መጽሐፈ ሲራክ 24
24
የጥበብ ክብር
1ጥበብ ራስዋን ታመሰግናለች፤
በአሕዛብም መካከል ትመካለች።
2በልዑልም ጉባኤ ትናገራለች፤
በኀይሉም ፊት ትመካለች።
3እንዲህም አለች፦ እኔ ከልዑል አፍ ወጣሁ፤
ምድርንም እንደ ጉም ሸፈንኋት።
4እኔ በሰማይ ኖርሁ፤
ዙፋኔንም በደመና ዐምድ ላይ ዘረጋሁ።
5ብቻዬንም በሰማይ ዳርቻ ዞርሁ፤
በውቅያኖስ መካከልም ተመላለስሁ፤
6በባሕርም ማዕበል ላይ በየብስም መካከል ሁሉ፥
በሕዝቡና በአሕዛቡ ሁሉ ጥሪትን አደረግሁ።#አንዳንድ የግእዝ ዘርዕ “ኢያጥረይኩ” ይላል።
7ከዚህም ሁሉ በኋላ ዕረፍትን ፈለግሁ፤
እንግዲህ በማን ርስት አድራለሁ?
8ከዚህም በኋላ ሁሉን የፈጠረ አዘዘኝ፤
ፈጣሪም ማደሪያዬን አዘጋጀልኝ፤ እንዲህም አለኝ፦
“በያዕቆብ እደሪ፤ ርስትሽም በእስራኤል ይሁን።”
9ዓለም ሳይፈጠር ወለደኝ፥
ለዘለዓለሙም ከእርሱ አልለይም።
10በተቀደሰ ማደሪያውም በፊቱ አገለገልሁ፤
በጽዮንም አደርሁ።
11እንዲሁም በተወደደችው ከተማ ዐረፍሁ፤
ግዛቴም ባስገዛኝ በኢየሩሳሌም ነበር።
12በእግዚአብሔር ርስት ዕድል ፋንታ፥
በከበረ ሕዝብ መካከል ሥር ሰደድሁ።
13በሊባኖስ እንዳለ ዝግባ ከፍ ከፍ አልሁ፤
በኤርሞን ተራራ እንዳለ ዋንዛም ገነንሁ።
14በውኃ ዳር እንዳለ ዘንባባም ረዘምሁ፤
በኢያሪኮ እንዳለ ጽጌረዳ፥
በምድረ በዳ እንዳለች እንዳማረች የዘይት እንጨትም መዓዛዬ የተወደደ ሆነ፤
እንደ ዋርካ ዛፍም ገነንሁ።
15መዓዛዬም እንደ ቀናንሞስና እንደ ደርሶኒ ሽቱ የተወደደ ሆነ፤
መዓዛዬም እንዳማረ የሽቱ መዓዛ ሆነ፤
እንደ ልባንጃና እንደ ጥርኝ፥ ሰጡቃጤ እንደሚባል ሽቱም፥
በደብተራ ኦሪት እንዳለ እንደ ነጭ ዕጣን መዓዛም የተወደደ ሆነ።
16ቅርንጫፎች እንደ ቡጥም ረዘሙ፤
ቅርንጫፎችም የክብርና የጌትነት ቅርንጫፎች ናቸው።
17እኔስ እንደ ተወደደ የወይን ሐረግ መወደድን አስገኘሁ።
18አበባዬም የክብርና የባለጸግነት ፍሬ ነው።#ግሪክ ሰባ. ሊ. “እኔ የፍቅርና የፍርሀት የዕውቀትና የቅዱስ ተስፋ እናት ነኝ ፤ ስለዚህም በስሙ ለተጠሩ ልጆች ሁሉ ዘለዓለማዊት ሆኜ ተሰጥቻለሁ” ይላል።
19የምትወዱኝ ሰዎች ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤
ከፍሬዬም ትጠግባላችሁ።
20ስም አጠራሬ ከማር፥
ርስትነቴም ከሸንኮር ይልቅ ይጣፍጣልና።
21የሚመገቡኝም አይጠግቡኝም፤
የሚጠጡኝም አይሰለቹኝም።
22የሚሰማኝም አያፍርም፤
ለእኔ የሚገዙ ሰዎች አይስቱም።
23ይህ ሁሉ ነገር የልዑል የሕጉ መጽሐፍ ነው፤
ስለ ያዕቆብም ወገኖች ርስት ሙሴ ያዘዘበት ሕግ ነው።
24በእግዚአብሔር የሚጸና አይደክምም፤
እርሱ ያጸናችሁ ዘንድ ተከተሉት፤
ሁሉን የሚችል ጌታ እግዚአብሔር ብቻ ነው፤
ከእርሱም በቀር ሌላ አዳኝ የለም።
25ጥበብን እንደ ኤፌሶን ፈሳሽ፥
በሚያዝያም ወራት እንደሚመላ እንደ ጤግሮስ ፈሳሽ የሚመላት እርሱ ነው።
26ምክርንም እንደ ኤፍራጥስ ፈሳሽ፥
ባዝመራም ወራት እንደ ዮርዳኖስ ፈሳሽ የሚመላት እርሱ ነው።
27ጥበብን እንደ ብርሃን፥
በወይን አዝመራ ወራትም እንደ አባይ ፈሳሽ የሚገልጣት እርሱ ነው።
28የመጀመሪያው አላወቃትም፤
የመጨረሻውም ፍለጋዋን አላገኘም።
29ምሥጢሯ ከባሕር ውኃ ይልቅ ይበዛል፤
ምክሯም ከባሕሩ ጥልቀት ይልቅ ይጠልቃል።
30ከወንዝ እንደሚፈስስ ውኃ ሆንሁ፤
እንደ መስኖ ውኃም ወደ ተክል ቦታ ገባሁ፤
31እንዲህም አልሁ፥ “የተክል ቦታዬን ላጠጣት፤ የጎመን ቦታዬን ላጠጣት፤”
ፈፋዬ እንደ ወንዝ ሆነልኝ፤ ወንዜም እንደ ባሕር ሆነልኝ።
32ዳግመኛም ጥበብን እንደ ጥዋት አበራታለሁ፤
እስከ ሩቅም ድረስ ብርሃንዋን አሳያለሁ።
33ትምህርትን እንደ ትንቢት አፈስሳታለሁ፤
ለዘለዓለምም ለልጅ ልጅ አጸናታለሁ።
34እነሆ፥ የደከምሁ ለሚፈልጉኝ ሰዎች ሁሉ ነው እንጂ፥
ለእኔ ብቻ እንዳይደለ እዩ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሲራክ 24: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ