በነጋም ጊዜ፥ የሳኦል ልጅ ዮናታን ጋሻ ጃግሬውን፥ “ና፤ በዚያ በኩል ወዳለው ወደ ፍልስጥኤማውያን ሰፈር እንለፍ” አለው፤ ለአባቱም አልነገረውም። ሳኦልም በመጌዶን ባለው በሮማኑ ዛፍ በታች በኮረብታው ላይ ተቀምጦ ነበር፤ ከእርሱም ጋር የነበረው ሕዝብ ስድስት መቶ የሚያህል ሰው ነበረ። የዔሊ ልጅ፥ የፊንሐስ ልጅ፥ የዮካብድ ወንድም፥ የአኪጦብ ልጅ በሴሎ ለእግዚአብሔር ካህን የሆነ፥ ኤፉድም የለበሰ አኪያ አብሮ ነበር፤ ሕዝቡም ዮናታን እንደ ሄደ አላወቁም ነበር። ዮናታንም ወደ ፍልስጥኤማውያን ሰፈር ሊሻገርበት በወደደው መተላለፊያ መካከል በወዲህ አንድ ሾጣጣ፥ በወዲህም አንድ ሾጣጣ ድንጋዮች ነበሩ፤ የአንዱም ስም ባዚስ፥ የሁለተኛውም ስም ሴና ነበረ። አንደኛዋ መንገድ በማኪማስ አንጻር በመስዕ በኩል የምትመጣ ናት፤ ሁለተኛዋም መንገድ በገባዖን አንጻር በአዜብ በኩል የምትመጣ ነበረች። ዮናታንም ጋሻ ጃግሬውን፥ “ና፥ ወደ እነዚህ ቈላፋን ሰፈር እንለፍ፤ በብዙ ወይም በጥቂት ማዳን እግዚአብሔርን አያስቸግረውምና ምናልባት እግዚአብሔር ይረዳን ይሆናል” አለው። ጋሻ ጃግሬውም፥ “ልብህ ያሰኘህን ሁሉ አድርግ እነሆ፥ ከአንተ ጋር ነኝ፤ እንደ አንተ ልብ የእኔም ልብ እንዲሁ ነው” አለው። ዮናታንም አለው፥ “እነሆ፥ ወደ ሰዎቹ እናልፋለን፤ ወደ እነርሱም እንቀርባለን፤ እነርሱም፦ እስክንነግራችሁ ድረስ ርቃችሁ ቈዩ ቢሉን ርቀን እንቆማለን፤ ወደ እነርሱም አንወጣም። ነገር ግን ወደ እኛ ውጡ ቢሉን እግዚአብሔር በእጃችን አሳልፎ ሰጥቶአቸዋልና እንወጣለን፤ ምልክታችንም ይህ ይሆናል።” ሁለታቸውም ወደ ፍልስጥኤማውያን ሰፈር ገቡ፤ ፍልስጥኤማውያንም “እነሆ፥ ዕብራውያን ከተሸሸጉበት ጕድጓድ ይወጣሉ” አሉ። የሰፈሩም ሰዎች፦ ዮናታንንና ጋሻ ጃግሬውን “ወደ እኛ ውጡ፤ አንድ ነገርንም እንነግራችኋለን” አሉ። ዮናታንም ጋሻ ጃግሬውን “እግዚአብሔር በእስራኤል እጅ አሳልፎ ሰጥቶአቸዋልና ተከተለኝ” አለው። ዮናታንም በእጁና በእግሩ ወጣ፤ ጋሻ ጃግሬውም ከእርሱ ጋር ነበረ፤ ዮናታንም ፊቱን መልሶ ገደላቸው፤ ጋሻ ጃግሬውም ተከትሎ ገደላቸው። የዮናታንና የጋሻ ጃግሬውም በወንጭፍና በዱላ የመጀመሪያ ግድያቸው በአንድ ትልም እርሻ መካከል ሃያ ያህል ሰው ነበረ። በሰፈሩና በእርሻውም ድንጋጤ ሆነ፤ በሰፈሩ የተቀመጡ ሕዝብና የሚዋጉትም ሁሉ ተሸበሩ፤ መዋጋትም አልቻሉም፤ ምድሪቱም ተናወጠች፤ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ታላቅ ድንጋጤ መጣ። በብንያም ገባዖን ያሉ የሳኦል ዘበኞችም ተመለከቱ፤ እነሆም፥ ሠራዊቱ ወዲህና ወዲያ እየተራወጡ ተበታተኑ። ሳኦልም ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሕዝብ፥ “እስኪ ተቋጠሩ፤ ከእኛ ዘንድ የሄደ ማን እንደ ሆነ ተመልከቱ” አላቸው። በተቋጠሩም ጊዜ እነሆ፥ ዮናታንና ጋሻ ጃግሬው በዚያ አልተገኙም። በዚያም ቀን አኪያ በእስራኤል ልጆች ፊት ኤፉድ ይለብስ ነበርና ሳኦል፥ “ኤፉድን አምጣ” አለው። ሳኦልም ከካህኑ ጋር ሲነጋገር በፍልስጥኤማውያን መንደር ግርግርታ እየበዛ ሄደ፤ ሳኦልም ካህኑን፥ “እጅህን መልስ” አለው። ሳኦልና ከእርሱም ጋር የነበሩት ሕዝብ ሁሉ ተሰብስበው ወደ ውጊያው መጡ፤ እነሆም፥ የእያንዳንዱ ሰው ሰይፍ በባልንጀራው ላይ ነበረ፤ እጅግም ታላቅ ሽብር ሆነ። ቀድሞ ከፍልስጥኤማውያን ጋር የነበሩና ወደ ሠራዊቱ የወጡ አገልጋዮችም ከሳኦልና ከዮናታን ጋር ወደ ነበሩ እስራኤላውያን ለመሆን ተመለሱ። በተራራማውም በኤፍሬም ሀገር የተሸሸጉት እስራኤል ሁሉ ፍልስጥኤማውያን እንደ ሸሹ በሰሙ ጊዜ እነርሱ ደግሞ ሊዋጉአቸው ተከተሉአቸው። እግዚአብሔርም በዚያ ቀን እስራኤልን አዳነ፤ ውጊያውም በባሞት በኩል አለፈ። ከሳኦልም ጋር የነበሩ ሕዝብ ሁሉ ዐሥር ሺህ የሚያህሉ ሰዎች ነበሩ፤ ውጊያውም በተራራማው በኤፍሬም ከተማ ሁሉ ተበታትኖ ነበር።
መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 14 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 14:1-23
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች