አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 14:1-23

አንደኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 14:1-23 አማ54

አንድ ቀንም እንዲህ ሆነ፥ የሳኦል ልጅ ዮናታን ጋሻ ጃግሬውን፦ ና፥ በዚያ በኩል ወዳለው ወደ ፍልስጥኤማውያን ጭፍራ እንለፍ አለው፥ ለአባቱም አልነገረውም። ሳኦልም በመጌዶን ባለው በሮማኑ ዛፍ በታች በጊብዓ ዳርቻ ተቀምጦ ነበር፥ ከእርሱም ጋር የነበረው ሕዝብ ስድስት መቶ የሚያህል ሰው ነበረ። የኢካቦድ ወንድም የአኪጦብ ልጅ የፊንሐስ ልጅ የዔሊ ልጅ በሴሎ ለእግዚአብሔር ካህን የሆነ ኤፉድም የለበሰ አኪያ አብሮ ነበር፥ ሕዝቡ ዮናታን እንደ ሄደ አላወቁም። ዮናታንም ወደ ፍልስጥኤማውያን ጭፍራ ሊሻገርበት በወደደው መተላለፊያ መካከል በወዲህ አንድ ሾጣጣ በወዲህ አንድ ሾጣጣ ድንጋዮች ነበሩ፥ የአንዱም ስም ቦጼጽ የሁለተኛውም ስም ሴኔ ነበረ። አንዱም ሾጣጣ በማክማስ አንጻር በሰሜን በኩል፥ ሁለተኛውም በጊብዓ አንጻር በደቡብ በኩል የቆሙ ነበሩ። ዮናታንም ጋሻ ጃግሬውን፦ ና፥ ወደ እነዚህ ቆላፋን ጭፍራ እንለፍ፥ በብዙ ወይም በጥቂቱ ማዳን እግዚአብሔርን አያስቸግረውምና ምናልባት እግዚአብሔር ይሠራልን ይሆናል አለው። ጋሻ ጃግሬውም፦ ልብህ ያሰኘህን ሁሉ አድርግ፥ እነሆ፥ ከአንተ ጋር ነኝ፥ እንደ አንተ ልብ ሁሉ የእኔም ልብ እንዲሁ ነው አለው። ዮናታንም አለ፦ እነሆ፥ ወደ ሰዎቹ እናልፋለን እንገለጥላቸውማለን፥ እነርሱም፦ ወደ እናንተ እስክንመጣ ድረስ ቆዩ ቢሉን በስፍራችን እንቆማለን፥ ወደ እነርሱም አንወጣም። ነገር ግን፦ ወደ እኛ ውጡ ቢሉን እግዚአብሔር በእጃችን አሳልፎ ሰጥቶአቸዋልና እንወጣለን፥ ምልክታችንም ይህ ይሆናል። ሁለታቸውም ለፍልስጥኤማውያን ጭፍራ ተገለጡ፥ ፍልስጥኤማውያንም፦ እነሆ፥ ዕብራውያን ከተሸሸጉበት ጉድጓድ ይወጣሉ አሉ። የጭፍራው ሰዎችም ዮናታንንና ጋሻ ጃግሬውን፦ ወደ እኛ ውጡ፥ አንድ ነገርም እናሳያችኋለን አሉ። ዮናታንም ጋሻ ጃግሬውን፦ እግዚአብሔር በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጥቶአቸዋልና ተከተለኝ አለው። ዮናታንም በእጁና በእግሩ ወጣ፥ ጋሻ ጃግሬውም ተከተለው፥ ፍልስጥኤማውያንም በዮናታን እጅ ወደቁ፥ ጋሻ ጃግሬውም ተከትሎ ገደላቸው። የዮናታንና የጋሻ ጃግሬውም የመጀመሪያ ግዳያቸው በአንድ ትልም እርሻ መካከል ሀያ ያህል ሰው ነበረ። በሰፈሩም በእርሻውና በሕዝቡም ሁሉ መካከል ሽብር ነበረ፥ በሰፈሩ የተቀመጡና ለምርኮ የወጡት ተሸበሩ፥ ምድሪቱም ተናወጠች፥ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ታላቅ ሽብር ሆነ። በብንያም ጊብዓ ያሉ የሳኦል ዘበኞችም ተመለከቱ፥ እነሆም፥ ሠራዊቱ ወዲህና ወዲያ እየተራወጡ ተበታተኑ። ሳኦልም ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሕዝብ፦ እስኪ ተቋጠሩ፥ ከእኛ ዘንድ የሄደ ማን እንደሆነ ተመልከቱ አላቸው። በተቋጠሩም ጊዜ እነሆ፥ ዮናታንና ጋሻ ጃግሬው በዚያ አልነበሩም። በዚያም ቀን አኪያ በእስራኤል ልጆች ፊት ኤፉድ ለብሶ ነበርና ሳኦል፦ ኤፉድን አምጣ አለው። ሳኦል ከካህኑ ጋር ሲነጋገር በፍልስጥኤማውያን ሰፈር ግርግርታ እየበዛና እየጠነከረ ሄደ፥ ሳኦልም ካህኑን፦ እጅህን መልስ አለው። ሳኦልና ከእርሱም ጋር የነበሩት ሕዝብ ሁሉ ተሰብስበው ወደ ውጊያው መጡ፥ እነሆም፥ የእያንዳንዱ ሰው ሰይፍ በባልንጀራው ላይ ነበረ፥ እጅግም ታላቅ ድንጋጤ ሆነ። ቀድሞ ከፍልስጥኤማውያን ጋር የነበሩት ከእነርሱም ጋር ከሰፈሩ ዙሪያ የወጡት ዕብራውያን ደግሞ ከሳኦልና ከዮናታን ጋር ወደ ነበሩት እስራኤላውያን ለመሆን ዞሩ። ከእስራኤልም ሰዎች በተራራማው በኤፍሬም አገር የተሸሸጉት ሁሉ ፍልስጥኤማውያን እንደ ኮበለሉ በሰሙ ጊዜ እነርሱ ደግሞ ሊዋጉአቸው ተከትለው ገሠገሡ። እግዚአብሔርም በዚያ ቀን እስራኤልን አዳን፥ ውጊያውም በቤትአዌን በኩል አለፈ። ከሳኦልም ጋር የነበሩ ሕዝብ ሁሉ አሥር ሺህ የሚያህሉ ሰዎች ነበሩ፥ ውጊያውም በተራራማው በኤፍሬም አገር ሁሉ ተበታትኖ ነበር።