መጽሐፈ ሲራክ 38
38
ባለ መድኀኒትና መድኀኒት
1ባለ መድኀኒትን አክብረው፥
እንደ እጁ እንዲሁ ክብሩ ነውና።
እርሱንም እግዚአብሔር ፈጥሮታልና።
2ማዳን ከእግዚአብሔር የሚገኝ ሲሆን፥
ክብርን ግን ከንጉሥ ይቀበላል።
3ሰው ሁሉ ባለ መድኀኒትን በጥበቡ ያከብረዋል፤
በመኳንንትም ዘንድ ይመሰገናል።
4እግዚአብሔር መድኀኒትን ከምድር ፈጠረ፤
ጠቢብ ሰውም ይህን አይንቀውም።
5ኀይሉን ያውቁ ዘንድ፥
ውኃ በእንጨት የጣፈጠ አይደለምን?
6በጌትነቱ ይከብሩ ዘንድ፥
እግዚአብሔር ለሰዎች ጥበብን ሰጣቸው።
7በመድኀኒቱ ያድናቸዋል፤
በሽታቸውንም ያርቅላቸዋል።
8ያድኑ ዘንድ ከእነርሱ መድኀኒትን ያደርጋሉ፤
እርሱም ለሀገር ሰላምን ያመጣል።
9ልጄ ሆይ፥ በሽታህን ቸል አትበል፤
ወደ እግዚአብሔርም ጸልይ፤
እርሱም ይፈውስሃል።
10ኀጢአትን ተዋት፤ እጅህን አቅና፤
ልቡናህንም ከኀጢአት ሁሉ አንጻ።
11መባእህን አግባ፤ የመታሰቢያውንም የስንዴ ዱቄት ስጥ፤
የሰባ መሥዋዕትህንም የተቻለህን ያህል አብዝተህ አቅርብ፤
12እግዚአብሔር እርሱን ፈጥሮታልና፤
ለባለ መድኀኒት መንገድን አብጅለት፥
እርሱንም ትሻዋለህና ከአንተ አታርቀው።
13በእጃቸው ፈውስ የሚደረግበት ጊዜ አለና።
14ይረዳቸው ዘንድ፥ ዕረፍትንም ይሰጣቸው ዘንድ፥
ሁልጊዜም ይፈውሳቸው ዘንድ እነርሱ ወደ እግዚአብሔር ይለምናሉ።
15ፈጣሪውን የሚበድል በባለ መድኀኒት እጅ ይወድቃል።
ለሞተ ሰው መታሰቢያ ስለ ማድረግ
16ልጄ ሆይ፥ ለሞተ ሰው አልቅስለት፥ እዘንለትም፤
ራስህንም አሳዝን፤ እንደ ሥርዐቱም መታሰቢያ አድርግለት።
ያገለገለህን ሰው ሞት ቸል አትበል።#ግሪክ ሰባ. ሊ. “እንደ ሥርዐቱ ሰውነቱን ገንዘው ፤ ቀብሩንም ችላ አትበለው” ይላል።
17እንደ ልማዱ መራራ ልቅሶ አልቅስለት፤
ጥልቅ ኀዘንም እዘንለት፥ የኀዘን መዝሙርም ዘምርለት፤
እንደ ሕጉም አንድ ቀን ቢሆን ሁለት ቀን ቢሆን አልቅስለት።
18ከዚህ በኋላ ልቅሶህን ተው።
ኀዘንም አይግባህ፤
በኀዘን የሞቱ ብዙዎች ናቸውና፥
የልብ ኀዘንም ኀይልን ይሰብራልና።
19ኀዘንና ትካዜ ለሞት ያደርሳል፤
የድሃም ዘመኑ ሁሉ በኀዘን ያልቃል።
20ኀዘንን ወደ ልቡናህ አታግባ፤
ኀዘንን ከአንተ አርቃት።
21ድኅነት እንደሌለባት ዕወቅ፤ ራስህንም ትጎዳለህ፥
ታሳዝናለህ፥ የምትጠቅመውም ነገር የለም።
22እኔ የተቀበልሁትን ፍዳ አስተውል፤
አንተም እንደዚሁ ፍዳን እንደምትቀበል ዕወቅ።
እኔ ዛሬ አንተም ነገ።
23የሞተ ሰውስ ዐረፈ፤
ነገር ግን መታሰቢያውን አድርግለት፤
ከዚህ በኋላ ነፍሱ ታርፍ ዘንድ ልቅሶህን ተው።#ግሪክ ሰባ. ሊ. “የሞተ ሰው ባረፈ ጊዜ ተዝካር ይሁንለት ነፍሱም ከእርሱ በተለየች ጊዜ ስለ እርሱ ተጽናና” ይላል።
24የጸሓፊ ጥበቡ በተሾመበት ወራት ነው፤
ሥራውን የማያበዛ ሰው አይራቀቅም።
25ዕርፉን የሚያጸና ሰው በምንም አይራቀቅም፥
በእርሻው ይታበያል፥ በሬውንም ይገርፋል፤ በሥራውም ይመላለሳል፤
ነገሩም ሁሉ ስለ በሬና ወይፈን ነው።
26አሳቡ እርሻውን እንዲያርስ ነው፤
ትጋቱም በሬውን ገለባ ያበላ ዘንድ ነው፤
ወይፈኑንም እስኪያቀና ድረስ ይደክማል።
27ሌሊቱ ቀን የሚሆንባቸው ጠራቢና የጠራቢዎች አለቃ፥
የማኅተም ቅርጽ የሚቀርጹና የሚያለዝቡ ሰዎች እንደ እርሱ ናቸው፤
እነዚህም አሳባቸው ሁሉ በየመልኩ መስለው ይሠሩ ዘንድ ነው፤
ምክራቸውም ሁሉ ማኅተሙን ማለዘብን ይጠነቀቁ ዘንድ ነው፤
ትጋታቸውም ሥራቸውን ይፈጽሙ ዘንድ ነው።
28በወናፍ አጠገብ የሚቀመጥ፥ የብረትንም ሥራ የሚማር አንጥረኛ እንደ እርሱ ነው።
የወናፉም ጢስ ሰውነቱን ያሻክረዋል።
እሳቱም ሰውነቱን ያቀልጣታል፤ የመዶሻውም ድምፅ ጆሮውን ያደነቍረዋል።
ዐይኖቹም ወደ መሣሪያው ይመለከታሉ፤
በልቡም ሥራውን ይጨርስ ዘንድ ያስባል፤
ትጋቱም መሣሪያውንና ወናፉን ያሳምር ዘንድ ነው።
29በሥራው የሚቀመጥ ሸክላ ሠሪም እንደ እርሱ ነው፥
በእግሩም መንኰራኵርን ያዞራል፤
ሥራውንም እንዴት እንደሚፈጽም ሁልጊዜ ያስባል።
የሠራውንም ሁሉ ይቈጥራል።
30በእጁም ጭቃውን መስሎ ይሠራል፤
በእግሩ ጭቃውን ሲረግጥ ኀይሉን ያደክማል፤
የልቡናውም አሳብ ሥራውን ይጨርስ ዘንድ ነው።
ትጋቱም መወልወያውን ያዞር ዘንድ ነው።
31እነዚህ ሁሉ የእጃቸውን ሥራ ተስፋ ያደርጋሉ፤
ሁሉም በሥራቸው ይራቀቃሉ።
32ያለ እነርሱም ሀገር መኖር አትችልም።
33ነገር ግን በሸንጎ ምክርን አያስመክሯቸውም፤
በአደባባይም ከመኳንንት ጋራ አያስቀምጧቸውም፤
የቅጣት ፍርድንም አያስፈርዷቸውም፤ አያስገዟቸውም፤ አያሠለጥኗቸውምም።
34ነገርን መስሎ በመናገር አይኖሩም፤
ነገር ግን ያገርን ፈቃድ ያጸናሉ፤ ጸሎታቸውም በሥራቸው ይራቀቁ ዘንድ ነው።
35 # ምዕ. 38 ቍ. 35 በግሪክ ሰባ. ሊ. የምዕ. 39 ቍ. 1 ነው። ዕውቀት ግን በልቡ ለሚተጋ ሰው ነው።
የልዑልንም ሕግ ለሚያስብ ሰው ነው።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሲራክ 38: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ