የዳዊት ኀያላን ስም ይህ ነው። የሦስተኛው ክፍል አለቃ የሆነ ከነዓናዊው ኢያቡስቴ ነበረ፤ ጎራዴውን መዝዞ ስምንት መቶ ያህል ጭፍሮችን በአንድ ጊዜ የገደለ አሶናዊው አዲኖን ነበረ። ከእርሱም በኋላ የዳዊት የአጎቱ ልጅ የዱዲ ልጅ ኤልያናን ነበረ፤ ለሰልፍ የተሰበሰቡትን ፍልስጥኤማውያንን በተገዳደሩ ጊዜ ከዳዊት ጋር ከነበሩ ከሦስቱ ኀያላን አንዱ እርሱ ነበረ፤ የእስራኤልም ሰዎች ተመለሱ። የእስራኤልም ሰዎች በጮኹ ጊዜ እርሱ ተነሥቶ እጁ እስከሚደክምና ከሰይፉ ጋር እስኪጣበቅ ድረስ ፍልስጥኤማውያንን መታ፤ በዚያም ቀን እግዚአብሔር ታላቅ መድኀኒት አደረገ፤ ሕዝቡም ከእርሱ በኋላ የሞቱትን ለመግፈፍ ብቻ ተመለሱ። ከእርሱም በኋላ የአሮዳዊው የአጌ ልጅ ሴሜይ ነበረ። ፍልስጥኤማውያንም በቴሪያ ተሰበሰቡ። በዚያም ምስር የሞላበት የእርሻ ክፍል ነበር፤ ሕዝቡም ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ። እርሱ ግን በእርሻው መካከል ቆሞ ጠበቀ፤ ፍልስጥኤማውያንንም ገደለ፤ እግዚአብሔርም ታላቅ መድኀኒት አደረገ። ከሠላሳውም አለቆች ሦስቱ ወርደው ወደ ቃሶን ወደ ዳዊት ወደ አዶላም ዋሻ መጡ፤ የፍልስጥኤማውያንም ጭፍራ በራፋይም ሸለቆ ሰፍሮ ነበር። በዚያ ጊዜም ዳዊት በምሽጉ ውስጥ ነበረ፤ የፍልስጥኤማውያንም ጭፍራ በዚያ ጊዜ በቤተ ልሔም ነበረ። ዳዊትም፥ “በበሩ አጠገብ ካለችው ከቤተ ልሔም ምንጭ ውኃ ማን ባጠጣኝ?” ብሎ ተመኘ። ያንጊዜም የፍልስጥኤማውያን ኀይል በቤተ ልሔም ነበረ። ሦስቱም ኀያላን የፍልስጥኤማውያንን ሠራዊት ሰንጥቀው ሄዱ፤ በበሩም አጠገብ ካለችው ከቤተ ልሔም ምንጭ ውኃ ቀዱ፤ ይዘውም ለዳዊት አመጡለት፤ እርሱ ግን ሊጠጣ አልወደደም፤ ነገር ግን ለእግዚአብሔር አፈሰሰው። “አቤቱ፥ ይህን አደርግ ዘንድ ከእኔ ይራቅ፤ ነፍሳቸውን ሰጥተው የሄዱ ሰዎች ደም አይደለምን?” ብሎ ይጠጣ ዘንድ አልወደደም። ሦስቱ ኀያላንም ያደረጉት ይህ ነው። የሶርህያም ልጅ የኢዮአብ ወንድም አቢሳ የሦስቱ አለቃ ነበር። እርሱም ጦሩን በሦስቱ መቶ ላይ አንሥቶ ገደላቸው፤ ስሙም በሦስቱ ዘንድ ተጠርቶ ነበር። እርሱም ከሦስቱ ይልቅ የከበረ ነበር፤ አለቃቸውም ሆነ፤ ነገር ግን ወደ ሦስቱ አልደረሰም። በቀበስሄል የነበረው ታላቅ ሥራ ያደረገው የዮዳሄ ልጅ በናያስ የሞዓባዊውን የአርኤልን ሁለት ልጆች ገደለ፤ በአመዳዩም ወራት ወርዶ በጕድጓድ ውስጥ አንበሳ ገደለ። እርሱም ልዩ የሆነውን ግብፃዊ ሰው ገደለ፤ ግብፃዊውም በእጁ ዛቢያው እንደ ድልድይ ዕንጨት የሆነ ጦር ነበረው፤ በናያስ ግን በትር ይዞ ወደ እርሱ ወረደ፤ ከግብፃዊውም እጅ ጦሩን ነጥቆ በገዛ ጦሩ ገደለው። የዮዳሄ ልጅ በናያስ ያደረገው ይህ ነው፤ ስሙም በሦስቱ ኀያላን ተጠርቶ ነበር። ከሦስቱም ይልቅ የከበረ ነበረ፤ ነገር ግን ወደ ሦስቱ አልደረሰም። ዳዊትም ትእዛዝ አስከባሪ አድርጎ ሾመው። የዳዊት ኀያላንም ስማቸው ይህ ነው። የኢዮአብ ወንድም አሣሄል በሠላሳው መካከል ነበረ፤ የቤተ ልሔም ሰው የአጎቱ የዱዲ ልጅ ኤልያናን፥ አሮዳዊው ሴሜይ፥ ሔሮዳዊው አልያቃ፥ ፈልጣዊው ሴሌ፥ የቴቁሓዊው የኤስካ ልጅ ዔራስ፥ ከአስቲጡ ልጆች ወገን የሚሆን አናቶታዊው አብዔዜር፥ የኤሎንያ ሰው ኤላን፥ የፋጤ ሰው ናኤሬት፥ የአንጢፋ ሰው የቦአና ልጅ ሔሌብ፥ ከብንያም ወገን ከጌብዓ የረባይ ልጅ ኢታይ፥ ኤፍራታዊው በናያስ፥ የአብሪስ ሰው አሶም፥ ዓረባዊው አቤዔልቦን፥ አልሞናዊው ኤማሱኖስ፥ አሴሌቦናዊው ኤልያሕባ፥ የአሶን ልጅ ዮናታን፥ አሮዳዊው ሳምናን፥ የሓተራዊው የሶሬ ልጅ አምናን፥ የመካኪ ልጅ የአሶብ ልጅ ኤላፍላት፥ የጊሎናዊው የአኪጦፌል ልጅ ኤልያብ፥ ቀርሜሎሳዊው አሰሬ፥ አረባዊው ኤፌዎ፥ የናታን ልጅ ኤአኪ፥ ከገዓድ ልጆች ወገን ማሶባ፥ አሞናዊው ኤልዩ፥ የሶርህያ ልጅ የኢዮአብ ጋሻ ጃግሬ ቤሮታዊው ጌሎሬ፥ ኤተራዊው ዒራስ፥ ኢታናዊው ጋሬብ፥ ኬጤያዊው ኦርዮ፤ ሁሉም በሁሉ ሠላሳ ሰባት ናቸው።
መጽሐፈ ሳሙኤል ካልእ 23 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ሳሙኤል ካልእ 23:8-39
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች