መጽሐፈ ጥበብ 9
9
ሰሎሞን ጥበብን ለማግኘት የጸለየው ጸሎት
1በፍጹም ልቤም እንዲህ አልሁ፥ “የአባቶች አምላክ፥ የምሕረት ጌታ፥ በቃልህ ዓለሙን ሁሉ የፈጠርኽ፤ 2በጥበብህም ሰውን በአንተ የተፈጠረውን ፍጥረት እንዲገዛ፥ 3ዓለሙንም በቸርነትና በጽድቅ እንዲሠራራ፥ በቅን ልቡናም እንዲፈርድ ያደረግኸው፥ 4በዙፋንህ የምትቀመጥ ጥበብን ስጠኝ፥ ከባሮችህም ለይተህ አትናቀኝ። 5እኔ ባሪያህና የሴት ባሪያህ ልጅ፥ ኀይሌ የደከመ ሰው፥ ዘመኔም ያነሰ፥ ሕግንና ፍርድንም ለማወቅ አነስተኛ ነኝና።
6“ከሰው ልጆችም ፍጹም የሆነ ሰው ቢኖር፥ በአንተ ዘንድም የምትገኝ ጥበብ ከእርሱ ብትርቅ እርሱ እንደ ኢምንት በሆነ ነበር። 7አንተ ለሕዝብህ ንጉሥ፥ ለወንዶች ልጆችህና ለሴቶች ልጆችህም ገዢ አድርገህ መረጥኸኝ። 8በቅዱስ ተራራህ ላይ ቤተ መቅደስ፥ በማረፊያህም ሀገር ከጥንት ጀምሮ ባዘጋጀኸው በቅድስናህ ማደሪያ አምሳል መሠዊያ እንዲሠራ አዘዝኽ። 9ሥራህንም የምታውቅ ጥበብ ከአንተ ጋር ነበረች፤ ዓለምንም በፈጠርኽ ጊዜ ነበረች፤ በፊትህ ደስ የሚያሰኝህም ምን እንደ ሆነ፥ ለትእዛዝህም የቀናው ምን እንደ ሆነ ትረዳ ነበር። 10ተነሥታ ትመጣ ዘንድ ከከበሩ ሰማዮች ከጌትነትህ ዙፋን ወደኔ ላካት፤ ከእኔም ጋራ ትኖርና ትደክም ዘንድ ደስ የሚያሰኝህም ምን እንደ ሆነ ዐውቅ ዘንድ ላካት። 11አንተ የምታውቀውን ሥራ ሁሉ ታውቃለችና ንጹሕ አድርጋ ወደ ሥራዎች ሁሉ ትምራኝ፤ በኀይሏም ትጠብቀኝ። 12ሥራዬ ሁሉ የተወደደ ይሁን፤ ወገኖችህንም በእውነት ልግዛ፤ ለአባቶች ዙፋኖችም የተዘጋጀሁ ልሁን።
13“የእግዚአብሔርን ምክር የሚያውቅ ሰው ማን ነው? እግዚአብሔር የሚወድደውንስ ዐስቦ የሚያውቅ ማን ነው? 14የሟቾች ዐሳባቸው ፈራሽ ነውና፥ የእኛም ዐሳብ ጐፃጕፅ ነውና። 15የሚፈርስ ሥጋ ነፍስን ያሸንፋታልና፥ ይከብዳታልምና፥ ምድራዊ ማደሪያም ልብን ይሸፍናልና። 16በብዙ ትጋትና ግዳጅ፥ በጭንቅም ብንመረምር በምድር የሚሠራውን ሥራ እናገኛለን፤ በእጃችን የምንዳስሰውንም ሥራ በድካም እናገኛለን። በሰማይ ያለውን ግን ማን መረመረው? 17አንተ ጥበብን የሰጠኸው፥ ቅዱስ መንፈስህንም ወደ እርሱ ከላይ የላክህለት ሰው ካልሆነ በቀር ምክርህን ማን ዐወቀ? 18ስለዚህ በዚህ ዓለም ያሉ ሰዎች መንገዳቸው ቀናላቸው፥ ደስ የሚያሰኝህንም ነገር ሰዎች ዐወቁ፥ በጥበብም ዳኑ።”
Currently Selected:
መጽሐፈ ጥበብ 9: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ