የአሦርም ንጉሥ ከባቢሎንና ከኩታ፥ ከአዋና ከሐማት፥ ከሴፌርዋይም ሰዎችን አመጣ፤ በእስራኤልም ልጆች ፋንታ በሰማርያ ከተሞች አኖራቸው፤ ሰማርያንም ወረሱአት፤ በከተሞችዋም ተቀመጡ። በዚያም መቀመጥ በጀመሩ ጊዜ እግዚአብሔርን አይፈሩትም ነበር፤ እግዚአብሔርም አንበሶችን ሰደደባቸው፤ ይገድሉአቸውም ነበር። ስለዚህም ለአሦር ንጉሥ፥ “ያፈለስኻቸው፥ በሰማርያም ከተሞች ያኖርኻቸው ሕዝቦች የሀገሩን አምላክ ሕግ አላወቁም፤ የሀገሩን አምላክ ሕግ አላወቁምና አንበሶችን ሰድዶባቸዋል፤ እነሆም፥ እየገደሉአቸው ነው” ብለው ተናገሩት። የአሦርም ንጉሥ፥ “ከዚያ ካመጣኋቸው ካህናት አንዱን ውሰዱ፤ ሄዶም በዚያ ይቀመጥ፤ የሀገሩንም አምላክ ሕግ ያስተምራቸው” ብሎ አዘዘ። ከሰማርያም ካፈለሱአቸው ካህናት አንዱን ወስደው በቤቴል አኖሩት፤ ያም ካህን እግዚአብሔርን እንዴት እንደሚፈሩት ያስተምራቸው ነበር። በየሕዝባቸውም አምላኮቻቸውን አደረጉ፤ ሳምራውያንም በሠሯቸው በኮረብታው መስገጃዎች ሕዝቡ ሁሉ በሚኖሩባቸው ከተሞቻቸው አኖሩአቸው። የባቢሎንም ሰዎች ሴኬቤቴናሆምን ሠሩ፤ የኩታም ሰዎች ኤርጌትን ሠሩ፤ የሐማትም ሰዎች አሲማትን ሠሩ፤ አዋውያንም ኤልባዝርንና ተርታቅን ሠሩ፤ የሴፌርዋይም ሰዎች ለሴፌርዋይም አማልክት ለአድራሜሌክና ለአኔሜሌክ ልጆቻቸውን በእሳት ይሠዉ ነበር። እግዚአብሔርንም ይፈሩ ነበር፤ ሕዝቡም ሁሉ በሚኖሩበት ከተማ በሰማርያ በሠሩት በከፍታው ቦታ ጣዖቶቻቸውን አኖሩ። እግዚአብሔርንም ይፈሩ ነበር፤ ከመካከላቸውም ለኮረብታው መስገጃዎች ካህናትን አደረጉ፤ በኮረብታውም መስገጃዎች ይሠዉ ነበር። እግዚአብሔርንም ሲፈሩ ከመካከላቸው እንደ ፈለሱት እንደ አሕዛብ ልማድ አምላካቸውን ያመልኩ ነበር። እስከ ዛሬም ድረስ እንደ ልማዳቸው ያደርጋሉ፤ እግዚአብሔርንም ይፈራሉ፤ እግዚአብሔርም እስራኤል ብሎ የጠራውን የያዕቆብን ልጆች እንዳዘዛቸው ሥርዐትና ፍርድ፥ ሕግና ትእዛዝም ያደርጋሉ። እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፤ እንዲህም ብሎ አዘዛቸው፥ “ሌሎችን አማልክት አትፍሩአቸው፤ አትስገዱላቸውም፤ አታምልኩአቸውም፤ አትሠዉላቸውም። ነገር ግን በታላቅ ኀይል በተዘረጋችም ክንድ ከግብፅ ምድር ያወጣችሁን እግዚአብሔርን እርሱን ፍሩ፤ ለእርሱም ስገዱ፤ ለእርሱም ሠዉ። የጻፈላችሁንም ሥርዐትና ፍርድ፥ ሕግና ትእዛዝም ለዘለዓለም ታደርጉ ዘንድ ጠብቁ፤ ሌሎችንም አማልክት አትፍሩ። ከእናንተም ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን አትርሱ፤ ሌሎችንም አማልክት አትፍሩ። ነገር ግን አምላካችሁን እግዚአብሔርን ፍሩ፤ እርሱም ከጠላቶቻቸሁ ሁሉ እጅ ያድናችኋል። ነገር ግን እነርሱ እንደሚያደርጉት ልማዳቸውን አትስሙ። እነዚህም አሕዛብ እግዚአብሔርን ይፈሩ ነበር፤ ደግሞም የተቀረጹ ምስሎቻቸውን ያመልኩ ነበር፤ ልጆቻቸውም፥ የልጅ ልጆቻቸውም አባቶቻቸው እንዳደረጉ እስከ ዛሬ ድረስ እንዲሁ ያደርጋሉ።”
መጽሐፈ ነገሥት ካልእ 17 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ነገሥት ካልእ 17:24-41
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች