መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 11
11
የሰማያ የትንቢት ቃል
(1ነገ. 12፥21-24)
1ሮብዓምም ወደ ኢየሩሳሌም በመጣ ጊዜ እስራኤልን ወግተው መንግሥቱን ወደ ሮብዓም ይመልሱ ዘንድ ከይሁዳና ከብንያም ቤት የተመረጡትን አንድ መቶ ሰማንያ ሺህ ሰልፈኞች ጐልማሶችን ሰበሰበ። 2የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እግዚአብሔር ሰው ወደ ሰማያ እንዲህ ሲል መጣ፦ 3“ለይሁዳ ንጉሥ ለሰሎሞን ልጅ ለሮብዓም፥ በይሁዳና በብንያምም ላሉት ለእስራኤል ሁሉ፦#“ለእስራኤል ሁሉ” የሚለው በዕብ. ብቻ። 4‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ይህ ነገር ከእኔ ዘንድ ነውና አትውጡ፤ ወንድሞቻችሁንም አትውጉ፤ እያንዳንዱም ወደ ቤቱ ይመለስ’ ብለህ ንገራቸው።” የእግዚአብሔርንም ቃል ሰሙ፤ በኢዮርብዓምም ላይ ከመሄድ ተመለሱ። 5ሮብዓምም በኢየሩሳሌም ተቀመጠ፤ በይሁዳም የተመሸጉትን ከተሞች ሠራ። 6በይሁዳና በብንያም ያሉትንም የተመሸጉትን ከተሞች፥ ቤተ ልሔምን፥ ኤጣምን፥ ቴቁሔን፤ 7ቤተሱራን፥ ሱላኮን፥ ዓዶላምን፥ 8ጌትን፥ መሪሳን፥ ዚፍን፥ 9አዶራይምን፥ ለኪስን፥ ዓዚቃን፤ 10ሶርዓን፥ ኤሎንን፥ ኬብሮንን ሠራ። 11ምሽጎቹንም አጠነከረ፤ አለቆችንም አኖረባቸው፤ ምግቡንም፥ ዘይቱንም፥ የወይን ጠጁንም አከማቸባቸው። 12በከተሞቹ ሁሉ አላባሽ አግሬ ጋሻና ጦርን አኖረ፤ ከተሞቹንም እጅግ አጠነከራቸው፤ ይሁዳና ብንያምም የእርሱ ወገን ነበሩ።
13በእስራኤልም ሁሉ ዘንድ የነበሩ ካህናትና ሌዋውያን ከየሀገራቸው ሁሉ ወደ እርሱ መጡ። 14የእግዚአብሔርም ካህናት እንዳይሆኑ ኢዮርብዓምና ልጆቹ አስለቅቀዋቸው ነበርና ሌዋውያን መሰምሪያቸውን ትተው ወደ ይሁዳና ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። 15እርሱ ግን ለኮረብታው መስገጃዎች፥ ከንቱ ለሆኑ ጣዖታቱም፥ ኢዮርብዓም ለሠራቸው እንቦሶችም ካህናትን አቆመ። 16ደግሞም ለአባቶቻቸው አምላክ ለእግዚአብሔር ይሠዉ ዘንድ ከእስራኤል ነገድ ሁሉ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን ለመፈለግ ልባቸውን የሰጡ ሁሉ እነርሱን ተከትለው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። 17ሦስት ዓመትም በዳዊትና በሰሎሞን መንገድ ይሄድ ነበርና ሦስት ዓመት የይሁዳን መንግሥት አበረቱ፤ የሰሎሞንንም ልጅ ሮብዓምን አጸኑ።
18ሮብዓምም የዳዊትን ልጅ የኢያሪሙትን ሴት ልጅ ሞላትን አገባ፤ እናቷም የእሴይ ልጅ የኤልያብ ልጅ አቢካኤል ነበረች። 19እርስዋም የዑስን፥ ሰማርያንና፥ ዘሃምን ወንዶች ልጆች ወለደችለት። 20ከእርስዋም በኋላ የአቤሴሎምን ልጅ መዓካን አገባ፤ እርስዋም አብያን፥ ኢያቲን፥ ዚዛን፥ ሰሎሚትን ወለደችለት። 21ሮብዓምም ከሚስቶቹና ከቁባቶቹ ሁሉ ይልቅ የአቤሴሎምን ልጅ መዓካን ወደደ፤ ዐሥራ ስምንትም ሚስቶችና ስድሳ ቁባቶች ነበሩት፤ ሃያ ስምንት ወንዶችና ስድሳ ሴቶች ልጆችንም ወለደ። 22ሮብዓምም ያነግሠው ዘንድ አስቦአልና የመዓካን ልጅ አብያን በወንድሞቹ ላይ አለቃ አድርጎ ሾመው። 23ብልሃተኛም ሆነ፤ ልጆቹንም ሁሉ በይሁዳና በብንያም ሀገር ሁሉ በምሽጉ ከተሞች ሁሉ ከፋፈላቸው፤ ብዙም ምግብ ሰጣቸው፤ ብዙም ሚስቶች ፈለገላቸው።#ምዕ. 11 ቍ. 23 በግእዝና በግሪክ ሰባ. ሊ. ያለው ግልጥ ስላልሆነ የዕብ. ተወስዶአል።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 11: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ