ዘፍጥረት 7:5-18

ዘፍጥረት 7:5-18 NASV

ኖኅም እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ አደረገ። የጥፋት ውሃ በምድር ላይ በወረደ ጊዜ ኖኅ የስድስት መቶ ዓመት ሰው ነበር። ኖኅና ወንዶች ልጆቹ፣ ሚስቱና የልጆቹ ሚስቶች ከጥፋት ውሃ ለመትረፍ ወደ መርከቧ ገቡ። ንጹሕ ከሆኑትና ንጹሕ ካልሆኑት እንስሳት፣ ከወፎችና በምድር ላይ ከሚሳቡ ፍጥረታት ሁሉ ጥንድ ጥንድ፣ ተባዕትና እንስት ሆነው ወደ ኖኅ መጡ፤ እግዚአብሔር ኖኅን ባዘዘውም መሠረት ወደ መርከቧ ገቡ። ከሰባት ቀንም በኋላ የጥፋት ውሃ በምድር ላይ መጣ። ኖኅ በተወለደ በስድስት መቶኛው ዓመት፣ በሁለተኛው ወር፣ ከወሩም በዐሥራ ሰባተኛው ቀን፣ በዚያ ቀን የታላቁ ጥልቅ ምንጮች በሙሉ ተነደሉ፤ የሰማይ መስኮቶችም ተከፈቱ፤ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በምድር ላይ ዝናብ ዘነበ። በዚያ ዕለት ኖኅና ልጆቹ ሴም፣ ካምና ያፌት፣ እንዲሁም ሚስቱና ሦስቱ የልጆቹ ሚስቶች ወደ መርከቧ ገቡ። ከዱር እንስሳት ከየወገኑ፣ ከቤት እንስሳት ከየወገኑ፣ በምድር ላይ ከሚሳቡ ፍጥረታት ከየወገናቸው፣ ከወፎችም ከየወገናቸውና ክንፍ ያላቸው ሁሉ ዐብረዋቸው ገቡ። የሕይወት እስትንፋስ ያለባቸው ፍጥረታት በሙሉ ጥንድ ጥንድ እየሆኑ ወደ ኖኅ በመምጣት መርከቧ ውስጥ ገቡ። ከሕያዋንም ፍጥረታት ሁሉ እግዚአብሔር ኖኅን ባዘዘው መሠረት ተባዕትና እንስት እየሆኑ ገቡ፤ ከዚያም እግዚአብሔር ከውጭ ዘጋበት። የጥፋት ውሃም ለአርባ ቀናት ያለ ማቋረጥ በምድር ላይ ዘነበ፤ ውሃው እየጨመረ በሄደ መጠን መርከቧን ከምድር ወደ ላይ አነሣት። ውሃው በምድር ላይ በጣም እየጨመረና ከፍ እያለ ሲሄድ፣ መርከቧ በውሃው ላይ ተንሳፈፈች።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}