የጢሮስ ንጉሥ ኪራም ለዳዊት በዘመኑ ሁሉ ወዳጁ ስለ ነበረ፥ ሰሎሞን በአባቱ ፋንታ ንጉሥ ለመሆን እንደ ተቀባ ሰምቶ ባሪያዎቹን ወደ ሰሎሞን ሰደደ። ሰሎሞንም ወደ ኪራም እንዲህ ብሎ ላከ “እግዚአብሔር ከእግሩ በታች እስኪጥልለት ድረስ በዙሪያው ስለ ነበረ ሰልፍ አባቴ ዳዊት የአምላኩን የእግዚአብሔርን ቤት መሥራት እንዳልቻለ አንተ ታውቃለህ። አሁንም አምላኬ እግዚአብሔር በዙሪያዬ ካሉት ዕረፍት ሰጥቶኛል፤ ጠላትም ክፉም ነገር የለብኝም። እነሆም፥ እግዚአብሔር ለአባቴ ለዳዊት ‘በአንተ ፋንታ በዙፋንህ ላይ የማስቀምጠው ልጅህ እርሱ ለስሜ ቤት ይሠራል፤’ ብሎ እንደ ነገረው፥ ለአምላኬ ለእግዚአብሔር ስም ቤት እሠራ ዘንድ አስባለሁ። አሁንም ከወገኔ እንደ ሲዶናውያን እንጨት መቍረጥ የሚያውቅ እንደሌለ ታውቃለህና የዝግባ ዛፍ ከሊባኖስ ይቈርጡልኝ ዘንድ ባሪያዎችህን እዘዝ፤ ባሪያዎቼም ከባሪያዎችህ ጋር ይሁኑ፤ የባሪያዎችህንም ዋጋ እንደ ተናገርኸው ሁሉ እሰጥሃለሁ።” ኪራምም የሰሎሞንን ቃል ሰምቶ እጅግ ደስ አለውና “በዚህ በታላቅ ሕዝብ ላይ ጥበበኛ ልጅ ለዳዊት የሰጠ እግዚአብሔር ዛሬ ይመስገን፤” አለ። ኪራምም “የላክህብኝን ሁሉ ሰማሁ፤ ስለ ዝግባውና ስለ ጥዱ እንጨት ፈቃድህን ሁሉ አደርጋለሁ። ባሪያዎቼ ከሊባኖስ ወደ ባሕር ይጐትቱታል፤ እኔም በታንኳ አድርጌ በባሕር ላይ እያንሳፈፍሁ አንተ እስከ ወሰንኸው ስፍራ ድረስ አደርስልሃለሁ፤ በዚያም እፈታዋለሁ፥ አንተም ከዚያ ታስወስደዋለህ፤ አንተም ፈቃዴን ታደርጋለህ፤ ለቤቴም ቀለብ የሚሆነውን ትሰጠኛለህ፤” ብሎ ወደ ሰሎሞን ላከ። እንዲሁም ኪራም የዝግባውንና የጥዱን እንጨት እንደሚሻው ያህል ሁሉ ለሰሎሞን ይሰጠው ነበር። ሰሎሞንም ለኪራም ስለ ቤቱ ቀለብ ሃያ ሺህ የቆሮስ መስፈሪያ ስንዴ ሃያ ኮርም ጥሩ ዘይት ይሰጠው ነበር፤ ሰሎሞንም ለኪራም በየዓመቱ ይህን ይሰጥ ነበር። እግዚአብሔርም እንደ ነገረው ለሰሎሞን ጥበብን ሰጠው፤ በኪራምና በሰሎሞንም መካከል ሰላም ነበረ፤ ሁለቱም ቃል ኪዳን ተጋቡ።
አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 5 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 5:1-12
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች