“አሁንም የሚመልስልህ ካለ ጥራ፥ ከቅዱሳን መላእክትም የምታየው ካለ? ሰነፉን ሰው ቍጣ ይገድለዋልና፥ ቅንዓትም ሰነፉን ያጠፋዋል። ሰነፎችን ሥር ሰድደው አየኋቸው፥ በድንገትም መኖሪያቸው ጠፋች። ልጆቻቸው ከደኅንነት ርቀዋል፥ በበርም ውስጥ ይቀጠቅጡአቸዋል፤ መከራም ያጸኑባቸዋል፥ የሚታደጋቸውም የለም። እነርሱ የሰበሰቡትንም ጻድቃን ይበሉታል። እነርሱን ግን ክፋት ቷጋቸዋለች፥ ኀይላቸውም ይደክማል። ችግር ከምድር አይወጣምና፥ መከራም ከተራሮች አይበቅልምና፤ የአሞራ ግልገሎች ግን ወደ ላይ እየበረሩ ከፍ እንዲሉ፥ ሰው እንዲሁ ለድካም ተወልዶአል። “እኔ ግን እግዚአብሔርን እለምነው ነበር፥ የሁሉ ጌታ እግዚአብሔርንም እጠራው ነበር። እርሱ የማይመረመረውን ታላቅ ነገርና የማይቈጠረውን የከበረና ድንቅ ነገር ያደርጋል። በምድር ላይ ዝናብን ይሰጣል፥ ከሰማይም በታች ውኃን ይልካል። የተዋረዱትን ከፍ ያደርጋቸዋል፥ የወደቁትንም ያነሣቸዋል። የተንኰለኞችን ምክር ይለውጣል፥ እጆቻቸውም ቅን አይሠሩም። ጠቢባንንም በተንኰላቸው ይይዛቸዋል፤ ምክርን የሚጐነጉኑ ሰዎችን አሳብ ያጠፋል። በቀን ጨለማ ያገኛቸዋል፥ በቀትርም ጊዜ በሌሊት እንዳሉ ይርመሰመሳሉ። በጦርነት ይጠፋሉ፤ ደካማውም ከኀያሉ እጅ ያመልጣል። ለምስኪኑ ተስፋ አለውና፤ የዐመጸኛም አፍ ይዘጋልና። “ነገር ግን እግዚአብሔር የሚገሥጸው ሰው ብፁዕ ነው፤ ስለዚህ ሁሉን የሚችለውን የአምላክን ተግሣጽ አትናቅ። እርሱ ይሰብራል፥ ዳግመኛም ይጠግናል፤ ይቀሥፋል፥ እጆቹም ይፈውሳሉ። ስድስት ጊዜ ከክፉ ነገር ያድንሃል፥ በሰባተኛውም ጊዜ ክፋት አትነካህም። በራብ ጊዜ ከሞት ያድንሃል፥ በጦርነትም ጊዜ ከሰይፍ እጅ ያድንሃል። ከምላስ ጅራፍ ይሰውርሃል፥ ከምትመጣብህም ክፋት አትፈራም። በኃጥኣንና በዐመጸኞች ላይ ትስቅባቸዋለህ፤ ከምድረ በዳ አራዊትም አትፈራም፤ የምድረ በዳ አራዊትም ከአንተ ጋር ይስማማሉ። ያንጊዜ ቤትህ በሰላም እንዲሆን ታውቃለህ፤ ከንብረትህም አንዳች አይጐድልም። ዘርህም ብዙ እንዲሆን፥ ልጆችህም እንደ አማረ መስክ ሣር እንዲሆኑ ታውቃለህ። በወራቱ የደረሰ አዝመራ እንዲሰበሰብ፥ የእህሉ ነዶም በወቅቱ ወደ አውድማ እንዲገባ፥ በረዥም ዕድሜ ወደ መቃብር ትገባለህ። እነሆ፥ ይህን ዐውቀን መረመርን፥ የሰማነውም ይህ ነው፤ አንተ ግን አንዳች ሠርተህ እንደ ሆነ ለራስህ ዕወቅ።”
መጽሐፈ ኢዮብ 5 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ኢዮብ 5:1-27
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች