አክዓብም ከሞተ በኋላ ሞዓብ በእስራኤል ላይ ዐመፀ። አካዝያስም በሰማርያ በሰገነቱ ላይ ሳለ በዐይነ ርግቡ ወድቆ ታመመ፤ እርሱም፥ “ሂዱ፥ ከዚህ ደዌ እድን እንደ ሆነ የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ጠይቁ” ብሎ መልእክተኞችን ላከ፤ እነርሱም ሊጠይቁለት ሄዱ። የእግዚአብሔርም መልአክ ቴስብያዊውን ኤልያስን ጠርቶ፥ “ተነሣ፤ የሰማርያን ንጉሥ መልእክተኞች ለመገናኘት ሂድና፦ የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ትጠይቁ ዘንድ የምትሄዱት በእስራኤል ዘንድ አምላክ ስለሌለ ነውን? ነገሩ እንዲህ አይደለም፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ትሞታለህ እንጂ ከወጣህበት አልጋ አትወርድም በላቸው” አለው። ኤልያስም ሄደ፤ እንዲሁም ነገራቸው። መልእክተኞቹም ወደ አካዝያስ ተመለሱ፤ እርሱም፥ “ለምን ተመለሳችሁ?” አላቸው። እነርሱም፥ “አንድ ሰው ሊገናኘን መጣና፦ ሂዱ፤ ወደ ላካችሁ ንጉሥ ተመልሳችሁ፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ትጠይቅ ዘንድ የላክህ በእስራኤል ዘንድ አምላክ ስለሌለ ነውን? ስለዚህ ትሞታለህ እንጂ ከወጣህበት አልጋ አትወርድም በሉት አለን” አሉት። እርሱም፥ “ሊገናኛችሁ የወጣው፦ ይህንስ ቃል የነገራችሁ ሰው መልኩ ምን ይመስላል?” አላቸው። እነርሱም፥ “ሰውዬው ጠጕራም ነው፤ በወገቡም ጠፍር ታጥቆ ነበር” አሉት። እርሱም፥ “ቴስብያዊው ኤልያስ ነው” አላቸው። ንጉሡም ይጠሩት ዘንድ የአምሳ አለቃውን ከአምሳ ሰዎች ጋር ወደ እርሱ ላከ፤ ወደ እርሱም ሄዱ፤ እነሆም፥ በተራራ ራስ ላይ ተቀምጦ አገኙት። የአምሳ አለቃውም፥ “የእግዚአብሔር ሰው ሆይ! ንጉሡ ይጠራሃል ፈጥነህ ና፤ ውረድ” አለው። ኤልያስም መልሶ የአምሳ አለቃውን፥ “እኔስ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ሆንሁ እሳት ከሰማይ ትውረድ፤ አንተንም፥ አምሳውንም ሰዎችህን ትብላ” አለው። እሳትም ከሰማይ ወርዳ እርሱንና አምሳውን ሰዎች በላች። ደግሞም ሌላ የአምሳ አለቃ ከአምሳ ሰዎች ጋር ላከበት፤ የአምሳ አለቃውም፥ “የእግዚአብሔር ሰው ሆይ! ንጉሡ፦ ና፤ ፈጥነህ ውረድ ይላል” ብሎ ተናገረ። ኤልያስም፥ “እኔስ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ሆንሁ እሳት ከሰማይ ትውረድ፤ አንተንም፥ አምሳውንም ሰዎችህን ትብላ” አለው። እሳትም ከሰማይ ወርዳ እርሱንና አምሳውን ሰዎች በላች። ንጉሡም ደግሞ ሦስተኛ የአምሳ አለቃ ከአምሳ ሰዎች ጋር ላከ፤ ሦስተኛውም የአምሳ አለቃ ወጥቶ በኤልያስ ፊት በጕልበቱ ተንበረከከና ለመነው እንዲህም አለው፥ “የእግዚአብሔር ሰው ሆይ! ሰውነቴና የእነዚህ የአምሳው ባሪያዎችህ ሰውነት በፊትህ የከበረች ትሁን። እነሆ፥ እሳት ከሰማይ ወርዳ የፊተኞቹን ሁለቱን የአምሳ አለቆችና አምሳ አምሳውን ሰዎቻቸውን በላች፤ አሁን ግን ነፍሴ በፊትህ የከበረች ትሁን።” የእግዚአብሔርም መልአክ ኤልያስን፥ “ከእርሱ ጋር ውረድ፤ ከፊታቸውም የተነሣ አትፍራ” ብሎ ነገረው። ኤልያስም ተነሥቶ ከእርሱ ጋር ወደ ንጉሡ ወረደ።
መጽሐፈ ነገሥት ካልእ 1 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ነገሥት ካልእ 1:1-15
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች