ከእነዚህም ነገሮች በኋላ እንዲህ ሆነ። እግዚአብሔር አብርሃምን ፈተነው፤ እንዲህም አለው፥ “አብርሃም! አብርሃም ሆይ፥” እርሱም፥ “እነሆ፥ አለሁ” አለ። “የምትወድደውን አንድ ልጅህን ይስሐቅን ይዘህ ወደ ከፍተኛው ተራራ ሂድ፤ እኔም በምነግርህ በአንድ ተራራ ላይ በዚያ መሥዋዕት አድርገህ ሠዋው” አለው። አብርሃምም በማለዳ ተነሥቶ አህያውን ጫነ፤ ሁለቱንም ሎሌዎቹንና ልጁን ይስሐቅን ከእርሱ ጋር ወሰደ፤ ዕንጨትንም ለመሥዋዕት ሰነጠቀ፤ ተነሥቶም እግዚአብሔር ወዳለው ቦታ ሄደ፤ በሦስተኛውም ቀን ደረሰ። አብርሃምም ዐይኑን አነሣና ቦታውን ከሩቅ አየ። አብርሃምም ሎሌዎቹን አላቸው፥ “አህያውን ይዛችሁ በዚህ ቈዩ፤ እኔና ልጄ ወደዚያ ተራራ ሄደን እንሰግዳለን፤ ሰግደንም ወደ እናንተ እንመለሳለን።” አብርሃምም የመሥዋዕቱን ዕንጨት አንሥቶ ለልጁ ለይስሐቅ አሸከመው፤ እርሱም እሳቱንና ቢላዋዉን በእጁ ያዘ፤ ሁለቱም አብረው ሄዱ። ይስሐቅም አባቱን አብርሃምን ተናገረው፥ “አባቴ ሆይ፥” አለ፤ እርሱም፥ “ልጄ፥ ምንድን ነው?” አለው። “እሳቱና ዕንጨቱ ይኸው አለ፤ የመሥዋዕቱ በግ ግን ወዴት አለ?” አለው። አብርሃምም፥ “ልጄ ሆይ፥ የመሥዋዕቱን በግ እግዚአብሔር ያዘጋጃል” አለው፤ ሁለቱም አብረው ሄዱ። እግዚአብሔር ወዳለውም ወደዚያ ቦታ ደረሱ፤ አብርሃምም በዚያ መሠዊያዉን ሠራ፤ ዕንጨትንም ረበረበ፤ ልጁን ይስሐቅንም አስሮ በመሠዊያዉ በዕንጨቱ ላይ በልቡ አስተኛው። አብርሃምም እጁን ዘረጋ፤ ልጁንም ያርድ ዘንድ ቢላዋ አነሣ። የእግዚአብሔር መልአክም ከሰማይ ጠራና፥ “አብርሃም! አብርሃም” አለው፤ እርሱም፥ “እነሆኝ” አለ። እርሱም፥ “በብላቴናው ላይ እጅህን አትዘርጋ፤ አንዳችም አታድርግበት፤ ለምትውድደው ልጅህ ከእኔ አልራራህለትምና አንተ እግዚአብሔርን የምትፈራ እንደሆንህ አሁን ዐውቄአለሁ” አለው። አብርሃምም ዐይኖቹን አቅንቶ በተመለከተ ጊዜ፥ በኋላው እነሆ፥ አንድ በግ ቀንዶቹ በዕፀ ሳቤቅ ተይዞ አየ፤ አብርሃምም ሄዶ በጉን ወሰደው፤ በልጁ በይስሐቅ ፈንታም ሠዋው። አብርሃምም ዛሬ በዚህ ተራራ እግዚአብሔር ፈጽሞ ታየኝ ሲል ያን ቦታ “ራእየ እግዚአብሔር” ብሎ ጠራው። የእግዚአብሔር መልአክም አብርሃምን ከሰማይ ሁለተኛ ጊዜ ጠራው፤ እንዲህም አለው፦ “እግዚአብሔር በራሴ ማልሁ ይላል፤ ይህን ነገር አድርገሃልና፥ ለምትወድደው ልጅህም ከእኔ አልራራህምና መባረክን እባርክሃለሁ፤ ዘርህንም እንደ ሰማይ ከዋክብትና በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ ፈጽሞ አበዛዋለሁ፤ ዘርህም የጠላት ሀገሮችን ይወርሳሉ፤ የምድር አሕዛብ ሁሉም በዘርህ ይባረካሉ፤ ቃሌን ሰምተሃልና።” አብርሃምም ወደ ብላቴኖቹ ተመለሰ፤ ተነሥተውም ወደ ዐዘቅተ መሐላ አብረው ሄዱ፤ አብርሃምም በዐዘቅተ መሐላ ተቀመጠ። እንዲህም ሆነ፤ ከዚህ ነገር በኋላ ለአብርሃም እንዲህ ተብሎ ተነገረ፥ “እነሆ፥ ሚልካ ደግሞ ለወንድምህ ለናኮር ልጆችን ወለደች፤ እነርሱም በኵሩ ዑፅ፥ ወንድሙ በዋክሲ፤ የአራም አባት ቀማኤል፥ አኮዛት፥ ኤዝራው፥ ፌልዳስ፥ ዮፋትና ባቱኤል” ናቸው። ባቱኤልም ርብቃን ወለደ፤ ሚልካ ለአብርሃም ወንድም ለናኮር የወለደችለት ስምንቱ ልጆች እነዚህ ናቸው። ሬሕማ የሚሉአት ዕቅብቱ ደግሞ ጥባህን፥ ቤካን፥ ጠኮንና ሜካን ወለደች።
ኦሪት ዘፍጥረት 22 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፍጥረት 22:1-24
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች