መጽሐፈ ሲራክ 22
22
ሰነፍና ስንፍና
1ሰነፍ ሰው በተቀመጠበት ቦታ እንደ ዋሻ ድንጋይ ነው፤
በጽኑ ስንፍናው ሁሉን ያቦዝናል።
2ሰነፍ ሰው በተኛበት ቦታ እንደ ተጣለ ፈርስ ነው።
የነካውም ሰው ሁሉ እጁን ያራግፋል።
3ያልተቀጣ ልጅ ለአባቱ ኀፍረት ነው፤
ያልተቀጣች ሴት ልጅም የጐሰቈለች ትሆናለች።
4ብልህ ሴት ልጅ ባልዋን ትወርሳለች፤
የምታሳፍር ሴት ልጅ ግን ለአባቷ ኀዘን ናት።
5አባትዋንም ታሳፍራለች፤ ባሏንም ታሳፍራለች፤ ደፋርም ናት፤
በሁለቱም ዘንድ እጥፍ ቷረዳለች።
ጥበብና ሞኝነት
6ባገኘበት ቦታ ነገሩን የሚናገር ሰው፥
በልቅሶ ቤት መሰንቆ እንደሚመታ ሰው ነው፤
ግርፋትና ተግሣጽ ሁልጊዜ ብልህ ያደርጋል።
7ሰነፍ ሰውን የሚያስተምር ሰው፥ የተሰበረ ገልን እንደሚጠግን ሰው ነው፤
የተኛ ሰውንም ከጽኑ እንቅልፍ እንደ መቀስቀስ ነው።
8ለሰነፍ ሰው የሚነግር በጽኑዕ እንቅልፍ ለተያዘ ሰው እንደሚነግር ነው፤
ነግረኸው ከጨረስህ በኋላ “ምን ተናገርኽ?” ይልሃል።
9ብርሃኑ አልፏልና ለሞተ ሰው አልቅስለት፤
አእምሮውም ጠፍትዋልና ለሰነፍ ሰው አልቅስለት።
10ከሞተ በኋላ አይመለስምና፥
ለሞተ ሰው ታለቅስለት ዘንድ አገባብ ነው።
ከመሞቱ መኖሩ ይከፋበታልና ለሰነፍ ሰው በሕይወት ሳለ አልቅስለት።
11ሰዎች ስለ ሞተ ሰው ሰባት ቀን ያለቅሱለታል፤
ለሰነፍና ለኀጢአተኛ ግን በሕይወት ዘመኑ ሁሉ አልቅስለት።
12ከሰነፍ ሰው ጋራ ነገርን አታብዛ፤
አእምሮ ከሌለውም ሰው ጋራ አትሂድ፤
ወደ መከራ እንዳያገባህ፥ አንተም በእርሱ ስንፍና እንዳትነቀፍ ተጠበቅ።
13ከእርሱ ራቅ፤ ሰውነትህም ታርፋለች፤ ይቀልሃልም፤
በእርሱም ስንፍና አንተ የምትጐዳው የለም።
14ከአረር#እርሳስ ወይም ማዕድን የሚከብድ ምን አለ?
ሰነፍ ከመባልስ የሚከፋ ምን አለ?
15ከሰነፍ ሰው ጋራ ከመኖር፥
ጨውና አሸዋ፥ ብረትንም ብትሸከም ይሻላል።
16ማገሩ ያማረ፥ በግንብ የታሰረ ቤት በምድር መናወጥ ጊዜ እንደማይፈርስ፥
የብልህ ሰው ምክርም በጽኑዕ ልቡና እንዲሁ ነው።
17ቅጥሩም ለዘለዓለም አይወድቅም፤
በዐዋቂ ሰው ምክር የጸና ልቡናም በግድግዳ ላይ እንዳለ የአሸዋ ምርግ ነው።
18በነፋስ ፊት ያለ ገለባም ነፋስ በነፈሰ ጊዜ እንደማይቆም፥
ያላዋቂ ሰው ዐሳብም ያስፈራው ሰው ቢኖር በማይቆም በፈሪ ሰው ልቡና ዘንድ እንዲሁ ነው።
ወዳጅነትን ጠብቆ ማቈየት
19ዐይኑን የሚጠነቍል ሰው እንባውን ያወርዳል፤
ልቡናውንም የሚነካ ሰው ጥበብን ያሳያል።
20በወፎች ድንጋይ የወረወረባቸው ሰው ያባርራቸዋል፤
በወዳጁም የሚዘብት ሰው ወዳጅነትን ያጠፋል።
21በወዳጅህ ላይ ሰይፍን ብትመዝ፥
ተመልሶ ወዳጅህ ይሆን ይሆናልና ተስፋ አትቍረጥ።
22ነገር ግን ብትላገድበት፥
አፍህንም በእርሱ ላይ ከፍና ዝቅ አድርገህ ብትናገር፥
ብትሰድበውም፥ ምክሩንም ብታወጣበት፥
ብትከዳውና፥ ብታሳዝነው በዚህ ነገር ወዳጅ ሁሉ ይሸሻል።
23አንተም ድሃ ብትሆን በደስታው ጊዜ ከእርሱ ጋር ደስ ይልህ ዘንድ፥
ከባልንጀራህ ጋር ታማኝነትህን ጠብቅ።#ግሪክ ሰባ. ሊ. “በደስታው ጊዜ ከእርሱ ጋር ደስ እንዲልህ በችግሩ ጊዜ ለባልንጀራህ ታማኝ ሁን” ይላል።
ቢቸገርም ርስቱን ባገኘ ጊዜ ከእርሱ ጋር ደስ ይልህ ዘንድ ከእርሱ ጋር ታገሥ።
24የእሳትም የጭሱ ትነት ይቀድማል፤
እንደዚሁም ደም ከማፍሰስ ጠብና ክርክር ይቀድማል።
25ወዳጄን መሰወር አላፍርም፤
ከፊቱም አልሰወርም።
26ነገር ግን በእርሱ ምክንያት ክፋት ብታገኘኝ፥
የሰማ ሁሉ ከእርሱ ራሱን ይጠብቅ።
27ለአንደበቴ ጠባቂ ማን ባኖረልኝ?
በእነርሱ እንዳልወድቅ፥ አንደበቴም እንዳትገድለኝ፥
በከንፈሮች የጥበብን ቍልፍ ማን ባኖረልኝ!
Currently Selected:
መጽሐፈ ሲራክ 22: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ