አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 15:1-24

አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 15:1-24 አማ54

የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት አብያም በይሁዳ ላይ ንጉሥ ሆነ። በኢየሩሳሌምም ሦስት ዓመት ነገሠ፤ እናቱም መዓካ የተባለችው የአቤሴሎም ልጅ ነበረች። ከእርሱ አስቀድሞ ባደረገው በአባቱ ኀጢአት ሁሉ ሄደ፤ ልቡም እንደ አባቱ እንደ ዳዊት ልብ ከአምላኩ ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም አልነበረም። ነገር ግን ልጁን ከእርሱ በኋላ ያስነሣ ዘንድ፥ ኢየሩሳሌምንም ያጸና ዘንድ አምላኩ እግዚአብሔር ስለ ዳዊት በኢየሩሳሌም መብራት ሰጠው፤ ዳዊት በዘመኑ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አድርጎ ነበርና፥ ካዘዘውም ነገር ሁሉ ፈቀቅ አላለም ነበርና። በኢዮርብዓምና በሮብዓም ልጅ በአብያም መካከል በዘመኑ ሁሉ ጠብ ነበረ። የቀረውም የአብያም ነገር፥ ያደርገውም ሁሉ፥ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? በአብያና በኢዮርብዓም መካከል ሰልፍ ነበረ። አብያምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ቀበሩት። ልጁም አሳ በፋንታው ነገሠ። በእስራኤል ንጉሥ በኢዮርብዓም በኻያኛውም ዓመት አሳ በይሁዳ ላይ ነገሠ። በኢየሩሳሌምም አርባ አንድ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም መዓካ የተባለች የአቤሴሎም ልጅ ነበረች። አሳ እንደ አባቱ እንደ ዳዊት በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አደረገ። ከአገሩም ሰዶማውያንን አስወገደ፤ አባቶቹም ያደረጉትን ጣዖታትን ሁሉ አራቀ። በማምለኪያ ዐፀድ ጣዖት ስለሠራች እናቱን መዓካን እቴጌ እንዳትሆን ሻራት፤ ጣዖትዋንም ሰበረው፤ በቄድሮንም ፈፋ አጠገብ አቃጠለው። ነገር ግን በኮረብቶች ላይ ያሉትን መስገጃዎች አላራቀም፤ የአሳ ልብ ግን በዘመኑ ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም ነበረ። አባቱ የቀደሰውንና እርሱም የቀደሰውን ወርቅና ብር ዕቃውንም ወደ እግዚአብሔር ቤት አገባው። በአሳና በእስራኤል ንጉሥ በባኦስ መካከል በዘመናቸው ሁሉ ሰልፍ ነበረ። የእስራኤልም ንጉሥ ባኦስ በይሁዳ ላይ ወጣ፤ ከይሁዳ ንጉሥ ከአሳ ዘንድ ማንም እንዳይወጣ ወደ እርሱም ማንም እንዳይገባ አድርጎ ራማን ሠራ። አሳም በእግዚአብሔር ቤትና በንጉሥ ቤት መዛግብት የቀረውን ብርና ወርቅ ሁሉ ወስዶ በባሪያዎቹ እጅ ሰጣቸው፤ ንጉሡም አሳ በደማስቆ ለተቀመጠው ለአዚን ልጅ ለጠብሪሞን ልጅ ለሶርያ ንጉሥ ቤንሀዳድ “በእኔና በአንተ መካከል በአባቴና በአባትህም መካከል ቃል ኪዳን ጸንቶአል፤ እነሆ፥ ብርና ወርቅ ገጸ በረከት ሰድጄልሃለሁ፤ እርሱ ከእኔ ዘንድ እንዲርቅ ሄደህ ከእስራኤል ንጉሥ ከባኦስ ጋር ያለህን ቃል ኪዳን አፍርስ፤” ብሎ ሰደደ። ቤንሀዳድም ለንጉሡ ለአሳ እሺ አለው፤ የሠራዊቱንም አለቆች በእስራኤል ከተሞች ላይ ሰድዶ ዒዮንንና ዳንን፥ አቤልቤት መዓካንና ኪኔሬትን ሁሉ የንፍታሌምንም አገር ሁሉ መታ። ባኦስም ያን በሰማ ጊዜ ራማን መሥራት ትቶ በቴርሳ ተቀመጠ። ንጉሡም አሳ በይሁዳ ሁሉ ላይ አዋጅ ነገረ፤ ማንም ነጻ አልነበረም፤ ባኦስም የሠራበትን የራማን ድንጋይና እንጨት ወሰዱ፤ ንጉሡም አሳ የብንያምን ጌባንና ምጽጳን ሠራበት። የቀረውም የአሳ ነገር ሁሉ፥ ጭከናውም ሁሉ፥ ያደረገውም ሁሉ፥ የሠራቸውም ከተሞች፥ በይሁዳ ነገሥት ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? ነገር ግን በሸመገለ ጊዜ እግሮቹ ታመሙ። አሳም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በአባቱም በዳዊት ከተማ ከአባቶቹ ጋር ተቀበረ። ልጁም ኢዮሣፍጥ በፋንታው ነገሠ።