ወንጌልን ለማስተማር አላፍርምና፤ አስቀድሞ አይሁዳዊን፥ ደግሞም አረማዊን፥ የሚያምኑበትን ሁሉ የሚያድናቸው የእግዚአብሔር ኀይሉ ነውና። “ጻድቅ በእምነት ይኖራል” ብሎ መጽሐፍ እንደ ተናገረ የእግዚአብሔር ጽድቅ ከእምነት ወደ እምነት በእርሱ ይገለጣልና። እውነትን ዐውቀው በክፋታቸው በሚለውጡአት በዐመፀናውና በኀጢአተናው ሰው ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር መቅሠፍት ከሰማይ ይመጣል። እግዚአብሔር ስለ ገለጠላቸው እግዚአብሔርን ማወቅ በእነርሱ ዘንድ ግልጥ ነውና። የማይታየው የእግዚአብሔር ባሕርይ እርሱም የዘለዓለም ኀይሉና ጌትነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ የፈጠረውን ፍጥረት በማሰብና በመመርመር ይታወቃል፤ መልስ የሚሰጡበትን ምክንያት እንዳያገኙ። እግዚአብሔርን ሲያውቁት እንደ እግዚአብሔርነቱ አላከበሩትም፤ አላመሰገኑትምም፤ ነገር ግን ካዱት፤ በአሳባቸውም ረከሱ፤ ልቡናቸውም ባለማወቅ ጨለመ። ጥበበኞች ነን ሲሉ አላዋቆች ሆኑ። የማይሞተውን የእግዚአብሔርን ክብር በሚሞት ሰውና በዎፎች፥ አራት እግር ባላቸውም፥ በሚንቀሳቀሱትም መልክ መስለው ለወጡ። ስለዚህም እግዚአብሔር እርስ በርሳቸው ሥጋቸውን ሊያዋርዱ በልባቸው ፍትወት ወደ ርኵሰት አሳልፎ ተዋቸው። የእግዚአብሔርን እውነት ሐሰት አድርገዋታልና፤ ተዋርደውም ፍጥረቱን አምልከዋልና፤ ሁሉን የፈጠረውን ግን ተዉት፤ እርሱም ለዘለዓለም ቡሩክ አምላክ ነው፤ አሜን። ስለዚህም እግዚአብሔር ክፉ መቅሠፍትን አመጣባቸው፤ ሴቶቻቸውም ለባሕርያቸው የሚገባውን ትተው ለባሕርያቸው የማይገባውን ሠሩ። ወንዶችም እንዲሁ ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን ትተው በፍትወት ተቃጠሉ፤ እርስ በርሳቸውም እየተመላለሱ፥ ወንዶች በወንዶች ላይ የሚያዋርዳቸውን ነውር ሠሩ፤ ነገር ግን ፍዳቸውን ያገናሉ፤ ፍዳቸውም በራሳቸው ይመለሳል። እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልወደዱ መጠን እንዲሁ እግዚአብሔር ይህን የማይገባውን ይሠሩ ዘንድ ሰነፍ አእምሮን ሰጣቸው። እነርሱም ዐመፅን ሁሉ፥ ክፋትንም፥ ምኞትንም፥ ቅሚያንም፥ ቅናትንም የተመሉ ናቸው፤ ምቀኞች፥ ነፍሰ ገዳዮች፥ ከዳተኞች፥ ተንኰለኞች፥ ኩሩዎች፥ ጠባያቸውንና ግብራቸውንም ያከፉ ናቸው። ሐሜተኞች፥ እግዚአብሔርን የሚጠሉ፥ ተሳዳቢዎች፥ ትዕቢተኞች፥ ትምክሕተኞች፥ ክፋትን የሚፈላለጉ፥ ለወላጆቻቸውም የማይታዘዙ ናቸው። የማያስተውሉ፥ ዝንጉዎች፥ ፍቅርም፥ ምሕረትም የሌላቸው ናቸው። ይህን እንዲህ ላደረገ ሞት እንደሚገባው እነርሱ ራሳቸው የእግዚአብሔርን ፍርድ እያወቁ፥ እነርሱ ብቻ የሚያደርጉት አይደለም፤ ነገር ግን ሌላውን ያነሣሡታል፤ ያሠሩታልም።
ወደ ሮሜ ሰዎች 1 ያንብቡ
ያዳምጡ ወደ ሮሜ ሰዎች 1
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ወደ ሮሜ ሰዎች 1:16-32
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች