መጽሐፈ ጥበብ 8
8
ሰሎሞን ለጥበብ የነበረው ፍቅር
1ጥበብ ከዳርቻ እስከ ዳርቻ ድረስ ደኅና ሆና ትደርሳለች፤ በቸርነትዋም ሁሉን ትሠራለች። 2እኔም ከጐልማሳነቴ ጀምሮ ወደድኋት፤ ፈለግኋትም። ለእኔም ሙሽራ አድርጌ እወስዳት ዘንድ ወደድሁ። ደም ግባትዋንም ወደድሁ። 3የዝምድናዋም ቸርነት ወደ እግዚአብሔር ያቀርባልና ሁሉን የሚገዛ እርሱ ወደዳት። 4የእግዚአብሔርን ምሥጢር ለማወቅ መካር ናትና፥ የሥራውም ወዳጅ ናትና።
5እርሷም ባለችበት ዘንድ ብልጽግና አለ፤ በዚህ ዓለም ገንዘብ ላደረጓት ሰዎች ከሁሉ ትመረጣለች፤ ሁሉን የምታደርግ ጥበብን የሚበልጣት ምንድን ነው? 6ዕውቀትም ቢደረግ በእርሷ ነው፤ ካሉትም ሁሉ ከእርሷ የሚበልጥ ብልህ ማን ነው? 7እውነትን የወደደ ሰውም ቢኖር በእርሷ ነው፤ ድካሟ ያማረ ነውና፥ ንጽሕናንና ጥበብን፥ እውነትንና ብርታትን፥ ትሩፋትንና ደግነትንም ታስተምራለች። በዓለሙ ውስጥም በሰው ሕይወት ከእርሷ የሚሻልና የሚጠቅም ምንም የለም። 8ብዙ ዕውቀትንና ደግነትን ያወቀ ሰው ቢኖር በእርሷ ነው፤ የቀደመውንና የሚመጣውንም ሥራ ያወቀ ሰው ቢኖር በእርሷ ነው፤ የነገር መልስንና ፈጥኖ መተርጐምን ቢያውቅም በእርሷ ነው፤ ተአምራትንና ድንቆችን፥ የጊዜያትንና የዓመታትንም መለዋወጥ አስቀድሞ ቢያውቅ በእርስዋ ነው።
9እኔም፦ ለበጎ ነገር የምትመክርና የምትገሥጽ ኀዘንንና ትካዝን የምታስተው እንደምትሆን ዐውቄ ከእኔ ጋራ እንድትኖር እይዛት ዘንድ ወደድሁ። 10በእርስዋም ምክንያት እኔ ጐልማሳው በብዙዎች ዘንድ ምስጋናን፥ በሽማግሌዎችም ዘንድ ክብርን አገኘሁ። 11ለመፍረድ አሳበ ፈጣን ሆንሁ፤ በኀያላኑም ፊት ተደነቅሁ። 12ዝም ስልም ታግሠው ይጠብቁኝ ነበር፤ ስናገርም ያዳምጡኝ ነበር፤ መናገርም ባበዛ አፋቸውን በእጃቸው ይይዙ ነበር።
13በእርስዋም ምክንያት አለመሞትን አገኘሁ፤ ከእኔም በኋላ ለሚመጡ ሰዎች ለዘለዓለም መታሰቢያን ተውሁ። 14ሕዝቡን እሠራራ ነበር፤ አሕዛብም ይገዙልኝ ነበር። 15የሚያስደነግጡ የምድር መኳንንትም ሰምተው ይፈሩኝ ነበር፤ በሸንጎ ደግ ሆኜ፥ በጠብም ጊዜ ብርቱ ሆኜ እታይ ነበር። 16ከእርሷ ጋር መኖር መራራነት የለበትምና፥ ከደስታና ከሐሤትም በቀር ድካምና ኀዘን አይቀርብምና ወደ ቤቴ በገባሁ ጊዜ በእርሷ ዐርፋለሁ።
17ይህንም በራሴ ሳስብ ኖርሁ፤ ከኀጢአትም መንጻት እንደማይቻለኝ ዐውቄ በልቡናዬ በእርስዋ እተጋለሁ፤ የጥበብ ዝምድናዋ ሕያውነት ነውና። 18በፍቅሯም መልካም ደስታ አለ፤ በእጅዋ ሥራም የማያልቅ ብልጽግና አለ፤ በነገሯም ውስጥ የዕውቀት ትምህርት አለ፤ ከእርሷም ጋር አንድ በመሆን የሚያስመካ ነገር አለ፤ ለራሴም እወስዳት ዘንድ እየፈለግኋት ሀገሩን ዞርሁ።
19እኔ ዐዋቂ ልጅ ነኝ፤ ሰውነቴም በጎ ሆነችልኝ። 20ደግ ነኝና ወደ ንጹሕ ሥጋዋ ገባሁ። 21እግዚአብሔር እርሷን ካልሰጠኝ በቀር እንደማላገኛት#ግእዙ “መንጻት እንደማልችል” ይላል። በዐወቅሁ ጊዜ ይህ ምክር ከጥበብ ሆነ፤ የማን ስጦታም እንደ ሆነች ዐውቅ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸለይሁ፥ ለመንሁትም።
Currently Selected:
መጽሐፈ ጥበብ 8: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ