መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 10
10
ዐሥሩ ነገደ እስራኤል እንደ ዐመፁ
(1ነገ. 12፥1-20)
1እስራኤልም ሁሉ ያነግሡት ዘንድ ወደ ሴኬም መጥተው ነበርና ሮብዓም ወደ ሴኬም ሄደ። 2የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓምም ከንጉሡ ከሰሎሞን ፊት ሸሽቶ በግብፅ ይኖር ነበርና ይህን በሰማ ጊዜ ኢዮርብዓም ከግብፅ ተመለሰ። 3ልከውም ጠሩት፤ ኢዮርብዓምና እስራኤልም ሁሉ ወደ ሮብዓም መጥተው እንዲህ አሉት፦ 4“አባትህ ቀንበር አክብዶብን ነበር፤ አሁንም አንተ ጽኑውን የአባትህን አገዛዝ፥ በላያችንም የጫነውን የከበደውን ቀንበር አቅልልልን፥ እኛም እንገዛልሃለን።” 5እርሱም፥ “ሂዱ ከሦስት ቀን በኋላ ወደ እኔ ተመለሱ” አላቸው። ሕዝቡም ሄዱ።
6ንጉሡም ሮብዓም፥ “ለዚህ ሕዝብ እመልስለት ዘንድ የምትመክሩኝ ምንድን ነው?” ብሎ አባቱ ሰሎሞን በሕይወት ሳለ በፊቱ ይቆሙ የነበሩትን ሽማግሌዎች ሰበሰበ። 7እነርሱም፥ “በዚች ዕለት ለዚህ ሕዝብ ቸርነት ብታደርግላቸው፥ ደስም ብታሰኛቸው፥ መልካም ነገርንም ብትናገራቸው፥ ሁልጊዜ አገልጋዮች ይሆኑልሃል” ብለው ተናገሩት። 8እርሱ ግን ሽማግሌዎች የመከሩትን ነገር ትቶ ከእርሱ ጋር ካደጉትና በፊቱ ይቆሙ ከነበሩት ብላቴኖች ጋር ተማከረ። 9እርሱም፥ “አባትህ የጫነብንን ቀንበር አቅልልልን ለሚሉኝ ሕዝብ እመልስላቸው ዘንድ የምትመክሩኝ ምንድን ነው?” አላቸው። 10ከእርሱም ጋር ያደጉት ብላቴኖች፥ “አባትህ ቀንበር አክብዶብን ነበር፤ አንተ ግን አቅልልልን ለሚሉህ ሕዝብ፦ ታናሺቱ ጣቴ ከአባቴ ወገብ ትወፍራለች፤ 11አሁንም አባቴ ከባድ ቀንበር ጭኖባችሁ ነበር፤ እኔ ግን በቀንበራችሁ ላይ እጨምራለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችሁ ነበር፤ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ በላቸው” ብለው ነገሩት።
12ንጉሡም፥ “በሦስተኛው ቀን ወደ እኔ ተመለሱ” ብሎ እንደ ተናገረ ኢዮርብዓምና ሕዝቡ ሁሉ በሦስተኛው ቀን ወደ ሮብዓም መጡ። 13ንጉሡም ጽኑ ምላሽ መለሰላቸው፤ ንጉሡም ሮብዓም የሽማግሌዎቹን ምክር ትቶ፦ 14“አባቴ ቀንበር አክብዶባችሁ ነበር፤ እኔ ግን እጨምርበታለሁ፤ አባቴ በአለንጋ ገርፎአችሁ ነበር፤ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ” ብሎ እንደ ብላቴኖቹ ምክር ተናገራቸው። 15እግዚአብሔርም በሴሎናዊው በአኪያ ቃል ስለ ናባጥ ልጅ ስለ ኢዮርብዓም የተናገረውን ቃሉን እንዲያጸና ለውጡ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነበርና ንጉሡ ሕዝቡን አልሰማም።
16ንጉሡ ስላልሰማቸው ሕዝቡ፥ “በዳዊት ዘንድ ምን ክፍል አለን? በእሴይም ልጅ ዘንድ ምን ርስት አለን? እስራኤል ሆይ፥ ወደ እየድንኳኖቻችሁ ተመለሱ፤ ዳዊት ሆይ፥ አሁን ቤትህን ተመልከት” ብለው ለንጉሡ መለሱለት። እስራኤልም ሁሉ ወደ እየድንኳኖቻቸው ሄዱ። 17በይሁዳ ከተሞች የተቀመጡት የእስራኤል ሰዎች ግን ሮብዓምን በላያቸው አነገሡ። 18ንጉሡም ሮብዓም አስገባሪውን አዶራምን ወደ እነርሱ ላከው፤ የእስራኤልም ልጆች በድንጋይ ወገሩት፤ ሞተም፤ ንጉሡም ሮብዓም ፈጥኖ ወደ ሰረገላው ወጣ፤ ወደ ኢየሩሳሌምም ሸሸ። 19እስራኤልም እስከ ዛሬ ድረስ ከዳዊት ቤት ሸፈተ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 10: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ