ለኢዮአብ፥ “ንጉሡ ስለ አቤሴሎም ያዝናል፤ ያለቅሳልም” ብለው ነገሩት። በዚያም ቀን፥ “ንጉሡ ስለ ልጁ አዘነ” ሲባል ሕዝቡ ሰምቶአልና በዚያው ቀን ሕይወት በሕዝቡ ሁሉ ዘንድ ወደ ኀዘን ተለወጠ። ከሰልፍ በሸሸ ጊዜ ያፈረ ሕዝብ ተሰርቆ እንደሚገባ በዚያ ቀን ሕዝቡ ተሰርቀው ወደ ከተማ ገቡ። ንጉሡም ፊቱን ሸፈነ፤ ንጉሡም በታላቅ ድምፅ፥ “ልጄ አቤሴሎም፥ አቤሴሎም፥ ልጄ” እያለ ይጮህ ነበር። ኢዮአብም ወደ ንጉሡ ወደ ቤት ገብቶ እንዲህ አለ፥ “ዛሬ ነፍስህንና የወንዶችንና የሴቶች ልጆችህን ነፍስ፥ የሚስቶችህንና የቁባቶችህን ነፍስ ያዳኑትን የአገልጋዮችህን ሁሉ ፊት በዚች ቀን አሳፍረሃል። አንተ የሚጠሉህን ትወድዳለህ፤ የሚወድዱህንም ትጠላለህ፤ አለቆችህና አገልጋዮችህ እንደማይጠቅሙህ እንደምታስብ ዛሬ ገልጠሃልና፤ አቤሴሎምም ድኖ ቢሆን ዛሬ እኛ ሁላችን እንሞት እንደ ነበር አውቃለሁ። ይህ በፊትህ ላንተ ቀና ነበረና። አሁንም ተነሥተህ ወጥተህ ለአገልጋዮችህ በልባቸው የሚገባ ነገር ንገራቸው። ዛሬ ወደ እነርሱ ካልወጣህ በዚች ሌሊት አንድ ሰው ስንኳ ከአንተ ጋር የሚያድር እንዳይኖር በእግዚአብሔር እምላለሁ፤ ከሕፃንነትህ ጀምሮ እስከዚች ቀን ድረስ ካገኘህ መከራ ሁሉ ዛሬ የምታገኝህ መከራ እንድትከፋብህ እንግዲህ አንተ ለራስህ ዕወቅ” አለው። ንጉሡም ተነሥቶ በበሩ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም ሁሉ ንጉሡ በበሩ ተቀምጧል ብለው ተናገሩ፤ ሕዝቡም ሁሉ በበሩ ወደ ንጉሡ ፊት ወጡ። እስራኤልም እያንዳንዱ ወደ ድንኳኑ ሸሽቶ ገብቶ ነበር። ከመላው ነገደ እስራኤል የተሰበሰቡ ሕዝብ፥ “ንጉሡ ዳዊት ከጠላቶቻችን እጅ ታድጎናል፥ ከፍልስጥኤማውያንም እጅ አድኖናል፤ አሁንም ስለ አቤሴሎም ከሀገሩና ከመንግሥቱ ሸሸ። በላያችን ላይ የቀባነው አቤሴሎምም በጦርነት ሞቶአል፤ አሁንም ንጉሡን ለመመለስ ስለምን ዝም ትላላችሁ?” አሉ፤ የእስራኤልም ቃል ወደ ንጉሥ ደረሰ። ንጉሡ ዳዊትም ለካህናቱ ለሳዶቅና ለአብያታር ልኮ እንዲህ አላቸው፥ “ለይሁዳ ሽማግሌዎች እንዲህ ብላችሁ ተናገሩአቸው፦ የእስራኤል ሁሉ ነገር ወደ ንጉሡ ደርሶአልና ንጉሡን ወደ ቤቱ ከመመለስ ስለምን ዘገያችሁ? እናንተ ወንድሞች፥ የአጥንቴ ፍላጭና የሥጋዬ ቍራጭ ናችሁ፤ እናንተ ንጉሡን ወደ ቤቱ ከመመለስ ስለምን ዘገያችሁ? ለአሚሳይም፦ አንተ የአጥንቴ ፍላጭና የሥጋዬ ቍራጭ አይደለህምን? በዘመንህም ሁሉ በኢዮአብ ፋንታ በፊቴ የሠራዊት አለቃ ሳትሆን ብትቀር ዛሬ እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ፤ ይህንም ይጨምርብኝ በሉት።” የይሁዳንም ሰዎች ሁሉ ልብ እንደ አንድ ሰው ልብ አድርጎ አዘነበለ፤ ወደ ንጉሡም፥ “አንተና ብላቴኖችህ፥ አገልጋዮችህም ሁሉ ተመለሱ” ብለው ላኩበት። ንጉሡም ተመልሶ እስከ ዮርዳኖስ ድረስ መጣ። የይሁዳ ሰዎችም ንጉሡን ሊቀበሉ፥ ንጉሡንም ዮርዳኖስን ሊያሻግሩ ወደ ጌልገላ መጡ። ከባውሪም ሀገር የነበረው የኢያሚን ልጅ የጌራ ልጅ ሳሚም ከይሁዳ ሰዎች ጋር ንጉሥ ዳዊትን ሊቀበል ፈጥኖ ወረደ። ከእርሱም ጋራ ከብንያም ወገን የሆኑ ሺህ ሰዎች ነበሩ፤ የሳኦልም ቤት አገልጋይ ሲባ ከእርሱም ጋር ዐሥራ አምስቱ ልጆቹና ሃያው አገልጋዮቹ ነበሩ፤ በንጉሡም ፊት በቀጥታ ወደ ዮርዳኖስ ሄዱ። ንጉሡንም የማሻገር ሥራ ሠሩ። የንጉሡንም ቤተ ሰብእ ያነሡ ዘንድ፥ በፊቱም የቀና ሥራን ይሠሩ ዘንድ ወደ ማዶ ተሻገሩ። ንጉሡም ዮርዳኖስን ከተሻገረ በኋላ የጌራ ልጅ ሳሚ በንጉሡ ፊት፦ በግንባሩ ወደቀ። እርሱም ንጉሡን አለው፥ “ጌታዬ! ኀጢአቴን አትቍጠርብኝ፤ ጌታዬ ንጉሡ ከኢየሩሳሌም በወጣህ ቀን ባሪያህ የበደልሁህን አታስብብኝ፤ ጌታዬ ንጉሡም በልብህ አታኑርብኝ። እኔ አገልጋይህ በደለኛ እንደ ሆንሁ አውቄአለሁና እነሆ፥ ከዮሴፍ ቤት ሁሉ አስቀድሜ ዛሬ መጣሁ፤ ጌታዬንም ንጉሡን ልቀበል ወረድሁ።” የሶርህያ ልጅ አቢሳ ግን፥ “ሳሚ እግዚአብሔር የቀባውን ሰድቦአልና እንግዲህ ሞት የተገባው አይደለምን?” ብሎ መለሰ። ዳዊትም፥ “እናንተ የሶርህያ ልጆች! ዛሬ ታስቱኝ ዘንድ በእኔና በእናንተ መካከል ምን አለኝ? ዛሬስ ከእስራኤል የሚሞት አንድ ሰው የለም። ዛሬስ በእስራኤል ላይ እንደ ነገሥሁ አላውቅምን?” ንጉሡም ሳሚን፥ “አትሞትም” አለው። ንጉሡም ማለለት።
መጽሐፈ ሳሙኤል ካልእ 19 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ሳሙኤል ካልእ 19:1-23
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች