ኦሪት ዘፍጥረት 7:5-18
ኦሪት ዘፍጥረት 7:5-18 አማ2000
ኖኅም እግዚአብሔር አምላክ ያዘዘውን ሁሉ አደረገ። ኖኅም የጥፋት ውኃ በምድር ላይ በሆነ ጊዜ የስድስት መቶ ዓመት ዕድሜ ነበረ። ኖኅም ስለ ጥፋት ውኃ ልጆቹንና ሚስቱን፥ የልጆቹንም ሚስቶች ይዞ ወደ መርከብ ገባ። ከንጹሓን ወፎችና ንጹሓን ካልሆኑ ወፎች፥ ከንጹሕ እንስሳ፥ ንጹሕም ካልሆነው እንስሳ፥ በምድር ላይ ከሚንቀሳቀሰው ሁሉ፥ እግዚአብሔር ኖኅን እንዳዘዘው፥ ሁለት ሁለት ተባትና እንስት እየሆኑ ወደ ኖኅ ወደ መርከብ ውስጥ ገቡ። ከሰባት ቀን በኋላም የጥፋት ውኃ በምድር ላይ ሆነ። በኖኅ ዕድሜ በስድስተኛው መቶ ዓመት በሁለተኛው ወር ከወሩም በዐሥራ ሰባተኛው ዕለት፥ በዚያው ቀን የታላቁ ቀላይ ምንጮች ሁሉ ተነደሉ፤ የሰማይ መስኮቶችም ተከፈቱ፤ ዝናቡም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ሆነ። በዚያውም ቀን ኖኅ ወደ መርከብ ገባ፤ የኖኅ ልጆችም ሴም፥ ካም፥ ያፌትና የኖኅ ሚስት፥ ሦስቱም የልጆቹ ሚስቶች ከእርሱ ጋር ገቡ። አራዊትም ሁሉ በየወገናቸው፥ እንስሳትም ሁሉ በየወገናቸው፥ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱ ተንቀሳቃሾችም ሁሉ በየወገናቸው፥ ወፎችም ሁሉ በየወገናቸው፥ የሚበሩ ወፎችም ሁሉ፥ ሥጋ ያላቸው ሕያዋን ሁሉ ሁለት ሁለት እየሆኑ ወደ ኖኅ መርከብ ውስጥ ገቡ። ሥጋ ካለው ሁሉ የገቡትም ተባትና እንስት እግዚአብሔር ኖኅን እንዳዘዘው ገቡ፤ እግዚአብሔር አምላክም መርከብዋን በስተውጭ ዘጋት። የጥፋት ውኃ በምድር ላይ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ነበረ፤ ውኃውም በዛ፤ መርከቢቱንም አነሣ፤ ከምድርም ወደ ላይ ከፍ ከፍ አለች። ውኃውም አሸነፈ፤ በምድር ላይም እጅግ በዛ፤ መርከቢቱም በውኃ ላይ ተንሳፈፈች።

