መጽሐፈ ሲራክ 20
20
1ለበጎ ነገር ሳይሆን የሚገሥጽ ሰው አለ፤
ዐዋቂ ሆኖ ሳለም ዝም የሚል ሰው አለ።#ምዕ. 20 ቍ. 1 በግሪኩ የምዕ. 19 መጨረሻ ነው።
2ነገር ግን ከመንቀፍ መገሠጽ ይሻላል።
3ስሕተቱን የሚያምን ከጥፋት ይድናል።
4ፍርድን ያደላ ዘንድ የሚወድ ሰው፥
ቆንጆ ልጅን እንደሚመኝ ጃንደረባ ነው።
5እያወቀ ዝም የሚል ሰው አለ፥
ንግግር በማብዛትም ራሱን የሚያስጠላ ሰው አለ።
6የሚመልሰውን አያውቅምና ዝም የሚል ሰው አለ፤
ጊዜውንም እስኪያገኝ ድረስ ዝም የሚል ሰው አለ።
7ብልህ ሰውም ጊዜውን እስኪያገኝ ድረስ ዝም ይላል፤
አላዋቂና ደፋር ሰው ግን እንዳገኘ ይናገራል።
8ነገርን የሚያበዛ ሰውን ይቈጡታል፤
ራሱንም የሚያኰራ ሰውን ይጠሉታል።
9ችግሩ የሚያዋርደው ሰው አለ፤
ገንዘብም አግኝቶ የማይበረክትለት ሰው አለ።
10የማይጠቅምህን የሚሰጥህ ሰው አለ፤
ሰጥቶም እጥፍ አድርጎ የሚቀበልህ ሰው አለ።
11እየተቸገረ ራሱን የሚያኰራ አለ፤
ራሱን በማዋረዱም የሚከብር አለ።
12በጥቂት ብዙ የሚገዛ አለ፤
ሰባት እጥፍ ያደርገውም ዘንድ ይፈልጋል።
13ብልህ ሰው በቃሉ ራሱን ያስወድዳል፤
የአላዋቂዎች ስጦታም ተወዳጅነት የላትም።
14አላዋቂ ሰው ጥቅምና ተወዳጅነት የሌለውን ገንዘብ ይሰጥሃል፤
ጥቂት ቢሰጥህም ለልቡ ብዙ የሰጠህ ይመስለዋል።
15ጥቂት ቢሰጥህ ብዙ እንደ ሰጠህ ይላገድብሃል፤
በአንተም ላይ ነገሩን ያበዛል፤ የሰጠህንም ይናገርብህ ዘንድ በአደባባይ ይዞራል፤
ዛሬ ቢሰጥህ ነገ ይከፈልሃል፥ እንዲህ ያለው ሰው የሚያስጠላ ነው።
16አላዋቂ ሰው ግን “ወዳጅ አልፈልግም ምን ይጠቅመኛል?
በጎ ነገር ያደረግሁለት እኔ ዋጋን አላገኝምና፤
እህሌንም የሚመገቡ ሰዎች በእኔ ክፉ ነገር ይናገራሉ።
17ሁሉም ሁልጊዜ ያሙኛል፤
በእኔም ይስቃሉ” ይላል።
የማይገባ ንግግር
18በአንደበትህ አድጦህ ከምትወድቅ፥
በምድር ላይ አድጦህ ብትወድቅ ይሻልሃል፤
እንዲሁ የክፉ ሰው አወዳደቅ ፈጥኖ ይመጣል።
19እንዳገኘ የሚናገር ሰው ራሱን ያስነውራል፤
ለቃሉም መወደድ የለውም፤ በአላዋቂዎች አንደበትም ነገር ይጠላል።
20በጊዜው አይናገረውምና፥
በአላዋቂ ሰው አንደበት ምሳሌ ይጠላል።
21በተቸገረ ጊዜ እግዚአብሔርን ወደ መፍራት የሚመለስ ሰው አለ፤
ሰውነቱም በመልካም ታርፋለች።
22በማፈርም ሰውነቱን የሚያጠፋ አለ፤
በአላዋቂነቱም ሰውነቱን ያጠፋል።
23በማፈር ላይሰጠው ለወዳጁ ተስፋ የሚሰጠው አለ።
ስለዚህም ነገር በከንቱ ጠላት ይሆነዋል።
24የሐሰተኛ ሰው ውርደቱ ክፉ ነው፤
የአላዋቂዎች ነገራቸው የተጠላ ነው።
25ከሐሰተኛ ሌባ ይሻላል፤
ነገር ግን የሁለቱም ፍጻሜያቸው ሞትና ውርደት ነው።
26ሐሰተኛ ሰው ፈጽሞ ይዋረዳል፥ ያፍራልም።
27በቃሉ ብልህ የሆነ ሰው ነገሩ ይሰማል፤
ብልህ ሰው መኳንንቱን ደስ ያሰኛል።
28ምድርን የሚያርሳት የእህሉን ክምር ያበዛል፤
መኳንንቱንም የሚያገለግል ራሱን ይጠቅማል።
29እጅ መንሻና መማለጃ የጠቢባንን ዐይን ያሳውራል፤
አፋቸውን ይዘጋል፤ ቃላቸውንም ያስለውጣል።
30የተሰወረ ጥበብ እንደ ተቀበረ ወርቅ ነው፤
እንግዲህ የሁለቱስ ጥቅማቸው ምንድን ነው?
31ጥበቡን ከሚሰውር ብልህ ሰው፤
አለማወቁን የሚሰውር አላዋቂ ሰው ይሻላል።
Currently Selected:
መጽሐፈ ሲራክ 20: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ