አክዓብ ከሞተ በኋላ ሞዓብ በእስራኤል ላይ ዐመፀ። በዚህ ጊዜ አካዝያስ በሰማርያ ካለው እልፍኝ ሰገነቱ ላይ ሳለ፣ ከዐይነ ርግቡ ሾልኮ ወድቆ ነበርና ታመመ፤ ስለዚህ፣ “ሄዳችሁ ከዚህ ሕመም እድን እንደ ሆነ የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ጠይቁ” ሲል መልእክተኞች ላከ። የእግዚአብሔር መልአክ ግን ቴስብያዊውን ኤልያስን እንዲህ አለው፤ “ተነሥተህ የሰማርያን ንጉሥ መልእክተኞች ለመገናኘት ውጣና፣ ‘የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ለመጠየቅ የምትሄዱ በእስራኤል አምላክ ስለሌለ ነውን?’ ብለህ ጠይቃቸው። ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ከተኛህበት ዐልጋ አትነሣም፤ በርግጥ ትሞታለህ።’ ” ከዚያም ኤልያስ ሄደ። መልእክተኞቹ ወደ ንጉሡ ሲመለሱ እርሱም፣ “ለምን ተመልሳችሁ መጣችሁ?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም እንዲህ ሲሉ መለሱለት፤ “አንድ ሰው ሊገናኘን መጥቶ፣ ‘ወደ ላካችሁ ንጉሥ ተመልሳችሁ ሂዱና፣ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ የአቃሮንን አምላክ ብዔልዜቡልን ለመጠየቅ ሰዎች የምትልከው በእስራኤል አምላክ ስለሌለ ነውን? ስለዚህ ከተኛህበት ዐልጋ አትነሣም፤ በርግጥ ትሞታለህ።” ’ ” ንጉሡም፣ “ለመሆኑ ሊገናኛችሁ መጥቶ እንዲህ ያላችሁ ሰው እንዴት ያለ ነው?” ሲል ጠየቃቸው። እነርሱም “ሰውየው ጠጕራም፣ በወገቡም ጠፍር ታጥቆ ነበር” አሉት። ንጉሡም፣ “ዐወቅሁት፤ ቴስብያዊው ኤልያስ ነው” አላቸው። ከዚያም ንጉሡ አንድ የዐምሳ አለቃ ከዐምሳ ወታደሮቹ ጋራ ወደ ኤልያስ ላከ። የዐምሳ አለቃውም ኤልያስ ወደ ተቀመጠበት ኰረብታ ጫፍ ወጥቶ፣ “አንተ የእግዚአብሔር ሰው፤ ንጉሡ፣ ‘ና ውረድ’ ይልሃል” አለው። ኤልያስም መልሶ የዐምሳ አለቃውን፣ “እኔ የእግዚአብሔር ሰው ከሆንሁ፣ እሳት ከሰማይ ወርዳ፣ አንተንና ዐምሳውን ሰዎችህን ትብላ!” አለው። ከዚያም እሳት ከሰማይ ወርዳ የዐምሳ አለቃውንና ሰዎቹን ፈጽማ በላች። እንደ ገናም ንጉሡ ሌላ የዐምሳ አለቃ ከዐምሳ ሰዎቹ ጋራ ላከ፤ የዐምሳ አለቃውም፣ “አንተ የእግዚአብሔር ሰው፤ ንጉሡ፣ ‘አሁኑኑ ና ውረድ’ ይልሃል” አለው። ኤልያስም መልሶ፣ “እኔ የእግዚአብሔር ሰው ከሆንሁ እሳት ከሰማይ ወርዳ አንተንና ኀምሳውን ሰዎችህን ትብላ!” አለው፤ ከዚያም እሳት ከሰማይ ወርዳ እርሱንና ሰዎቹን ፈጽማ በላች። ስለዚህም ንጉሡ ሦስተኛውን የዐምሳ አለቃ ከዐምሳ ሰዎቹ ጋራ ላከ። ይህም ሦስተኛው የዐምሳ አለቃ ወጥቶ፣ በኤልያስ ፊት በጕልበቱ ተንበርክኮ እንዲህ ሲል ለመነ፤ “አንተ የእግዚአብሔር ሰው፤ እባክህ የእኔና የእነዚህ የዐምሳዎቹ አገልጋዮችህ ነፍስ በፊትህ የከበረች ትሁን። እነሆ፤ እሳት ከሰማይ ወርዳ፣ የፊተኞቹን ሁለት ዐምሳ አለቆችና ሰዎቻቸውን ሁሉ በላች፤ አሁን ግን ሕይወቴ በፊትህ የከበረች ትሁን።” የእግዚአብሔርም መልአክ ኤልያስን፣ “ዐብረኸው ውረድ፤ ደግሞም አትፍራው” አለው። ስለዚህ ኤልያስ ተነሣ፤ ዐብሮትም ወደ ንጉሡ ወረደ።
2 ነገሥት 1 ያንብቡ
ያዳምጡ 2 ነገሥት 1
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 2 ነገሥት 1:1-15
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች