ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 4:1-22

ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 4:1-22 አማ54

ደግሞም ርዝመቱ ሃያ ክንድ፥ ወርዱም ሃያ ክንድ፥ ቁመቱም ዐሥር ክንድ የነበረውን የናሱን መሠዊያ ሠራ። ከፈሰሰም ናስ ከዳር እስከ ዳር ዐሥር ክንድ፥ ቁመቱም አምስት ክንድ፥ በዙሪያውም ሠላሳ ክንድ የሆነ ክብ ኵሬ ሠራ። በበታቹም ለአንድ ክንድ ዐሥር፥ ለአንድም ክንድ አሥር፥ ጕብጕቦች አዞረበት፤ ኵሬውም በቀለጠ ጊዜ ጕብጕቦቹ በሁለት ተራ ከእርሱ ጋር አብረው ቀልጠው ነበር። በዐሥራ ሁለትም በሬዎችም ምስል ላይ ተቀምጦ ነበር፤ ከእነርሱም ሦስቱ ወደ ሰሜን፥ ሦስቱም ወደ ምዕራብ፥ ሦስቱም ወደ ደቡብ፥ ሦስቱም ወደ ምሥራቅ ይመለከቱ ነበር፤ ኵሬውም በላያቸው ነበረ፤ የሁሉም ጀርባቸው በስተ ውስጥ ነበረ። ውፍረቱም አንድ ጋት ያህል ነበረ፤ ከንፈሩም አንድ ጽዋ ከንፈር፥ እንደ ሱፍ አበባ ሆኖ ተሠርቶ ነበር፤ ሦስት ሺህም የባዶስ መሥፈሪያ ይይዝ ነበር። ደግሞም ዐሥር የመታጠቢያ ሰኖች ሠራ፤ ለሚቃጠለውም መሥዋዕት የሚቀርበው ነገር ሁሉ ይታጠብባቸው ዘንድ አምስቱን በቀኝ፥ አምስቱንም በግራ አኖራቸው፤ ኵሬው ግን ካህናት ይታጠቡበት ነበር። ዐሥሩንም መቅረዞች እንደ ሥርዓታቸው ከወርቅ ሠርቶ አምስቱን በቀኝ፥ አምስቱንም በግራ በመቅደሱ ውስጥ አኖራቸው። ዐሥሩንም ገበታዎች ሠርቶ አምስቱን በቀኝ፥ አምስቱን በግራ በመቅደስ ውስጥ አኖራቸው። አንድ መቶም የወርቅ ድስቶች ሠራ። ደግሞም የካህናቱን አደባባይ፥ ታላቁንም አደባባይ፥ የአደባባዩንም ደጆች ሠራ፤ ደጆቻቸውንም በናስ ለበጠ። ኵሬውንም በቤቱ ቀኝ በአዜብ በኩል አኖረው። ኪራምም ምንቸቶቹንና መጫሪያዎቹን፥ ድስቶቹንም ሠራ። ኪራምም ለንጉሡ ለሰሎሞን በእግዚአብሔር ቤት የሠራውን ሥራ ሁሉ ጨረሰ። ሁለቱን አዕማድ፥ ጽዋዎቹንም፥ በፃምዶቹምም ላይ የነበሩትን ሁለት ጕልላቶች፥ በዓምዶቹም ላይ የነበሩትን የጕልላቶች ሁለቱን ጽዋዎች የሚሸፍኑትን ሁለቱን መርበቦች ሠራ። በዓምዶቹም ላይ የነበሩትን ሁለቱን ጕልላቶች ይሸፍኑ ዘንድ፥ ለእያንዳንዱ መረበብ ሁለት ሁለት ተራ ሮማኖች፥ ለሁለቱ መርበቦች አራት መቶ ሮማኖች አደረገ። መቀመጫዎቹንና በመቀመጫዎቹ ላይ የሚቀመጡትን የመታጠቢያ ሰኖች፥ አንዱንም ኵሬ፥ በበታቹም የሚሆኑትን ዐሥራ ሁለት በሬዎች ሠራ። ምንቸቶቹንም መጫሪያዎቹንም ሜንጦዎቹንም ዕቃቸውንም ሁሉ ኪራም ለንጉሡ ለሰሎሞን ስለ እግዚአብሔር ቤት ከለስላሳ ናስ ሠራ። ንጉሡም በዮርዳኖስ ሜዳ በሱኮትና በጽሬዳ መካከል ባለው በወፍራሙ መሬት ውስጥ አስፈሰሰው። ሰሎሞንም እነዚህን ዕቃዎች ሁሉ እጅግ አብዝቶ ሠራ፤ የናሱም ሚዛን አይቈጠርም ነበር። ሰሎሞንም በእግዚአብሔር ቤት የነበረውን ዕቃ ሁሉ፥ የወርቁንም መሠዊያ፥ የገጹንም ኅብስት የነበረባቸውን ገበታዎች፥ በቅድስተ ቅዱሳንም ፊት እንደ ሥርዓታቸው ያበሩ ዘንድ መቅረዞችንና ቀንዲሎቻቸውን ከጥሩ ወርቅ ሠራ። አበባዎቹንና ቀንዲሎቹን መኮስተሪያዎቹንም ከጥሩ ወርቅ ሠራ። ጕጠቶቹንም ድስቶቹንም ጭልፋዎቹንም ማንደጃዎቹንም ከጥሩ ወርቅ ሠራ። የውስጠኛውም ቤት የቅድስተ ቅዱሳን ደጆች የቤተ መቅደሱም ደጆች የወርቅ ነበሩ።