ሳኦልም በእስራኤል ላይ ከነገሠ ሁለት ዓመት ሆነው፥ ያንጊዜም ሳኦል ሦስት ሺህ ሰዎችን ከእስራኤል መረጠ፤ ሁለቱም ሺህ በማኪማስና በቤቴል ተራራ ከሳኦል ጋር ነበሩ፤ አንዱም ሺህ በብንያም ገባዖን ከልጁ ከዮናታን ጋር ነበሩ፤ የቀረውንም ሕዝብ እያንዳንዱን ወደ ድንኳኑ አሰናበተ። ዮናታንም በኮረብታው የነበሩትን የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ መታ፤ ፍልስጥኤማውያንም ያን ሰሙ፤ ሳኦልም፦ እስራኤል ይስሙ ብሎ በሀገሩ ሁሉ ቀንደ መለከት ነፋ። እስራኤልም ሁሉ ሳኦል የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ እንደ መታ፥ ደግሞም እስራኤል በፍልስጥኤማውያን ዘንድ እንደ በረቱ ሰሙ፤ ሕዝቡም ደንፍተው ሳኦልን ለመከተል ወደ ጌልጌላ ተሰበሰቡ። ፍልስጥኤማውያንም ከእስራኤል ጋር ለመዋጋት ተሰበሰቡ፤ ሠላሳ ሺህ ሰረገሎች፥ ስድስት ሺህም ፈረሰኞች፥ በባሕርም ዳር እንዳለ አሸዋ ብዙ ሕዝብ ነበሩ፤ ወጥተውም ከቤቶሮን በአዜብ በኩል በማኪማስ ሰፈሩ። የእስራኤልም ሰዎች ወደ እነርሱ መሄድ እንደሚያስጨንቃቸው ባዩ ጊዜ ሕዝቡ በዋሻና በግንብ፥ በገደልና በቋጥኝ፥ በጕድጓድም ውስጥ ተሸሸጉ። ዮርዳኖስንም ተሻግረው ወደ ጋድና ወደ ገለዓድ ምድር የሄዱ አሉ፤ ሳኦል ግን ገና በጌልጌላ ነበረ፤ ሕዝቡም ሁሉ ፈርተው እርሱን መከተልን ትተው ተበተኑ። ሳኦልም ሳሙኤል እንደ ቀጠረው ጊዜ ሰባት ቀን ቈየ፤ ሳሙኤል ግን ወደ ጌልጌላ አልመጣም፤ ሕዝቡም ከእርሱ ተለይተው ተበታተኑ። ሳኦልም፥ “የሚቃጠል መሥዋዕትና የደኅንነት መሥዋዕት አምጡልኝ” አለ። የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አሳረገ። የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ማሳረግ በፈጸመ ጊዜ፥ እነሆ፥ ሳሙኤል መጣ፤ ሳኦልም እንዲባርከው ሊገናኘው ወጣ። ሳሙኤልም፥ “ያደረግኸው ምንድን ነው?” አለ። ሳኦልም፥ “ሕዝቡ ከእኔ ተለይተው እንደ ተበታተኑ፥ አንተም በነገርኸኝ መሠረት በቀጠሮው ቀን እንዳልመጣህ፥ ፍልስጥኤማውያንም ወደ ማኪማስ እንደ ተሰበሰቡ አየሁ፤ ስለዚህ፦ ፍልስጥኤማውያን አሁን ወደ እኔ ወደ ጌልጌላ ይወርዱብኛል፤ እኔም የእግዚአብሔርን ፊት አልለመንሁም አልሁ፤ ስለዚህም ደፍሬ የሚቃጠል መሥዋዕትን አሳረግሁ” አለ። ሳሙኤልም ሳኦልን፥ “በድለኻል፤ አምላክህ እግዚአብሔር ያዘዘህን ትእዛዙን አልጠበቅህምና፤ ዛሬ እግዚአብሔር መንግሥትህን በእስራኤል ላይ ለዘለዓለም አጽንቶልህ ነበር። ከእንግዲህ ወዲያ ግን መንግሥትህ አይጸናም፤ እግዚአብሔር እንደ ልቡ የሆነ ሰው መርጦአል፤ እግዚአብሔርም ያዘዘህን አልጠበቅህምና እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ንጉሥን ያነግሣል” አለው። ሳሙኤልም ከጌልጌላ ተነሥቶ መንገዱን ሄደ፤ የቀሩትም ሕዝብ ሳኦልን ተከትለው ሰልፈኞቹን ሊገናኙ ሄዱ። ከጌልጌላም ተነሥተው ወደ ብንያም ገባዖን መጡ፤ ሳኦልም ከእርሱ ጋር የነበሩትን ሕዝብ ቈጠረ፤ ስድስት መቶም የሚያህሉ ሰዎች ነበሩ።
መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 13 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 13:1-15
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች