እንዲህም ሆነ፤ በዮርዳኖስ ማዶ በተራራማው በሜዳውም በታላቁ ባሕር ዳር በሊባኖስም ፊት ለፊት የነበሩ ነገሥት ሁሉ፥ ኬጤዎናዊዉ፥ አሞሬዎናዊዉም፥ ከነዓናዊዉም፥ ፌርዜዎናዊዉም፥ ኤዌዎናዊዉም፥ ኢያቡሴዎናዊዉም፥ ጌርጌሴዎናዊዉም ይህን በሰሙ ጊዜ፥ ኢያሱንና እስራኤልን ሁሉ ሊወጉ አንድ ሆነው ተሰበሰቡ። በገባዖን የሚኖሩ ሰዎች ግን እግዚአብሔር በኢያሪኮና በጋይ ያደረገውን በሰሙ ጊዜ፥ እነርሱ ደግሞ ተንኰል አድርገው መጡ፤ ለራሳቸውም ስንቅ ያዙ፤ በትከሻቸውም ላይ አሮጌ ዓይበትና ያረጀና የተቀደደ የተጠቀመም የጠጅ ረዋት ተሸከሙ። በእግራቸውም ያደረጉት ጫማ ያረጀና ማዘቢያው የተበጣጠሰ፥ ልብሳቸውም በላያቸው ያረጀ ነበረ፤ ለስንቅም የያዙት እንጀራ ሁሉ የደረቀ፥ የሻገተና የተበላሸ ነበረ። ወደ ኢያሱና ወደ እስራኤል ጉባኤ ወደ ጌልገላ መጥተው ለኢያሱና ለእስራኤል ሁሉ፥ “ከሩቅ ሀገር መጥተናል፤ አሁንም ከእኛ ጋር ቃል ኪዳን አድርጉ” አሉ። የእስራኤልም ልጆች ኤዌዎናውያንን፥ “ምናልባት በመካከላችን የምትቀመጡ እንደ ሆነ እንዴትስ ከእናንተ ጋር ቃል ኪዳን እናደርጋለን?” አሉአቸው። ኢያሱንም፥ “እኛ ባሪያዎችህ ነን፤ ከሩቅ ሀገርም ነን” አሉት። ኢያሱም፥ “እናንተ እነማን ናችሁ? ከወዴትስ መጣችሁ?” አላቸው። እነርሱም አሉት፥ “በአምላክህ በእግዚአብሔር ስም እጅግ ከራቀ ሀገር ባሪያዎችህ መጥተናል፤ ዝናውንም፥ በግብፃውያንም ያደረገውን ሁሉ፥ በዮርዳኖስ ማዶም በነበሩት በሁለቱ በአሞሬዎን ነገሥት በሐሴቦን ንጉሥ በሴዎን፥ በአስታሮትና በኤድራይን በነበረው በባሳን ንጉሥ በዐግ ያደረገውን ሁሉ ሰምተናል። ሽማግሌዎቻችንና የሀገራችን ሰዎች ሁሉ፦ ለመንገድ ስንቅ ያዙ፤ ልትገናኙአቸውም ሂዱ፦ እኛ ባሪያዎቻችሁ ነን፤ አሁንም ከእኛ ጋር ቃል ኪዳን አድርጉ በሉአቸው አሉን። ወደ እናንተ ለመምጣት በተነሣንበት ቀን ይህን እንጀራ ትኩሱን ለስንቅ ከቤታችን ያዝነው፤ አሁንም እነሆ፥ ደርቆአል፤ ሻግቶአልም። እነዚህም የጠጅ ረዋቶች አዲሶች ሳሉ ሞላንባቸው፤ እነሆም፥ አርጅተው ተቀድደዋል፤ መንገዳችንም እጅግ ስለ ራቀብን እነዚህ ልብሶቻችንና ጫማዎቻችን አርጅተዋል።” አለቆችም ከስንቃቸው ወሰዱ፤ እግዚአብሔርንም አልጠየቁም። ኢያሱም ከእነርሱ ጋር ሰላም አደረገ፤ በሕይወት እንዲተዋቸውም ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፤ የማኅበሩም አለቆች ማሉላቸው።
መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 9 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ኢያሱ ወልደ ነዌ 9:1-15
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች