2 ሳሙኤል 23:8-39

2 ሳሙኤል 23:8-39 NASV

የዳዊት ኀያላን ሰዎች ስም ይህ ነው፤ የታሕክሞን ሰው ዮሴብ በሴትቤት የሦስቱ አለቆች አለቃ ሲሆን፣ እርሱም ጦሩን ሰብቆ በአንድ ውጊያ ላይ ስምንት መቶ ሰው የገደለ ነው። ከርሱ ቀጥሎ የአሆሃዊው የዱዲ ልጅ ኤልዔዘር ነበረ፤ እርሱም ለጦርነት አንድ ላይ ተሰብስበው የነበሩትን ፍልስጥኤማውያንን በተገዳደሩ ጊዜ፣ ከዳዊት ጋራ ከነበሩት ከሦስቱ ኀያላን ሰዎች አንዱ ነበር። ከዚያም የእስራኤል ሰዎች ሸሹ። እርሱ ግን የቆመበትን ስፍራ አልለቀቀም፤ እጁ እስኪዝልና ከሰይፉ ጋራ እስኪጣበቅ ድረስ ፍልስጥኤማውያንን ወጋ፤ በዚያችም ዕለት እግዚአብሔር ታላቅ ድልን ሰጠ። የሸሸውም ሰራዊት ወደ ኤልዔዘር የተመለሰው የተገደሉትን ሰዎች ለመግፈፍ ብቻ ነበር። ከርሱም ቀጥሎ የሃራራዊው የአጌ ልጅ ሣማ ነበር፤ ፍልስጥኤማውያንም ሌሒ በተባለ ስፍራ ምስር በሞላበት አንድ ዕርሻ ላይ በአንድነት ተሰብስበው ሳሉ፣ የእስራኤል ሰራዊት ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፤ ሣማ ግን የቆመበትን ስፍራ አልለቀቀም፤ ጦርነቱንም ተቋቁሞ ፍልስጥኤማውያንን ገደለ፤ በዚያችም ዕለት እግዚአብሔር ታላቅ ድል ሰጣቸው። በመከር ወራት፣ የፍልስጥኤም ሰራዊት በራፋይም ሸለቆ ሰፍሮ ሳለ፣ ከሠላሳዎቹ አለቆች ሦስቱ ዳዊት ወዳለበት ወደ ዓዶላም ዋሻ መጡ። በዚያ ጊዜ ዳዊት በምሽግ ውስጥ ነበረ፤ የፍልስጥኤማውያንም ሰራዊት በቤተ ልሔም ነበረ፤ ዳዊትም በናፍቆት፣ “በቤተ ልሔም በር አጠገብ ካለችው ጕድጓድ ውሃ ማን ባመጣልኝ!” አለ። ስለዚህ ሦስቱ ኀያላን በፍልስጥኤማውያን ሰራዊት መካከል ሰንጥቀው በማለፍ፣ በቤተ ልሔም በር አጠገብ ካለችው ጕድጓድ ውሃ ቀድተው ለዳዊት አመጡለት። እርሱ ግን አልጠጣውም፤ ይልቁን በእግዚአብሔር ፊት መሥዋዕት አድርጎ አፈሰሰው፤ “እርሱም፣ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንዲህ ያለውን ነገር ላደርግ? ይህስ ከእኔ ይራቅ! ይህ በነፍሳቸው ቈርጠው የሄዱ ሰዎች ደም አይደለምን?” አለ፤ ዳዊትም ሊጠጣው አልፈለገም። እንግዲህ ሦስቱ ኀያላን ሰዎች ያደረጉት ጀብዱ እንዲህ ነበር። የጽሩያ ልጅ የኢዮአብ ወንድም አቢሳ የሦስቱ ኀያላን አለቃ ነበረ። በሦስት መቶ ሰዎች ላይ ጦሩን ሰብቆ የገደላቸውና እንደ ሦስቱ ኀያላን ሁሉ እርሱም ዝናን ያተረፈ ሰው ነበረ። አቢሳ ከሦስቱ ይልቅ እጅግ የከበረ አልነበረምን? ከእነርሱ እንደ አንዱ ባይሆንም አለቃቸው ነበረ። የቀብጽኤል አገር ሰው የሆነው የዮዳሄ ልጅ በናያስ ታላቅ ጀብዱ የሠራ ሌላው ጐበዝ ተዋጊ ነበረ፤ እርሱም ሁለት በጣም የታወቁ የሞዓብ ሰዎችን ገደለ፤ እንዲሁም በረዶ በጣለበት ዕለት በጕድጓድ ውስጥ ገብቶ አንበሳ ገድሏል፤ ደግሞም አንድ ግዙፍ ግብጻዊ ገድሏል፤ ግብጻዊው በእጁ ጦር የያዘ ቢሆንም፣ በናያስ ግን ሊገጥመው በትር ይዞ ወደ እርሱ ሄደ፤ ከግብጻዊውም እጅ ጦሩን ነጥቆ በገዛ ጦሩ ገደለው። የዮዳሄ ልጅ የበናያስ ጀብዱ እንደዚህ ያለ ነበረ፤ እርሱም እንደ ሦስቱ ኀያላን ሁሉ ዝናን ያተረፈ ሲሆን፣ ከሠላሳዎቹ ሁሉ በላይ የከበረ ሰው ነበረ፤ ነገር ግን ከሦስቱ እንደ አንዱ አልነበረም። ዳዊትም የክብር ዘበኞቹ አለቃ አድርጎ ሾመው። ከሠላሳዎቹ መካከል የሚከተሉት ይገኙባቸዋል፤ የኢዮአብ ወንድም አሣሄል፣ የቤተ ልሔሙ ሰው የዱዲ ልጅ ኤልያናን፣ አሮዳዊው ሣማ፣ አሮዳዊው ኤሊቃ፣ ፈሊጣዊው ሴሌስ፣ የቴቁሐዊው የዒስካ ልጅ ዒራስ፣ የዓናቶቱ ሰው አቢዔዜር፤ ኩሳታዊው ምቡናይ፣ አሆሃዊው ጸልሞን፣ ነጦፋዊው ማህራይ፣ የነጦፋዊው የበዓና ልጅ ሔሌብ፣ ከብንያም ወገን የጊብዓ ሰው የሆነው የሪባይ ልጅ ኢታይ፣ ጲርዓቶናዊው በናያስ፣ የገዓስ ሸለቆ ሰው ሂዳይ፣ ዐረባዊው አቢዓልቦን፣ በርሑማዊው ዓዝሞት፣ ሸዓልቦናዊው ኤሊያሕባ፣ የአሳን ልጆች፤ ዮናታን የተባለው፣ የሃራራዊው የሣማ ልጅ፣ የሃራራዊው የሻራር ልጅ አሒአም፤ የማዕካታዊው የአሐስባይ ልጅ ኤሌፋላት፣ የጊሎናዊው የአኪጦፌል ልጅ ኤሊአም፣ ቀርሜሎሳዊው ሐጽሮ፤ አርባዊው ፈዓራይ፣ የሱባ ሰው የሆነው የናታን ልጅ ይግአል፣ ጋዳዊው ባኒ፣ አሞናዊው ጼሌቅ፣ የጽሩያ ልጅ የኢዮአብ ጦር መሣሪያ ያዥ የነበረው ብኤሮታዊው ነሃራይ፣ ይትራዊው ዒራስ፣ ይትራዊው ጋሬብ፣ እንዲሁም ኬጢያዊው ኦርዮ።