እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ፤ እንደ ገናም በባርነት ቀንበር አትኑሩ። እነሆ፥ እኔ ጳውሎስ እላችኋለሁ፤ “ብትገዘሩም በክርስቶስ ዘንድ ምንም አይጠቅማችሁም።” ደግሞም ለተገዘረ ሰው ሁሉ የኦሪትን ሕግ መፈጸም እንደሚገባው እመሰክራለሁ። በኦሪት ልትጸድቁ የምትፈልጉ እናንተ ከክርስቶስ ተለይታችሁ ከጸጋዉ ወድቃችኋል። እኛ ግን በመንፈስ ቅዱስ፥ በእምነትም ልንጸድቅ ተስፋ እናደርጋለን። በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ በፍቅር የምትሠራ እምነት እንጂ መገዘር አይጠቅምምና፤ አለመገዘርም ግዳጅ አይፈጽምምና። ቀድሞስ በመልካም ተፋጥናችሁ ነበር፤ በእውነት እንዳታምኑ ማን አሰናከላችሁ? ይህ መፋጠናችሁ ከሚጠራችሁ አይደለምና። ጥቂት እርሾ ብዙውን ዱቄት መጻጻ ያደርገው የለምን? እኔ ሌላ እንዳታስቡ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምኛችሁ ነበር፤ የሚያውካችሁ ግን የሆነው ቢሆን ፍዳውን ይሸከማል። ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ግዝረትን ገና የምሰብክ ከሆነ፥ እንግዲህ ለምን ያሳድዱኛል? እንግዲህ የክርስቶስ የመስቀሉ ተግዳሮት እንዲያው ቀርቶአል። የሚያውኩአችሁም ሊለዩ ይገባል። ወንድሞች ሆይ፥ እናንተስ ለነጻነት ተጠርታችኋል፤ ነገር ግን በሥጋችሁ ፈቃድ ለነጻነታችሁ ምክንያት አታድርጉላት፤ ለወንድሞቻችሁም በፍቅር ተገዙ። “ወንድምህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚለው አንድ ቃል ሕግን ሁሉ ይፈጽማልና። እርስ በርሳችሁ የምትበላሉና የምትነካከሱ ከሆነ ግን፥ እርስ በርሳችሁ እንዳትተላለቁ ተጠንቀቁ። እላችኋለሁ፤ በመንፈስ ኑሩ እንጂ የሥጋችሁን ፈቃድ አታድርጉ። ሥጋ መንፈስ የማይሻውን ይሻልና፥ መንፈስም ሥጋ የማይሻውን ይሻልና፥ የምትሹትንም እንዳታደርጉ እርስ በርሳቸው ይጣላሉ። የመንፈስን ፈቃድ የምትከተሉ ከሆናችሁ፥ ከኦሪት ወጥታችኋል። የሥጋም ሥራው ይታወቃል፤ እርሱም ዝሙት፥ ርኵሰት፥ መዳራት፥ ጣዖት ማምለክ፥ ሥራይ ማድረግ፥ መጣላት፥ ኵራት፥ የምንዝር ጌጥ፥ ቅናት፥ ቍጣ፥ ጥርጥር፥ ፉክክር፥ ምቀኝነት፥ መጋደል፥ ስካር ይህንም የመሰለ ሁሉ ነው። አስቀድሜ እንደ ነገርኋችሁ ይህን የሚያደርግ የእግዚአብሔርን መንግሥት አያይም። የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ምጽዋት፥ ቸርነት፥ እምነት፥ ገርነት፥ ንጽሕና ነው። ከዚህ ሕግ የሚበልጥ የለም። በኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑ ግን ሰውነታቸውን ከምኞትና ከኀጢአት ለዩ። አሁንም በመንፈስ እንኑር፤ በመንፈስም እንመላለስ። ኩሩዎች አንሁን፤ እርስ በርሳችን አንተማማ፤ እርስ በርሳችንም አንቀናና።
ወደ ገላትያ ሰዎች 5 ያንብቡ
ያዳምጡ ወደ ገላትያ ሰዎች 5
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ወደ ገላትያ ሰዎች 5:1-26
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች