ትንቢተ ኤርምያስ 46
46
ግብፅ በከርከሚሽ ላይ ድል እንደ ሆነች
1በአሕዛብ ላይ ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው።#ግሪክ ሰባ. ሊ. ልዩ ነው። 2በግብፅ ላይ፤ በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ በከርኬማስ በነበረው፥ በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም በአራተኛው ዓመተ መንግሥት የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በመታው በግብፅ ንጉሥ በፈርዖን ኒካዑ ሠራዊት፥
3“ጋሻና ጦር ያዙ፤ ወደ ሰልፍም ቅረቡ። 4ፈረሰኞች ሆይ፥ ፈረሶችን ጫኑና ውጡ፤ ራስ ቍርንም ደፍታችሁ ቁሙ፤ ጦርንም ሰንግሉ፤ ጥሩርንም ልበሱ። 5ፈርተው ወደ ኋላ ሲመለሱ፥ ኀያላኖቻቸውም ሲደክሙ፥ ወደ ኋላቸውም ሳይመለከቱ ፈጥነው ሲሸሹ ለምን አየሁ? በዙሪያቸውም ይከቡአቸዋል፥” ይላል እግዚአብሔር። 6ፈጣኑም አያመልጥም፤ ኀያሉም አይድንም፤ በሰሜን በኤፍራጥስ ወንዝ በኩል ደክመው ወደቁ።
7ይህ እንደ ወንዝ የሚነሣ ውኃውም እንደ ወንዝ የሚናወጥ ማን ነው? 8ግብፅ እንደ ወንዝ ይነሣል፤ ከባሕሩም እንደሚታወክ ማዕበል ይሆናል፤ እርሱም እንዲህ ብሏል፥ “እነሣለሁ፤ ምድርንም ሁሉ እከድናለሁ፤ ከተሞችንና የሚኖሩባቸውን አጠፋለሁ። 9በፈረሶች ተቀመጡ፤ ሰረገሎችንም አዘጋጁና ውጡ፤ ጋሻም የሚያነግቡ የኢትዮጵያና የሊብያ#ግእዝና ዕብ. “ፉጥ” ይላል። ኀያላን፥ ቀስትንም ይዘው የሚስቡ የሉድ ኀያላን ይውጡ። 10ያ ቀን ጠላቶቹን የሚበቀልበት የአምላካችን የእግዚአብሔር የበቀል ቀን ነው፤ የእግዚአብሔር ሰይፍ በልቶ ይጠግባል፤ በደማቸውም ይሰክራል፤ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር መሥዋዕት በሰሜን ምድር በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ ነውና። 11ድንግሊቱ የግብፅ ልጅ ሆይ! ወደ ገለዓድ ውጪ፤ የሚቀባ መድኀኒትንም ውሰጂ፤ ለምንም የማይጠቅምሽን መድኀኒት በከንቱ አብዝተሻል። 12ጦረኞች በጦረኞች ላይ ተሰናክለው ሁለቱ በአንድነት ወድቀዋልና አሕዛብ ቃልሽን ሰምተዋል፤ ልቅሶሽም ምድርን ሞልቶአታል።”
ናቡከደነፆር ወደ ግብፅ እንደ መጣ
13የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር እንደሚመጣና የግብፅን ምድር እንደሚመታ እግዚአብሔር ለነቢዩ ለኤርምያስ የተናገረው ቃል ይህ ነው።
14“በግብፅ ተናገሩ፤#“በግብፅ ተናገሩ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። በሚግዶልም አውሩ፤ በሜምፎስና በጣፍናስ አሰሙ፤ ሰይፍ በዙሪያህ ያለውን በልቶአልና፦ ተነሥ ተዘጋጅም በሉ። 15ኀይለኞችህ ስለ ምን ታጡ? እግዚአብሔር ስላደከማቸው የሉም።#ግሪክ ሰባ. ሊ. “አፒስ ለምን ሸሸፍክ? ምርጥ በሬውም አልቆመም ፤ እግዚአብሔር አድክሞአቸዋልና” ይላል። 16ብዛታቸውም ደከመ፤ ወደቀም፤ አንዱም አንዱ ለጓደኛው፦ ተነሥ፤ ከአረማውያን ሰይፍ ፊት ወደ ወገናችን ወደ ተወለድንባት ምድር እንመለስ አለው። 17በዚያም የግብፅ ንጉሥ የፈርዖንን ስም ጊዜውን የሚያሳልፍ ብለው ጠሩት። 18እኔ ሕያው ነኝና በተራሮች መካከል እንዳለ እንደ አጤቤርዮን፥#ዕብ. “ታቦር” ይላል። በባሕርም አጠገብ እንዳለ እንደ ቀርሜሎስ፥ እንዲሁ በእውነት ይመጣል፥ ይላል ስሙ የሠራዊት ጌታ የሆነ ንጉሥ እግዚአብሔር። 19አንቺ በግብፅ የምትቀመጪ ልጅ ሆይ! ሜምፎስ ባድማ ትሆናለችና፥ የሚቀመጥባትም አይገኝምና ለፍልሰት የሚሆን ዕቃ አዘጋጂ።
20“ግብፅ የተዋበች ጊደር ናት፤ ጥፋት ግን ከሰሜን#ግእዝ “ከደቡብ” ይላል። በኩል ይመጣባታል። 21በእርስዋም ያሉ የተቀጠሩ ሠራተኞች በእርስዋ ተቀልበው እንደ ሰቡ ወይፈኖች ናቸው፤ የጥፋታቸው ቀንና የቅጣታቸው ጊዜ መጥቶባቸዋልና ተመለሱ፤ በአንድነትም ሸሹ፤ አልቆሙምም። 22ሠራዊትም በኀይል ይዘምቱባታልና፥ እንደ እንጨት ቈራጮችም በምሳር ይመጡባታልና ድምፅዋ እንደምትሸሽ እባብ ይተማል። 23ሊቈጠሩ የማይችሉ የዱርዋን ዛፎች ይቈርጣሉ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ከአንበጣ ይልቅ በዝተዋልና፥ ቍጥርም የላቸውምና። 24የግብፅ ልጅ ታፍራለች፤ በሰሜን ሕዝብ እጅም አልፋ ትሰጣለች።” 25የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “እነሆ የኖእ አሞንን፥ ፈርዖንንም፥ ግብጽንም፥ አማልክቶችዋንና ነገሥታቶችዋንም፥ ፈርዖንንና በእርሱም የሚታመኑትን እቀጣለሁ።#ምዕ. 46 ቍ. 25 በግሪክ ሰባ. ሊ. ልዩ ነው። 26ነፍሳቸውንም በሚፈልጉ ሰዎች እጅ፥ በባቢሎንም ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ፥ በአገልጋዮቹም እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ ከዚያም በኋላ እንደ ቀድሞው ዘመን የሰው መኖሪያ ትሆናለች፥ ይላል እግዚአብሔር።”#ምዕ. 46 ቍ. 26 በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም።
እግዚአብሔር ሕዝቡን እንደሚታደግ
27“ነገር ግን አንተ ባሪያዬ ያዕቆብ ሆይ! አትፍራ፥ አንተም እስራኤል ሆይ! አትደንግጥ፤ እነሆ አንተን ከሩቅ፥ ዘርህንም ከተማረኩባት ምድር አድናለሁ፤ ያዕቆብም ተመልሶ ያርፋል፤ ተዘልሎም ይተኛል፤ ማንም አያስፈራውም። 28አንተ ባሪያዬ ያዕቆብ ሆይ! እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፥” ይላል እግዚአብሔር፤ አንተንም ያሳደድሁባቸውን አሕዛብን ሁሉ ፈጽሜ አጠፋለሁና፥ አንተን ግን ፈጽሜ አላጠፋህም፤ በመጠን እቀጣሃለሁ፥ ያለ ቅጣትም አልተውህም።”#ምዕ. 46 በግሪክ ሰባ. ሊ. ምዕ. 26 ነው።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 46: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ