረው ገደሉ። ለአሦርም ንጉሥ፣ “ወደ ሰማርያ ከተሞች ወስደህ ያሰፈርኸው ሕዝብ የዚያ አገር አምላክ የሚፈልገውን አላወቀም፤ ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር ሰብሮ የሚገድል አንበሳ ላከበት” የሚል ወሬ ደረሰው። ከዚያም የአሦር ንጉሥ፣ “ከሰማርያ ማርካችሁ ካመጣችኋቸው ካህናት አንዱን፣ በዚያው እንዲኖር መልሳችሁ ውሰዱትና የአገሩ አምላክ ምን እንደሚፈልግ ሕዝቡን ያስተምር” ሲል አዘዘ። ስለዚህ ከሰማርያ ማርከው ከወሰዷቸው ካህናት አንዱ ወደ ቤቴል ተመልሶ እግዚአብሔርን እንዴት መፍራት እንደሚገባቸው አስተማራቸው። ያም ሆኖ ግን እያንዳንዱ ወገን በየሰፈረበት ከተማ የራሱን አምላክ ሠራ፤ ያንም ቀድሞ የሰማርያ ሕዝብ በኰረብታው ላይ በሠራው ማምለኪያ እየወሰደ አቆመ። ከባቢሎን የመጡት ሱኮት በኖትን፣ ከኩታ የመጡት ኔርጋልን፣ ከሐማት የመጡት አሲማትን ሠሩ፤ አዋውያንም ኤልባዝርንና ተርታቅ የተባሉትን አማልክት ሲሠሩ፣ ከሴፈርዋይም የመጡት ደግሞ አድራሜሌክና አናሜሌክ ለተባሉት አማልክታቸው ልጆቻቸውን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ። እግዚአብሔርን አመለኩ፤ ይሁን እንጂ እያንዳንዱ ወገን የመጣበትን ሕዝብ ልማድ ተከትሎ፣ በየኰረብታው ባሉት ቤተ ጣዖታት የሚያገለግሉትን ካህናት ሾመ። በአንድ በኩል እግዚአብሔርን ሲያመልኩ፣ በሌላ በኩል ግን እንደየአገራቸው ልማድ የየራሳቸውን አማልክት ያመልኩ ነበር። ይህንም ልማዳቸውን እስከ ዛሬ ድረስ አልተዉትም፤ እግዚአብሔርን በአግባቡ አያመልኩም፤ እንዲሁም እስራኤል ብሎ ለጠራው ለያዕቆብ ዘሮች የሰጣቸውን ሥርዐቶችና ደንቦች፣ ሕጎችና ትእዛዞችን አይከተሉም። እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ጋራ ኪዳን ሲገባ እንዲህ ሲል አዝዟቸው ነበር፤ “ሌሎችን አማልክት አትፍሯቸው፤ አትስገዱላቸው፤ አታገልግሏቸው፤ አትሠዉላቸውም፤ መፍራት የሚገባችሁ ግን በታላቅ ኀይልና በተዘረጋች ክንድ ከግብጽ ምድር ያወጣችሁን እግዚአብሔርን ብቻ ነው። ለርሱ ስገዱ፤ ለርሱም መሥዋዕት አቅርቡ። የጻፈላችሁን ሥርዐቶችና ደንቦች፣ ሕጎችና ትእዛዞች ምን ጊዜም ተግታችሁ ጠብቁ። ሌሎች አማልክትን አታምልኩ። ከእናንተ ጋራ የገባሁትን ኪዳን አትርሱ፤ ሌሎች አማልክትም አታምልኩ። ይልቅስ አምላካችሁን እግዚአብሔርን አምልኩ፤ ከጠላቶቻችሁ ሁሉ እጅ የሚታደጋችሁ እርሱ ነውና።” ነገር ግን በቀደመው ልማዳቸው ጸኑ እንጂ አልተመለሱም። እነዚህ ሕዝቦች ምንም እንኳ በአንድ ወገን እግዚአብሔርን ቢያመልኩትም፣ የተቀረጹ ምስሎቻቸውንም ያገለግሉ ነበር። ልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸውም አባቶቻቸው ያደረጉትን ዛሬም እንደ ቀጠሉበት ነው።