1 ሳሙኤል 14:1-23
1 ሳሙኤል 14:1-23 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በነጋም ጊዜ፥ የሳኦል ልጅ ዮናታን ጋሻ ጃግሬውን፥ “ና፤ በዚያ በኩል ወዳለው ወደ ፍልስጥኤማውያን ሰፈር እንለፍ” አለው፤ ለአባቱም አልነገረውም። ሳኦልም በመጌዶን ባለው በሮማኑ ዛፍ በታች በኮረብታው ላይ ተቀምጦ ነበር፤ ከእርሱም ጋር የነበረው ሕዝብ ስድስት መቶ የሚያህል ሰው ነበረ። የዔሊ ልጅ፥ የፊንሐስ ልጅ፥ የዮካብድ ወንድም፥ የአኪጦብ ልጅ በሴሎ ለእግዚአብሔር ካህን የሆነ፥ ኤፉድም የለበሰ አኪያ አብሮ ነበር፤ ሕዝቡም ዮናታን እንደ ሄደ አላወቁም ነበር። ዮናታንም ወደ ፍልስጥኤማውያን ሰፈር ሊሻገርበት በወደደው መተላለፊያ መካከል በወዲህ አንድ ሾጣጣ፥ በወዲህም አንድ ሾጣጣ ድንጋዮች ነበሩ፤ የአንዱም ስም ባዚስ፥ የሁለተኛውም ስም ሴና ነበረ። አንደኛዋ መንገድ በማኪማስ አንጻር በመስዕ በኩል የምትመጣ ናት፤ ሁለተኛዋም መንገድ በገባዖን አንጻር በአዜብ በኩል የምትመጣ ነበረች። ዮናታንም ጋሻ ጃግሬውን፥ “ና፥ ወደ እነዚህ ቈላፋን ሰፈር እንለፍ፤ በብዙ ወይም በጥቂት ማዳን እግዚአብሔርን አያስቸግረውምና ምናልባት እግዚአብሔር ይረዳን ይሆናል” አለው። ጋሻ ጃግሬውም፥ “ልብህ ያሰኘህን ሁሉ አድርግ እነሆ፥ ከአንተ ጋር ነኝ፤ እንደ አንተ ልብ የእኔም ልብ እንዲሁ ነው” አለው። ዮናታንም አለው፥ “እነሆ፥ ወደ ሰዎቹ እናልፋለን፤ ወደ እነርሱም እንቀርባለን፤ እነርሱም፦ እስክንነግራችሁ ድረስ ርቃችሁ ቈዩ ቢሉን ርቀን እንቆማለን፤ ወደ እነርሱም አንወጣም። ነገር ግን ወደ እኛ ውጡ ቢሉን እግዚአብሔር በእጃችን አሳልፎ ሰጥቶአቸዋልና እንወጣለን፤ ምልክታችንም ይህ ይሆናል።” ሁለታቸውም ወደ ፍልስጥኤማውያን ሰፈር ገቡ፤ ፍልስጥኤማውያንም “እነሆ፥ ዕብራውያን ከተሸሸጉበት ጕድጓድ ይወጣሉ” አሉ። የሰፈሩም ሰዎች፦ ዮናታንንና ጋሻ ጃግሬውን “ወደ እኛ ውጡ፤ አንድ ነገርንም እንነግራችኋለን” አሉ። ዮናታንም ጋሻ ጃግሬውን “እግዚአብሔር በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጥቶአቸዋልና ተከተለኝ” አለው። ዮናታንም በእጁና በእግሩ ወጣ፤ ጋሻ ጃግሬውም ከእርሱ ጋር ነበረ፤ ዮናታንም ፊቱን መልሶ ገደላቸው፤ ጋሻ ጃግሬውም ተከትሎ ገደላቸው። የዮናታንና የጋሻ ጃግሬውም በወንጭፍና በዱላ የመጀመሪያ ግድያቸው በአንድ ትልም እርሻ መካከል ሃያ ያህል ሰው ነበረ። በሰፈሩና በእርሻውም ድንጋጤ ሆነ፤ በሰፈሩ የተቀመጡ ሕዝብና የሚዋጉትም ሁሉ ተሸበሩ፤ መዋጋትም አልቻሉም፤ ምድሪቱም ተናወጠች፤ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ታላቅ ድንጋጤ መጣ። በብንያም ገባዖን ያሉ የሳኦል ዘበኞችም ተመለከቱ፤ እነሆም፥ ሠራዊቱ ወዲህና ወዲያ እየተራወጡ ተበታተኑ። ሳኦልም ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሕዝብ፥ “እስኪ ተቋጠሩ፤ ከእኛ ዘንድ የሄደ ማን እንደ ሆነ ተመልከቱ” አላቸው። በተቋጠሩም ጊዜ እነሆ፥ ዮናታንና ጋሻ ጃግሬው በዚያ አልተገኙም። በዚያም ቀን አኪያ በእስራኤል ልጆች ፊት ኤፉድ ይለብስ ነበርና ሳኦል፥ “ኤፉድን አምጣ” አለው። ሳኦልም ከካህኑ ጋር ሲነጋገር በፍልስጥኤማውያን መንደር ግርግርታ እየበዛ ሄደ፤ ሳኦልም ካህኑን፥ “እጅህን መልስ” አለው። ሳኦልና ከእርሱም ጋር የነበሩት ሕዝብ ሁሉ ተሰብስበው ወደ ውጊያው መጡ፤ እነሆም፥ የእያንዳንዱ ሰው ሰይፍ በባልንጀራው ላይ ነበረ፤ እጅግም ታላቅ ሽብር ሆነ። ቀድሞ ከፍልስጥኤማውያን ጋር የነበሩና ወደ ሠራዊቱ የወጡ አገልጋዮችም ከሳኦልና ከዮናታን ጋር ወደ ነበሩ እስራኤላውያን ለመሆን ተመለሱ። በተራራማውም በኤፍሬም ሀገር የተሸሸጉት እስራኤል ሁሉ ፍልስጥኤማውያን እንደ ሸሹ በሰሙ ጊዜ እነርሱ ደግሞ ሊዋጉአቸው ተከተሉአቸው። እግዚአብሔርም በዚያ ቀን እስራኤልን አዳነ፤ ውጊያውም በባሞት በኩል አለፈ። ከሳኦልም ጋር የነበሩ ሕዝብ ሁሉ ዐሥር ሺህ የሚያህሉ ሰዎች ነበሩ፤ ውጊያውም በተራራማው በኤፍሬም ከተማ ሁሉ ተበታትኖ ነበር።
1 ሳሙኤል 14:1-23 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አንድ ቀን የሳኦል ልጅ ዮናታን ወጣት ጋሻ ጃግሬውን፣ “ና በሌላ በኩል ወዳለው የፍልስጥኤማውያን ጦር ሰፈር እንሻገር” አለው። ይህን ግን ለአባቱ አልነገረውም ነበር። ሳኦልም በጊብዓ ዳርቻ ሚግሮን በተባለ ስፍራ ከአንድ የሮማን ዛፍ ሥር ሰፍሮ ነበር፤ ስድስት መቶ ያህል ሰዎችም ዐብረውት ነበሩ፤ ኤፉድ ይለብስ የነበረውም አኪያ በመካከላቸው ነበር። እርሱም በሴሎ የእግዚአብሔር ካህን የነበረው የዔሊ ልጅ፣ የፊንሐስ ልጅ የኢካቦድ ወንድም የአኪጦብ ልጅ ነበር። ዮናታን አለመኖሩን ግን ያወቀ ሰው አልነበረም። ዮናታን ወደ ፍልስጥኤማውያን ጦር ሰፈር ለመሻገር በፈለገበት መተላለፊያ ግራና ቀኝ አንዱ ቦጼጽ ሌላው ሴኔ የተባሉ ሁለት ሾጣጣ ዐለቶች ነበሩ። አንዱ ዐለት በስተሰሜን በኩል በማክማስ አንጻር፣ ሌላው ደግሞ በስተ ደቡብ በኩል በጌባዕ አንጻር ይገኝ ነበር። ዮናታን ወጣት ጋሻ ጃግሬውን፣ “ና፤ ወደነዚያ ሸለፈታሞች ጦር ሰፈር እንሻገር፤ ምናልባትም እግዚአብሔር ይዋጋልን ይሆናል፤ በብዙም ሆነ በጥቂት ለማዳን እግዚአብሔርን የሚያግደው የለምና” አለው። ወጣቱም ጋሻ ጃግሬ፣ “በልብህ ያሰብኸውን ሁሉ አድርግ፤ ወደ ኋላም አትበል፤ እኔም በሙሉ ልብ ካንተው ጋራ ነኝ” አለው። ዮናታንም እንዲህ አለው፣ “እንግዲያውስ ና፤ ወደ ሰዎቹ እንሻገርና እንታያቸው። እነርሱም፣ ‘ወደ እናንተ እስክንመጣ እዚያው ጠብቁን’ ካሉን፣ ባለንበት ሆነን እንጠብቃቸዋለን፤ ወደ እነርሱም አንወጣም። ነገር ግን፣ ‘ወደ እኛ ውጡ’ ካሉን፣ እግዚአብሔር እነርሱን በእጃችን አሳልፎ የሰጠን ለመሆኑ ምልክቱ ይህ ስለ ሆነ፣ ወደ እነርሱ እንወጣለን።” ሁለቱም ለፍልስጥኤማውያን ጭፍራ በታዩ ጊዜ፣ ፍልስጥኤማውያን፣ “እነሆ፤ ዕብራውያን ከተደበቁባቸው ጕድጓዶች እየወጡ ነው” አሉ። የፍልስጥኤም ጦር ሰፈር ሰዎችም፣ “ኑ ወደ እኛ ውጡ፤ አንድ ነገር እናሳያችሁ” ሲሉ በዮናታንና በጋሻ ጃግሬው ላይ ጮኹባቸው። ስለዚህ ዮናታን ጋሻ ጃግሬውን፣ “ተከትለኸኝ ውጣ፤ እግዚአብሔር በእስራኤላውያን እጅ አሳልፎ ሰጥቷቸዋልና” አለው። ዮናታን በእጁና በእግሩ ተፍጨርጭሮ፣ ጋሻ ጃግሬውን በማስከተል ወጣ። ፍልስጥኤማውያንም በዮናታን እጅ ወደቁ፤ ጋሻ ጃግሬውም ከበስተኋላው እየተከተለ ገደላቸው። ዮናታንና ጋሻ ጃግሬው በመጀመሪያው ቀን ባደረጉት ግዳይ አንድ ጥማድ በምታውል የዕርሻ ቦታ ላይ ሃያ ያህል ሰዎች ገደሉ። በሰፈር በዕርሻ ላይና በሕዝብ ሁሉ መካከል ሽብር ሆነ፤ ከተማ ጠባቂዎችና አደጋ ጣዮችም ሁሉ ተንቀጠቀጡ፤ ምድሪቱም ተናወጠች፤ ሽብሩም ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከ ነበር። በብንያም ግዛት በጊብዓ የነበሩ የሳኦል ዘቦች፣ የፍልስጥኤም ሰራዊት በየአቅጣጫው መበታተኑን አዩ። ሳኦልም ዐብረውት የነበሩትን ሰዎች፣ “እስኪ፣ ሰራዊቱን ቍጠሩና ማን ከዚህ እንደ ሄደ እዩ” አላቸው። ይህን ባደረጉ ጊዜም ዮናታንና ጋሻ ጃግሬው በዚያ አልነበሩም። ሳኦልም አኪያን፣ “የእግዚአብሔርን ታቦት ወደዚህ አምጣ” አለው፤ በዚያ ጊዜ ታቦቱ በእስራኤላውያን ዘንድ ነበር። ሳኦል ለካህኑ በመናገር ላይ ሳለ፣ በፍልስጥኤማውያን ሰፈር ሁካታው እየጨመረ ሄደ። ስለዚህ ሳኦል ካህኑን፣ “እጅህን መልስ” አለው። ከዚያም ሳኦልና ሰዎቹ ተሰብስበው ወደ ውጊያው ሄዱ። እነርሱም ፍልስጥኤማውያን በሰይፋቸው እየተጨፋጨፉ በታላቅ ትርምስ ላይ ሆነው አገኟቸው። እነዚያ ቀድሞ ከፍልስጥኤማውያን ጐን ተሰልፈው የነበሩትና ዐብረዋቸውም ወደ ሰፈራቸው የወጡት ዕብራውያን ከሳኦልና ከዮናታን ጋራ ወደ ነበሩት እስራኤላውያን ገቡ። በኰረብታማው የኤፍሬም አገር ተሸሽገው የነበሩት እስራኤላውያን ሁሉ ፍልስጥኤማውያኑ በሽሽት ላይ መሆናቸውን በሰሙ ጊዜ፣ አጥብቀው በመከታተል አሳደዷቸው። በዚያ ቀን እግዚአብሔር እስራኤልን ታደገው፤ ጦርነቱም ከቤትአዌን ዘልቆ ሄደ።
1 ሳሙኤል 14:1-23 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
አንድ ቀንም እንዲህ ሆነ፥ የሳኦል ልጅ ዮናታን ጋሻ ጃግሬውን፦ ና፥ በዚያ በኩል ወዳለው ወደ ፍልስጥኤማውያን ጭፍራ እንለፍ አለው፥ ለአባቱም አልነገረውም። ሳኦልም በመጌዶን ባለው በሮማኑ ዛፍ በታች በጊብዓ ዳርቻ ተቀምጦ ነበር፥ ከእርሱም ጋር የነበረው ሕዝብ ስድስት መቶ የሚያህል ሰው ነበረ። የኢካቦድ ወንድም የአኪጦብ ልጅ የፊንሐስ ልጅ የዔሊ ልጅ በሴሎ ለእግዚአብሔር ካህን የሆነ ኤፉድም የለበሰ አኪያ አብሮ ነበር፥ ሕዝቡ ዮናታን እንደ ሄደ አላወቁም። ዮናታንም ወደ ፍልስጥኤማውያን ጭፍራ ሊሻገርበት በወደደው መተላለፊያ መካከል በወዲህ አንድ ሾጣጣ በወዲህ አንድ ሾጣጣ ድንጋዮች ነበሩ፥ የአንዱም ስም ቦጼጽ የሁለተኛውም ስም ሴኔ ነበረ። አንዱም ሾጣጣ በማክማስ አንጻር በሰሜን በኩል፥ ሁለተኛውም በጊብዓ አንጻር በደቡብ በኩል የቆሙ ነበሩ። ዮናታንም ጋሻ ጃግሬውን፦ ና፥ ወደ እነዚህ ቆላፋን ጭፍራ እንለፍ፥ በብዙ ወይም በጥቂቱ ማዳን እግዚአብሔርን አያስቸግረውምና ምናልባት እግዚአብሔር ይሠራልን ይሆናል አለው። ጋሻ ጃግሬውም፦ ልብህ ያሰኘህን ሁሉ አድርግ፥ እነሆ፥ ከአንተ ጋር ነኝ፥ እንደ አንተ ልብ ሁሉ የእኔም ልብ እንዲሁ ነው አለው። ዮናታንም አለ፦ እነሆ፥ ወደ ሰዎቹ እናልፋለን እንገለጥላቸውማለን፥ እነርሱም፦ ወደ እናንተ እስክንመጣ ድረስ ቆዩ ቢሉን በስፍራችን እንቆማለን፥ ወደ እነርሱም አንወጣም። ነገር ግን፦ ወደ እኛ ውጡ ቢሉን እግዚአብሔር በእጃችን አሳልፎ ሰጥቶአቸዋልና እንወጣለን፥ ምልክታችንም ይህ ይሆናል። ሁለታቸውም ለፍልስጥኤማውያን ጭፍራ ተገለጡ፥ ፍልስጥኤማውያንም፦ እነሆ፥ ዕብራውያን ከተሸሸጉበት ጉድጓድ ይወጣሉ አሉ። የጭፍራው ሰዎችም ዮናታንንና ጋሻ ጃግሬውን፦ ወደ እኛ ውጡ፥ አንድ ነገርም እናሳያችኋለን አሉ። ዮናታንም ጋሻ ጃግሬውን፦ እግዚአብሔር በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጥቶአቸዋልና ተከተለኝ አለው። ዮናታንም በእጁና በእግሩ ወጣ፥ ጋሻ ጃግሬውም ተከተለው፥ ፍልስጥኤማውያንም በዮናታን እጅ ወደቁ፥ ጋሻ ጃግሬውም ተከትሎ ገደላቸው። የዮናታንና የጋሻ ጃግሬውም የመጀመሪያ ግዳያቸው በአንድ ትልም እርሻ መካከል ሀያ ያህል ሰው ነበረ። በሰፈሩም በእርሻውና በሕዝቡም ሁሉ መካከል ሽብር ነበረ፥ በሰፈሩ የተቀመጡና ለምርኮ የወጡት ተሸበሩ፥ ምድሪቱም ተናወጠች፥ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ታላቅ ሽብር ሆነ። በብንያም ጊብዓ ያሉ የሳኦል ዘበኞችም ተመለከቱ፥ እነሆም፥ ሠራዊቱ ወዲህና ወዲያ እየተራወጡ ተበታተኑ። ሳኦልም ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሕዝብ፦ እስኪ ተቋጠሩ፥ ከእኛ ዘንድ የሄደ ማን እንደሆነ ተመልከቱ አላቸው። በተቋጠሩም ጊዜ እነሆ፥ ዮናታንና ጋሻ ጃግሬው በዚያ አልነበሩም። በዚያም ቀን አኪያ በእስራኤል ልጆች ፊት ኤፉድ ለብሶ ነበርና ሳኦል፦ ኤፉድን አምጣ አለው። ሳኦል ከካህኑ ጋር ሲነጋገር በፍልስጥኤማውያን ሰፈር ግርግርታ እየበዛና እየጠነከረ ሄደ፥ ሳኦልም ካህኑን፦ እጅህን መልስ አለው። ሳኦልና ከእርሱም ጋር የነበሩት ሕዝብ ሁሉ ተሰብስበው ወደ ውጊያው መጡ፥ እነሆም፥ የእያንዳንዱ ሰው ሰይፍ በባልንጀራው ላይ ነበረ፥ እጅግም ታላቅ ድንጋጤ ሆነ። ቀድሞ ከፍልስጥኤማውያን ጋር የነበሩት ከእነርሱም ጋር ከሰፈሩ ዙሪያ የወጡት ዕብራውያን ደግሞ ከሳኦልና ከዮናታን ጋር ወደ ነበሩት እስራኤላውያን ለመሆን ዞሩ። ከእስራኤልም ሰዎች በተራራማው በኤፍሬም አገር የተሸሸጉት ሁሉ ፍልስጥኤማውያን እንደ ኮበለሉ በሰሙ ጊዜ እነርሱ ደግሞ ሊዋጉአቸው ተከትለው ገሠገሡ። እግዚአብሔርም በዚያ ቀን እስራኤልን አዳን፥ ውጊያውም በቤትአዌን በኩል አለፈ። ከሳኦልም ጋር የነበሩ ሕዝብ ሁሉ አሥር ሺህ የሚያህሉ ሰዎች ነበሩ፥ ውጊያውም በተራራማው በኤፍሬም አገር ሁሉ ተበታትኖ ነበር።
1 ሳሙኤል 14:1-23 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አንድ ቀን የሳኦል ልጅ ዮናታን የጦር መሣሪያ የሚሸከምለትን ወጣት ጋሻ ጃግሬውን “ወደ ፍልስጥኤማውያን የጦር ሰፈር እንሻገር” አለው። ነገር ግን ዮናታን ይህን ጉዳይ ለአባቱ እንኳ አልነገረውም፤ በዚህ ጊዜ ሳኦል ከጊብዓ በጣም ሳይርቅ በሚግሮን በአንድ የሮማን ዛፍ ሥር ሰፍሮ ነበር፤ ከእርሱም ጋር ስድስት መቶ ያኽል ጭፍሮች ነበሩ፤ በሴሎ የእግዚአብሔር ካህን የነበረው የዔሊ ልጅ ካህኑ ፊንሐስ የወለደው የኢካቦድ ወንድም የአሒጡብ ልጅ አኪያ ኤፉድ ለብሶ ከእርሱ ጋር አብሮ ነበር። እነርሱም ዮናታን ወዴት እንደ ሄደ አላወቁም ነበር። ዮናታን ወደ ፍልስጥኤማውያን ሰፈር ለመድረስ በሚክማስ መተላለፊያ መውጣት ነበረበት፤ በመተላለፊያውም ከግራና ከቀኝ ሁለት ሾጣጣ አለቶች ሲኖሩ የአንደኛው አለት ስም ቦጼጽ፥ የሁለተኛውም ስም ሴኔ ተብሎ ይጠራል፤ ከአለቶቹም አንዱ ከመተላለፊያው በስተ ሰሜን በኩል በሚክማስ ፊት ለፊት የሚገኘው ሲሆን፥ ሁለተኛውም በስተደቡብ በኩል በጌባዕ ፊት ለፊት ይገኝ ነበር። ዮናታን ጋሻ ጃግሬ የሆነውን ወጣት “ና ወደ እነዚያ ወደ አልተገረዙት ወገኖች የጦር ሰፈር እንሻገር እግዚአብሔር ይረዳን ይሆናል፤ በብዙም ሆነ በጥቂት እግዚአብሔር ማዳን አይሳነውም” አለው። ወጣቱም ጋሻጃግሬ “የምትፈቅደውን ነገር ሁሉ አድርግ፤ እኔ ከአንተ አልለይም፤ በሙሉ ልቤም ከአንተ ጋር ነኝ” አለው። ዮናታንም እንዲህ አለው፤ “እሺ እንግዲያውስ ወደ ማዶ እንሻገርና ለፍልስጥኤማውያን ፊት ለፊት እንታያቸው፤ እነርሱም ‘ወደ እናንተ እስክንመጣ ድረስ በዚያ ጠብቁን’ ቢሉን፥ ባለንበት እንቈያለን፤ ነገር ግን ‘ወደ እኛ ኑ’ ቢሉን፥ ወደ እነርሱ እንሄዳለን፤ ይህም እግዚአብሔር በፍልስጥኤማውያን ላይ ድልን የሚያቀዳጀን ለመሆኑ ምልክት ይሆንልናል።” እነርሱም ወጣ ብለው ለፍልስጥኤማውያን ታዩአቸው፤ ፍልስጥኤማውያንም “እነሆ! አንዳንድ ዕብራውያን ከተሸሸጉበት ጒድጓድ በመውጣት ላይ ናቸው!” ተባባሉ፤ ከዚህ በኋላ ፍልስጥኤማውያን ዮናታንንና ጋሻጃግሬውን ጠርተው “የምንነግራችሁ ጉዳይ ስላለን ወደዚህ እኛ ወዳለንበት ኑ!” አሉአቸው። ዮናታንም ጋሻጃግሬውን “እንግዲህ ተከተለኝ፤ እግዚአብሔር በፍልስጥኤማውያን ላይ ድልን ለእስራኤል ይሰጣል” አለው፤ ዮናታንም በእጁና በጒልበቱ እየዳኸ ወደ አፋፉ ወጣ፤ ጋሻጃግሬውም ተከተለው፤ ዮናታንም በፍልስጥኤማውያን ላይ ድንገተኛ አደጋ በመጣል መታቸው፤ ጋሻጃግሬውም ገደላቸው። በመጀመሪያውም ግድያ በአንድ የእርሻ ክልል ላይ ኻያ ያኽል ሰዎችን ገደሉ፤ በገጠር የነበሩ ፍልስጥኤማውያንም ሁሉ ተሸበሩ፤ አደጋ ጣዮችና በሰፈር የነበሩ ወታደሮችም ሁሉ በፍርሃት ተንቀጠቀጡ፤ እግዚአብሔር በላከባቸውም አስጨናቂ ሽብር መሬት ተንቀጠቀጠች። የሳኦል ወታደሮች የብንያም ግዛት በሆነችው በጊብዓ መሽገው ሁኔታውን ሁሉ በመጠባበቅ ላይ ሳሉ በመታወክ የሚሸሹትን ፍልስጥኤማውያን አዩ። ስለዚህም ሳኦል “እስቲ ወታደሮችን ቊጠሩና ከእኛ መካከል የጐደሉ እንዳሉ አረጋግጡ” ብሎ አዘዘ፤ በትእዛዙም መሠረት ሠራዊቱን በቈጠሩ ጊዜ ዮናታንና ጋሻጃግሬው አለመኖራቸው ታወቀ። ሳኦልም ካህኑን አኪያን “ኤፉዱን ይዘህ ና” አለው። በዚያን ቀን ካህኑ አኪያ ኤፉድ ለብሶ በእስራኤል ሕዝብ ፊት ነበር፤ ሳኦል ከካህኑ ጋር በመነጋገር ላይ ሳለ፥ በፍልስጥኤማውያን ሰፈር የተነሣው ሁከትና ሽብር እየባሰበት ሄደ፤ ሳኦልም ካህኑን “እግዚአብሔርን ለመጠየቅ አሁን ጊዜ የለንም” አለው። ከዚህ በኋላ ሳኦልና ወታደሮቹ ካሉበት በመንቀሳቀስ ወደ ውጊያው ሄዱ፦ እዚያም ፍልስጥኤማውያን ግራ በመጋባት እርስ በርሳቸው በሰይፍ ይጋደሉ ነበር። ከፍልስጥኤማውያን ጋር በመተባበር ወደ ጦሩ ሰፈር ሄደው የነበሩ አንዳንድ ዕብራውያንም ፍልስጥኤማውያንን ከድተው ከሳኦልና ከዮናታን ጋር ተባበሩ። በኤፍሬም ኮረብታዎች ተደብቀው የነበሩ ሌሎች እስራኤላውያንም ፍልስጥኤማውያን በሽሽት ላይ መሆናቸውን ሰሙ፤ ስለዚህም ከወገን ጦር ጋር ተባብረው ፍልስጥኤማውያንን ማሳደድ ጀመሩ፤ እስከ ቤትአዌን ከተማ ማዶ ባለው መንገድ ሁሉ ተከታትለው ወጉአቸው፤ እግዚአብሔርም በዚያን ቀን እስራኤልን በመታደግ አዳነ።
1 ሳሙኤል 14:1-23 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አንድ ቀን የሳኦል ልጅ ዮናታን ወጣት ጋሻ ጃግሬውን፥ “ና በሌላ በኩል ወዳለው የፍልስጥኤማውያን ጦር ሰፈር እንሻገር” አለው። ይህን ግን ለአባቱ አልነገረውም ነበር። ሳኦልም በጊብዓ ዳርቻ በሚግሮን ከአንድ የሮማን ዛፍ ሥር ሰፍሮ ነበር፤ ስድስት መቶ ያህል ሰዎችም አብረውት ነበሩ፤ ኤፉድ ይለብስ የነበረውም አኪያ በመካከላቸው ነበር። እርሱም በሴሎ የጌታ ካህን የነበረው የዔሊ ልጅ፥ የፊንሐስ ልጅ የኢካቦድ ወንድም የአኪጦብ ልጅ ነበር። ሕዝቡም ዮናታን አለመኖሩን አላወቁም ነበር። ዮናታን ወደ ፍልስጥኤማውያን ጦር ሰፈር ለመሻገር በፈለገበት መተላለፊያ ግራና ቀኝ ሁለት ሾጣጣ ድንጋዮች ነበሩ፤ የአንዱ ስም ቦጼጽ ሲሆን፥ ሌላው ሴኔ ተብሎ ይጠራል። ከድንጋዮቹም አንዱ ከመተላለፊያው በስተ ሰሜን በኩል በሚክማስ ፊት ለፊት የሚገኘው ሲሆን፥ ሁለተኛውም በስተ ደቡብ በኩል በጌባዕ ፊት ለፊት ይገኝ ነበር። ዮናታን ወጣት ጋሻ ጃግሬውን፥ “ና፤ ወደነዚያ ያልተገረዙ ሰዎች ጦር ሰፈር እንሻገር፤ ምናልባትም ጌታ ይዋጋልን ይሆናል፤ በብዙም ሆነ በጥቂት ለማዳን ጌታን የሚያግደው የለምና” አለው። ወጣቱ ጋሻ ጃግሬም፥ “በልብህ ያሰብኸውን ሁሉ አድርግ፤ ወደ ኋላም አትበል፤ እኔም በሙሉ ልብ ካንተው ጋር ነኝ” አለው። ዮናታንም እንዲህ አለው፥ “እንግዲያውስ ና፤ ወደ ሰዎቹ እንሻገርና እንታያቸው። እነርሱም፥ ‘ወደ እናንተ እስክንመጣ እዚያው ጠብቁን’ ካሉን፥ ስፍራችንን ይዘን እንጠብቃቸዋለን፤ ወደ እነርሱም አንወጣም። ነገር ግን፥ ‘ወደ እኛ ኑ’ ካሉን፥ ጌታ እነርሱን በእጃችን አሳልፎ የሰጠን ለመሆኑ ምልክቱ ይህ ስለሆነ፥ ወደ እነርሱ እንወጣለን።” ሁለቱም ለፍልስጥኤማውያን ሠራዊት በታዩ ጊዜ፥ ፍልስጥኤማውያን፥ “እነሆ፤ ዕብራውያን ከተደበቁባቸው ጉድጓዶች እየወጡ ነው” አሉ። የፍልስጥኤም ጦር ሰፈር ሰዎችም፥ “ኑ ወደ እኛ ውጡ፤ የምናሳያችሁ ነገር ይኖራል” ሲሉ በዮናታንና በጋሻ ጃግሬው ላይ ጮኹባቸው። ስለዚህ ዮናታን ጋሻ ጃግሬውን፥ “ተከትለኸኝ ውጣ፤ ጌታ በእስራኤላውያን እጅ አሳልፎ ሰጥቷቸዋልና” አለው። ዮናታን በእጁና በእግሩ ወደ አፋፉ፥ ጋሻ ጃግሬውን በማስከተል ወጣ። በዮናታንም እጅ ወደቁ፤ ጋሻ ጃግሬውም ከበስተኋላው እየተከተለ ገደላቸው። ዮናታንና ጋሻ ጃግሬው በመጀመሪያው ቀን ባደረጉት ግዳያቸው በአንድ ጥማድ የእርሻ ቦታ ላይ ሃያ ያህል ሰዎች ገደሉ። በሰፈር በእርሻ ላይና በሕዝብ ሁሉ መካከል ሽብር ሆነ፤ ከተማ ጠባቂዎችና አደጋ ጣዮችም ሁሉ ተቀጠቀጡ፤ ምድሪቱም ተናወጠች፤ ሽብሩም ከእግዚአብሔር ዘንድ የተላከ ነበር። በብንያም ግዛት በጊብዓ የነበሩ የሳኦል ጠባቂዎች፥ የፍልስጥኤም ሠራዊት በየአቅጣጫው መበታተኑን አዩ። ሳኦልም አብረውት የነበሩትን ሰዎች፥ “ሠራዊቱን ቁጠሩና ማን ከዚህ እንደ ሄደ ለዩ” አላቸው። በቆጠሩም ጊዜ፥ እነሆ፥ ዮናታንና ጋሻ ጃግሬው በዚያ አልነበሩም። ሳኦልም አኪያን፥ “የእግዚአብሔርን ታቦት ወደዚህ አምጣ” አለው፤ በዚያን ጊዜ የእግዚአብሔር ታቦት በእስራኤላውያን ዘንድ ነበር። ሳኦል ለካህኑ በመናገር ላይ ሳለ፥ በፍልስጥኤማውያን ሰፈር ሁካታው እየጨመረ ሄደ። ስለዚህ ሳኦል ካህኑን፥ “እጅህን መልስ” አለው። ከዚያም ሳኦልና ሰዎቹ ተሰብስበው ወደ ውጊያው ሄዱ። እዚያም ፍልስጥኤማውያን ግራ በመጋባት በታላቅ ትርምስ እርስ በርሳቸው በሰይፍ ይጋደሉ ነበር። እነዚያ ቀድሞ ከፍልስጥኤማውያን ጐን ተሰልፈው የነበሩትና አብረዋቸውም ወደ ሰፈራቸው የወጡት ዕብራውያን ከሳኦልና ከዮናታን ጋር ወደነበሩት እስራኤላውያን ገቡ። በተራራማው የኤፍሬም አገር ተሸሽገው የነበሩት እስራኤላውያን ሁሉ ፍልስጥኤማውያኑ በሽሽት ላይ መሆናቸውን በሰሙ ጊዜ፥ እነርሱም አጥብቀው በመከታተል ሊወጉአቸው አሳደዷቸው። በዚያ ቀን ጌታ እስራኤልን ታደገው፤ ጦርነቱም ከቤትአዌን ዘልቆ ሄደ።